ሪፖርት | ኤሌክትሪክ ላለመውረድ በሚያደርገው ትግል ወስጥ ወሳኝ ድል አሳክቷል

በአዲስ አበባ ስታድየም ወልዲያን ያስተናገደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአንጋፋው አጥቂ ታፈሰ ተስፋዬ ድንቅ ግብ ታግዞ 1-0 በማሸነፍ ከሊጉ ግርጌ ተላቆ ወደ 12ኝነት ከፍ ብሏል።

ከ21ኛው ሳምንት ጨዋታዎች አንፃር በሁለቱም ተጋጣሚዎች በኩል በርካታ የተጨዋች ለውጦች ታይተዋል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በጅማ አባ ጅፋር 4-0 ከተሸነፈው የመጀመሪያ አሰላለፉ ውስጥ ግርማ በቀለ ፣ ጫላ ድሪባ ፣ ዲዲዬ ለብሪ እና ቅጣት ላይ የሚገኘው በሀይሉ ተሻገርን በሲሴ ሀሰን ስንታየሁ ዋለጬ ፣ ስንታየሁ ሰለሞን እና ጥላሁን ወልዴ ተክተዋል። በወልዲያ በኩል ደግሞ አመረ በቀለ ፣ ብርሀኔ አንለይ እና ዳንኤል ደምሴ በሲዳማ ቡና ከተሸነፈው ቡድን ውስጥ ያረፉ ሲሆን በምትካቸው ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኃላ ወደሜዳ የተመለሰው አዳሙ መሀመድ ፣ ያሬድ ሀሰን እና ምንያህል ተሾመ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በርከት ያሉ ሙከራዎችን ባያስመለክተንም ጥሩ የጨዋታ ፍሰት እና ፍጥነት ነበረው። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወልዲያዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በመያዝ እንዲሁም የተጋጣሚያቸው የኃላ መስመር ኳስን በነፃነት እንዳይቀባበል በማድረግ ጫና በመፍጠሩ በኩል ተሳክቶላቸው ነበር። ከምንያህል ተሾመ የሚነሱ ኳሶች እና ከግራ መስመር አማካዩ መስፍን ኪዳኔ የሚሻገሩ ኳሶች ለቡድኑ ዋነኛ የጥቃት መሳሪያ ሆነው ሲያገለግሉም ነበር። ወልዲያዎች የጠራ የግብ ዕድልን አይፍጠሩ እንጂ ወደ መጨረሻው የግብ ክልል በመድረሱም በኩል የተሻሉ ነበሩ። ሆኖም ኢትዮ ኤሌክሪኮች የወልዲያ የኳስ ስርጭት ዋነኛ ማዕከል የሆነውን ምንያህል ተሾመ በስንታየው ዋለጬ ማርክ ካደረጉ በኃላ ወልዲያዎች ብዙ ሜዳ አካለው ለመጫወት ሲሞክሩ ለሚታዩት አጥቂዎቻቸው ኤደም ኮድዞ እና አንዷለም ንጉሴ ኳሶችን ማድረስ ተስናቸዋል። እንደመጀመሪያው ደቂቃዎችም በኢትዮ ኤሌክትሪክ ሜዳ ላይ ብዙ ሰዐት ማሳለፍ አልቻሉም። 

በሂደት ወደ ጨዋታው መግባት የቻሉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በረጃጅሙ ወደፊት ከሚጥሏቸው ኳሶች እምብዛም ስኬትን ባያገኙም የተጋጣሚያቸውን የመሀል ሜዳ የበላይነት መቆጣጠር ከቻሉ በኃላ ግን በቅብብሎች ወደ ወልዲያ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል የሚቀርቡባቸውን አጋጣሚዎች ማበራከት ችለዋል። በተለይም በቡድኑ የግራ ወገን የተሰለፉት ስንታየው ዋለጬ እና የመስመር ተከላካዩ ስንታየው ሰለሞን የተሻለ የቅብብል ስኬት በማሳየት እና ከብድኑ የጨዋታ ፍሰት ጋር ተናበው በማጥቃት ለቡድናቸው ዋነኛ ጥንካሬ ሆነዋል። ታፈሰ ተስፋዬ በ28ኛው ደቂቃ በድንገት በወልዲያ የግብ አፋፍ ላይ ተገኝቶ የኢትዮ ኤሌክትሪክን ጎል ሲያስቆጥርም ኳሱን መጥኖ ያሻገረለት የግራ መስመሩ ተከላካይ ስንታየሁ ሰለሞን ነበር። ከግቡ ውጪ በጥላሁን ወልዴ የርቀት ሙከራ ያደረጉት ኤሌክትሪኮች መጨረሻ ደቂቃ ላይ ታፈሰ ተስፋዬ ከቀኝ መስመር ባሻገረው ኳስ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ቢቃረቡም ኃይሌ እሸቱ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

