ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | 22ኛ ሳምንት የሚያዚያ 21 ጨዋታዎች

ዛሬ እና ትናንት አራት ጨዋታዎች የተካሄዱበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ነገ ደግሞ መቐለ እና አዲስ አበባ ላይ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጉበታል። ጨዋታዎቹን የተመለከቱ ዋና ዋና ነጥቦችንም እንደተለመደው በቅድመ ጨዋታ ዳሰሳችን ተመልክተናቸዋል። 

መቐለ ከታማ ከ ወላይታ ድቻ

በ21ኛው ሳምንት ውጤታቸው ከድል መልስ የሚገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ጥሩ ፉክክር የሚስተናግድበት ጨዋታ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ከመሪው በአምስት ነጥቦች ብቻ ርቆ እና ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎችን ይዞ የተቀመጠው መቐለ ከተማ ደደቢት ላይ ያሳካው ድል በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ያለውን ቦታ ለማጠናከር በእጅጉ ጠቅሞታል። ከዚህ ውጤት በኃላ ወደ ሜዳው መመለሱ ደግሞ ለቡድኑ ይበልጥ የዐዕምሮ ጥንካሬን የሚያላብስ ይሆናል። ከአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውጪ ከሆነ በኃላ በእዮብ አለማየሁ ሶስታ ታግዞ ፋሲልን የረታው ወላይታ ድቻ ደግሞ ሙሉ ትከረቱን ወደ ሊጉ አድርጓል። ድቻ እንደተጋጣሚው ሁሉ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ቢኖሩትም እስካሁን የሰበሰበው 27 ነጥቦችን በመሆኑ ደረጃውን አሻሽሎ ራሱን ወደ ፉክክሩ ለማስጠጋት ከሜዳ ውጪ ያለውን ደካማ ሪከርድ ማሻሻል እና ከመሰል ጠንካራ ቡድኖች ነጥቦችን ማግኘት የሚኖርበት በመሆኑ ከመቐለው ጨዋታ በአሸናፊነት ለመመለስ ይፋለማል።

የመቐለ ከተማዎቹ ያሬድ ከበደ እና ዳንኤል አድሃኖም እንዲሁም የወላይታ ድቻው ፀጋዬ ብርሀኑ በጉዳት ከዚህ ጨዋታ ውጪ ናቸው። በሌላ በኩል ያሬድ ዳዊትን በጉዳት የሚያጣው ወላይታ ድቻ እርቅይሁን ተስፋዬ ከጉዳት ታመልሶለታል። 

በውድድሩ አጋማሽ የተወሰኑ ግዢዎችን የፈፀመው መቐለ ከተማ ላመጣቸው ተጨዋቾች በሚሰጠው ሀላፊነት የሚና ቅይይሮችን ሲያደርግ ይስተዋላል። የዐመለ ሚልኪያስ እና ሚካኤል ደስታ ጥምረት በጋቶች ፓኖም መምጣት የአስር ቁጥር እና የጥልቅ አማካይነት ሚና ላይ ለውጦችን ሲያደርግ አማኑኤል ገ/ሚካኤል እና ቢስማርክ ኦፖንግም እንዲሁ በፊት አጥቂነት እና በመስመር አማካይነት ሚና ላይ ሲተካኩ ይታያል። ልውውጦቹ እንደጨዋታው ሁኔታ በሜዳ ላይ የሚደረጉ መሆናቸው ቡድኑ ተገማች እንዳይሆን ከማድረጉም በላይ ለተጋጣሚ ቡድኖች ግርታን የሚፈጥር ነው። በዛው ልክ ደግሞ የቡድን ውህደት ላይ የሚፈጥረው ጫና የሚነሳ ነው። በጥቅሉ ግን ቡድኑ በተለይ ለመልሶ ማጥቃት የተመቸ ሆኖ ሲታይ ከጋቶች ፓኖም እና ፎስይኒ ኑሁ የምነሱ ኳሶች ለአማኑኤል ቀጥተኛ ጥቃት የተመጠኑ ናቸው። ይህ አቀራረባቸው ጥሩ የመከላከል ሽፋን ከሚሰጠው  የወላይታ ድቻ የአማካይ ክፍል ጋር ሲገናኝ በጨዋታው ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለውም ተጠባቂ ይሆናል። 

አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ሀላፊነቱን ከተረከቡ በኃላ በማይለዋወጥ የአሰላለፍ እና የጨዋታ ዘይቤ እንዲሁም በማይቀያየር የተጨዋቾች ምርጫ ጥሩ የሚባል መናበብን የፈጠረው ወላይታ ድቻ አሁን ደግሞ እንደ ፀጋዬ ባልቻ እና እዮብ አለማየሁ የመሳሰሉ ተጨዋቾችን ወደ ዋና አሰላለፍ ማስገባት መጀመሩ እየጠቀመው ይገኛል። ተጨዋቾቹ የተሰጣቸውን ሀላፊነት በአግባቡ እየተወጡ መሆናቸውም ለአሰልጣኙ አማራጮችን እየፈጠረላቸው ይገኛል። በነገውም ጨዋታ የኃይማኖት ወርቁ እና አብዱልሰመድ አሊ የአማካይ ክፍል የሜዳ ቁመት ጥምረት መቐለዎች በቀላሉ ጥቃቶችን እንዳይሰነዝሩ ለማድረግ ሀላፊነት እንደሚሰጠው ሲገመት ከመስመር አማካዮቹ እና ከበዛብህ መለዮም የሚነሱ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች በጥልቀት ወደ ኃላ በመሳብ እና ወደ መስመሮችም በመውጣት ተከላካዮች ላይ ጫና ከሚፈጥረው ጃኮ አራፋት እንቅስቃሴ ጋር በመደመር የቡድኑ ዋነኛ የግብ ዕድል መፍጠሪያዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል። 

የእርስ በእርስ ግንዝኙነት እውነታዎች

– በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገናኙበት የ7ኛው ሳምንት ጨዋታ መቐለ በቢስማርክ ኦፖንግ ብቸኛ ጎል ሶዶ ላይ 1-0 ማሸነፍ ችሏል። 

– እስካሁን በሜዳው አንድ ጊዜ ብቻ ሽንፈት የደረሰበት መቐለ ከተማ ለመጨረሻ ጊዜ መቐለ ላይ ጨዋታ ያደረገው ሁለተኛው ዙር በጀመረበት ሳምንት ሲሆን በዛን ጊዜ አርባምንጭን 4-0 መርታት ችሎ ነበር።

– ሳምንት በቅጣት ምክንያት ሰበታ ላይ ፋሲልን ከገጠመበት ጨዋታ ውጪ ወላይታ ድቻ በሁለተኛው ዙር ለመጀመሪያ ጊዜ ከሜዳው የሚወጣ ሲሆን 14ኛው ሳምንት ላይ በጅማ 2-1 የተሸነፈበት ጨዋታ የመጨረሻው የሜዳ ውጪ ጨዋታው ነበር።

ዳኛ

– ፌደራል ዳኛ ወልዴ ንዳው ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት እንዲመራ ተመድቧል። 


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ኢትዮጵያ ቡና ከ ጅማ አባ ጅፋር

ይህ የአዲስ አበባ ስታድየሙ የዕለቱ ብቸኛ ጨዋታ በሳምንቱ ከሚደረጉት ጨዋታዎች ሁሉ ትልቅ ግምት የተቸረው ነው። ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታውን በማሸነፍ ራሱን ከመሪው ጋር ሊያስተካክል ይችልበት የነበረውን ዕድል በሸገር ደርቢ ሽንፈቱ ምክንያት ቢያጣም የዋንጫው ኮስታራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቀጠል ከዚህ ጨዋታ ሶስት ነጥብ የማሳካት ግዴታ አለበት። ጅማ አባጅፋርም ቢሆን ሊጉን እየመራ ይገኝ እንጂ ተስተካካይ ጨዋታ ያላቸው የቅርብ ተፎካካሪዎቹ ሊደርሱበት የሚችሉበት ዕድል ያለ በመሆኑ መሪነቱን ለማስቀጠል ከእያንዳድንዱ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ለማግኘት መጣር ይኖርበታል። ሁለቱ ክለቦች ካሉበት ደረጃ አንፃር ሽንፈት ብቻ ሳይሆን የአቻ ውጤትም ተጠቃሚ የማያደርጋቸው በመሆኑ ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይገመታል።

የኢትዮጵያ ቡናው የመሀል ተከላካይ አክሊሉ አያናው ጉዳት የገጠመው ከመሆኑ በቀር በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተሰማ የጉዳት ዜና የለም። በቅጣትም ከሌላው የቡና ተከላካይ አስናቀ ሞገስ ውጪ ጨዋታው የሚያመልጠው ተጨዋች አይኖርም።

ኢትዮጵያ ቡና በሸገር ደርቢ ባልተጠበቀ መልኩ ባፒቲስቴ ፋዬን የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በማስገባት ለአጥቂው ከሚጣሉ ኳሶች መነሻነት ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከረበት መንገድ እምብዛም ውጤታማ አልሆነም። ቡድኑ ለዚህ አካሄድ ቅድሚያ የሰጠበትን ምክንያት መናገር ባይቻልም በነገው ጨዋታ ላይ እንደሚደግመው ማሰብ ግን ይከብዳል። እንደመጀመሪያ እቅዱ ተደርጎ በሚወሰደው እና በኳስ ቁጥጥር የበላይነት ላይ በተመሰረተው አጨዋወቱ ደግሞ በተከላካይ እና አማካይ መስመሮች መሀል ክፍተትን በማይሰጠው የተጋጣሚው አደረጃጀት ውስጥ ቁልፍ የሚባሉ አማካዮቹ ቦታ አያያዝ እጅግ ወሳኝ ይሆናል። በተለይ ቡድኑ በማጥቃት ሂደት ላይ የሜዳውን ስፋት አብዝቶ በመጠቀም እና አባ ጅፋሮች በመሀል ክፍተት እንዲፈጥሩ በማድረግ እንደ ኤልያስ ማሞ ያሉ አማካዮች የመጨረሻ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን ማድረስ ከሚችሉበት ቦታ ላይ እንዲገኙ የማድረግ ግዴታ ይኖርበታል። 

ኢትዮጵያ ቡናን በገጠሙበት የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ የተጋጣሚያቸውን የኳስ ቁጥጥር በመስበር በመልሶ ማጥቃት ግብ ማስቆጠር የሚችሉበትን አማራጭ በአግባቡ የተጠቀሙት ጅማዎች ነገም ይህንኑ እንደሚተገብሩ ይታሰባል። በአሚኑ ነስሩ እና ይሁን እንዳሻው ጥምረት አማካይ ክፍል ላይ ከሚነጠቁ ኳሶች ሔኖክ ኢሳያስ እና ዮናስ ገረመው በሁለቱም መስመሮች ቀርበው ኳስ በመቀበልም ሆነ ቀጥተኛ ሩጫዎችን በማድረግ አደጋ ከሚፈጥሩት አጥቂዎቻቸው ጋር በሚያደርጓቸው ቅብብሎች ከኢትዮጵያ ቡና የኃላ ክፍል ጀርባ መገኝት ለጅማ ዋነኛ አደጋ የመፍጠሪያ መንገድ ይሆንለታል። አባ ጅፋር በዚህ መንገድ የሚገኙ ዕድሎችን ወደ ግብ ለመቀየር የሚችሉ አጥቂዎችን በተለይም ኦኪኪ አፎላቢን የያዘ ቡድን መሆኑ ደግሞ ለአሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል።  

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ጅማ አባ ጅፋር ወደ ፕሪምየር ሊጉ ባደገበት በያዝነው አመት 7ኛው ሳምንት ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ጅማ ላይ አስተናግዶ ከጨዋታ ብልጫ ጋር 2-0 ማሸነፉ ይታወሳል።

– ኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ የክልል ቡድኖችን ከገጠመባቸው 7 አጋጣሚዎች 4 ጊዜ ድል ሲቀናው አንዴ ደግሞ ተሸንፏል።

– ጅማ አባ ጅፋር በሁለተኛው ዙር ከሜዳው በወጣባቸው 3 አጋጣሚዎች 4 ነጥቦችን ማሳካት ችሏል።

– ኢትዮጵያ ቡና በሁለተኛው ዙር ምንም ጨዋታዎችን አቻ አልተለያየም። 4 ድል እና 2 ሽንፈት በ6ቱ ጨዋታዎች ያስመዘገባቸው ውጤቶች ናቸው።

– አባጅፋር በዘንድሮው የሊጉ ቆይታው ሶስቴ ወደ አዲስ አበባ ስታድየም የመጣ ሲሆን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለግብ ተለያይቶ ደደቢትን አሸንፎ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ገጥሞታል። 

ዳኛ

– ይህን ጨዋታ የመዳኘት ሀላፊነቱ የተሰጠው ለፌደራል ዳኛ ማኑዬ ወ/ፃዲቅ ነው።