የሁለተኛው አጋማሽ አጀመመር ከመጀመሪያው አንፃር ቀዝቀዝ ያለ ነበር። ሆኖም ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በመጀመሪያው አጋማሽ ማብቂያ ያገኙትን የበላይነት ማስቀጠል ችለዋል። የአቻነት ግብ ለማግኘት ወደፊት ተጠግተው ለመጫወት ይሞክሩ የነበሩት ወልዲያዎች ከኃላቸው ይተው በነበረው ክፍተት ላይ የተሻለ ነፃነት አግኝተው ለመንቀሳቀስ ዕድሉ የተፈጠረላቸው ኤሌክትሪኮች በብዛት በግራ መስመር ከሚነሱ ኳሶች ጫና ሲፈጥሩ ተስተውለዋል። ይሁን እንጂ ወደ ወልዲያ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ሰብረው ይገቡ የነበሩባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ነበሩ። 67ኛው ደቂቃ ላይ ድንቅ ሆኖ ያመሸው ስንታየው ዋለጬ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቷት በግቡ አግዳሚ የተመለሰችው ኳስ እና ይሄው ተጨዋች ወደ ጨዋታው ማብቂያ ከዲዲዬ ለብሪ በተሻገረለት ኳስ ነፃ ሆኖ ሞክሯት ለጥቂት የወጣችው ኳስ የባለሜዳዎቹ የሁለተኛ አጋማሽ ጥሩ ሙከራዎች ነበሩ። 

እንደመጀመሪያው በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ይፈጥሩ የነበሩትን ጫና መድገም ያልቻሉት ወልዲያዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱንም መልሰው ባለመያዛቸው አልፎ አልፎ የሚመጡ የመልሶ ማትቃት ሂደቶችን ለመጠቀም ጥረት አድርገዋል። በተለይ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ የግራ መስመር ተከላካይ ስንታየሁ ሰለሞን ለማጥቃት ወደ ፊት ሲሳብ የሚተወውን ክፍተት በበላይ አባይነህ እንዲሁም እሱን ቀይሮ በገባው አሳልፈው መኮንን አማካይነት ለመጠቀም ሞክረዋል። ሆኖም በዚህ መንገድ እና ጥሩ በሚባሉ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ዕድሎችን አግኝተው አደጋ ክልል ውስጥ ቢገኙም በተሳሳቱ ቅብብሎች ምክንያት ጥረታቸው ፍሪያማ ሳይሆን ቀርቷል። ነገር ግን መጨረሻ ደቂቃ ላይ አሳልፈው መኮንን ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ አሻግሮት ሱሊማና አቡ እንደምንም ያወጣው እና እሱን ተከትሎ የተሰጠው የማዕዘን ምት ሲሻማ ቢያድግልኝ ኤልያስ በግንባሩ የሞከረው ኳስ የቡድኑ ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ። ወልዲያዎች በዚህ መልኩ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ ጫና ቢፈጥሩም የአቸነት ጎል ሳያገኙ ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

ም/አሰልጣኝ ቦጋለ ዘውዴ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ጨዋታው ለሁለታችንም አስፈላጊ ነበር። ተጨዋቾቻችንም ከፍተኛ መስዋትነት ከፍለው ከወራጅ ቀጠና የሚያወጣንን ሶስት ነጥብ አስገኝተዋል። በተደጋጋሚ በርካታ ግቦች እየተቆጠሩብን ስለነበር ተከላካይ ክፍላችን ላይ የነበረውን ችግር ለማስተካከል ሞክረናል። አሁንም የሚቀረው ነገር ቢኖርም በመከላከሉ እና በስነልቦናው በኩል ያሉብንን ችግሮች ማስተካከላችን ጠቅሞናል። በቀጣይም ይህን ውጤት አስቀጥለን ሳንወርድ በሊጉ ለመቆየት ጥረታችንን እንቀጥላለን።  

አሰልጣኝ ኃይማኖት ግርማ – ወልዲያ

ውጤቱ ለሁለታችንም በጣም አስፈላጊ ነበር። ከእረፍት በፊት እነሱ የተሻሉ ነበሩ። ከእረፍት መልስ ግን እኛ የተሻለ ወደ ጎል ለመድረስ ሞክረን ነበር። ያገኘናቸውን ዕድሎች መጠቀም አልቻልንም እንጂ። ቡድናችን በአብዛኛው ካወቃቅቀሩ ጅምሮ የስኳድ ጥበት እና በርካታ ጉዳቶች ያሉበት በመሆኑ ባሉን ተጨዋቾች ነው እየጠጋገንን ለመጫወት የምንሞክረው። ምንአልባትም ከዚህ በኃላ ያሉትንም ጨዋታዎች ከባድ ሊያደርግብን ይችላል።