ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

በ22ኛው ሳምንት የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማን ከ ሀዋሳ ከተማ ጋር ያገናኘው ጨዋታ በድራማዊ ክስተት ታጅቦ 1 – 1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማ ወደ አዳማ አቅንቶ በአዳማ ከተማ 1-0 ተሸንፎ ከተመለሰበት ስብስቡ ሳውሬል ኦልሪሽ እና ዮሴፍ ደንገቱን አሳርፎ በምትኩ ያሬድ ታደሰ እና ዮሴፍ ዳሙዬን ሲያስገባ በአንፃሩ ሀዋሳዎች በሜዳቸው በመከላከያ የ 4 – 0 በሆነ ከባድ ሽንፈት ካስተናገዱበት ስብስባቸው ዳንኤል ደርቤ እና ያቡን ዊልያምን አሳርፈው ፣ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃንን ደግሞ በቅጣት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ በመሆኑ ሲይላ መሀመድ ፣ ታፈሰ ሰለሞን እና እስራኤል እሸቱን በማስገባት ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ፌደራል ዳኛ ይርጋለም ወ/ጊዮርጊስ  በመሩት በዚህ ጨዋታ በሁለቱም በኩል በፈጣን የጨዋታ እንቅስቃሴ ወደ ጎል በመድረስ ጎል ለማስቆጠር የሚያሳዩት አጨዋወት ለተመልካቹ አዝናኝ ነበር ። በተለይ ሀዋሳዎች በሚታወቁበት ለጎል የቀረበ አጨዋወታቸው ከድሬዎቹ የተሻሉ አድርጓቸው የነበረ ቢሆንም ታፈሰ ሰለሞን እና ፍሬው ሰለሞን የሚያገኙትን ነፃ ኳስ ለአጥቂዎቹ ዳዊት ፍቃዱ እና ለእስራኤል እሸቱ በተገቢው መልኩ አለማድረሳቸው እንደወሰዱት ብልጫ በጨዋታው 15 ደቂቃ ውስጥ ጎል እንዳያስቆጥሩ አድርጓቸዋል። በሙከራ ረገድ እንግዶቹ ሀዋሳዎች በ11 ኛው ደቂቃ ላይ ሲላ መሀመድ ከመዓዘን ምት የተሻገረውን ኳሱ አጠንክሮ አለመምታቱ በቀላሉ ግብጠባቂው ሳምሶን ጥላሁን ያወጣበት የሚጠቀስ ነው። ድሬዎች በተደጋጋሚ በሀዋሳ ከተማ የቀኝ መስመር የሜዳ ክፍል አድልተው በበረከት ይስሀቅ አማካኝነት በሚፈጠሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ጎል ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም በረከት ይስሐቅ የሚያገኛቸውን ነፃ ኳሶች ራሱ ያለመጨረስ እና ለቡድን አጋሮቹ የግብ ዕድል የመፍጠር ችግር አሁንም ቡድኑን ዋጋ ማስከፈሉን ቀጥሏል። 16 ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ ፍሬው ሰለሞን ያሻገረለትን ኳስ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመልስ ጨዋታውን ለማድረግ ወደ ቡሩንዲ አቅንቶ 1-0 ተሸንፎ ከማጣርያው ውጭ በሆነው ስብስብ ውስጥ ተካቶ ወደ ስፍራው በማቅናት የመጀመርያውን የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ያደረገው እስራኤል እሸቱ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከሳምሶን አሰፋ ጋር ብቻውን ተገናኝቶ በጥሩ ሆኔታ ጎል በማስቆጠር ሀዋሳዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ጎል ያስተናገዱት ባለሜዳዎቹ ወደ ጨዋታው በፍጥነት ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ከፊት ያሉት አጥቂዎች ከትኩረት ማጣት የተነሳ በተለይ በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት በ21 እና 23 ደቂቃ ላይ ያሬድ ታደሰ በጥሩ ሁኔታ ያቀበለውን ሀብታሙ ወልዴ ሳይጠቀምበት መቅረቱ ደጋፊውን ለተቃውሞ ድምፁን እንዲያሰማ አድርጎታል ። ድሬዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ በሙሉ ኃይላቸው ለማጥቃት በሚያደርጉት ሽግግር ውስጥ ባክኖ የሚመለሰውን ኳስ በመልሶ ማጥቃት በተደጋጋሚ በድሬዳዋ የሜዳ ክፍል የሀዋሳ አጥቂዎች ከድሬ ተከላካዮች በቁጥር በዝተው የግብ አጋጣሚ  አግኝተው ጎል ለማስቆጠር በሚያደርጉት ከልክ ያለፈ ጉጉት የተነሳ ኳሶች ይባክኑ የነበረ መሆኑ እንግዶቹን ሀዋሳዎች የኋላ የኋላ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። በተለይ 44 ኛው ደቂቃ ላይ ከመአዘን ምት የተሻገረውን ጋብርኤል አህመድ በግንባሩ ወደ ጎል መትቶ ቋሚው ጋር ተደርቦ ይከላከል የነበረው አንተነህ ተስፋዬ እንደምንም ያወጣው ኳስ ለሀዋሳዎች ተጨማሪ ጎል የሚያስቆጥሩበት አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።

ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንደ መጀመርያው አጋማሽ መልካም እንቅስቃሴ አሳይቶን ያላለፈ ቢሆንም ብዙ ድራማዊ ክስተቶችን አስመልክቶን አልፏል ። በሁለተኛው ዙር ከኢትዮዽያ ቡና ወደ ድሬዳዋ የተመለሰው በረከት ይስሐቅ እንደወትሮ ሁሉ ዛሬም በግሉ የሚያደርገው ጥረት መልካም ቢሆንም በተደጋጋሚ የሚሰራቸው ስህተቶች ከተመልካቹ ከፍተኛ ተቃውሞ በማስከተሉ የተነሳ አሰልጣኝ ስምኦን አባይ በጉዳት ያለፉትን ሳምንታት ከጨዋታ ውጪ የነበረውን አትራም ኩዋሜን ቀይረው በማስገባት ተቃውሞውን ለማብረድ ጥረት አድርገዋል። ተመልካቹ አሰልጣኝ ስሞን አባይ ላይ ሲያሳይ የነበረው ተቃውሞ በርትቶ የጨዋታውን ቀሪ 25 ደቂቃዎች ከተቀመጡበት ቦታ ሳይነሱ ጨዋታውን ለመጨረስ ተገደዋል። ድሬዎች ያደረጉት ቅያሪ በአንፃራዊነት የማጥቃት እንቅስቃሴውን የተሻለ ቢያደርገውም ለጎል ለማስቆጠር ዘግይተዋል ። በአንፃሩ ሀዋሳዎች ኳሱን ተቆጣጥረው የሚያደርጉት የተሳካ ቅብብሎሽ መልካም የሚባል ቢሆንም የግብ እድል ለመፍጠር ባያስችላቸውም የድሬደዋ ስፖርት ቤተሰብ በእንቅስቃሴያቸው በመማረክ አድናቆቱን በጭብጨባ ይገልፁላቸው ነበር ። 

68ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አትራም ኩዋሜ በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ አምልጦ በመግባት ግሩም ጎል አስቆጥሮ ድሬዎችን አቻ ማድረግ ችሏል። ከጎሉ መቆጠር በኋላ ጉዳት አጋጠመኝ ያለው የሀዋሳው ግብጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳ ተቀይሮ እስኪወጣ እና እሱን ተክቶ የሚገባው ተክለማርያም ሻንቆ እስኪገባ ድረስ የወሰደው ረጅም ደቂቃ ተመልካቹን ለከፍተኛ ተቃዉሞ ሲያነሳሳ ተመልክተናል። ጨዋታው ከተቋረጠበት ቀጥሎ ሙሉ ብልጫ ወስደው ሲያጠቁ የነበሩት ድሬዎች 86ኛው ደቂቃ ላይ በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ያሬድ ታደሰ ላይ ግብ ጠባቂው ተክለማሪያም ሻንቆ ጥፋት በመስራቱ የተሰጠውን ፍ/ቅ/ምት አትራም ኩዋሜ ቢመታውም የግቡ አግዳሚ የመለሰበት አጋጣሚ ላለመውረድ ለሚፍጨረጨሩት ድሬዎች የሚያስቆጭ አጋጣሚ ሲሆን የደጋፊዎቹን ስሜት በእጅጉ የጎዳ አጋጣሚ ነበር ። ፌደራል ዳኛ ይርጋለም ወ/ጊዮርጊስ በሰጡት 10 ተጨማሪ ደቂቃ ውስጥ ድሬዳዋ ከተማዎች በዮሴፍ ዳሙዬ አማካኝነት ጎል አስቆጥረው በሚያስገርም ሁኔታ ተጨዋቾቹ ደጋፊዎች ደስታቸውን እየገለፁ ባለበት ቅስበት ረዳት ዳኛው ከጨዋታ ውጭ ነው በሚል ባሳዩት ምልክት የመሀል ዳኛው ይርጋለም ወ/ጊዮርጊስ ጎሉን መሻራቸው ከደስታ ወደ ሀዘን የተለወጠ ድራማዊ ትዕይንት አስመልክቶን ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል ። 

ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ በወራጅ ቀጠናው ለመቆየት ሲገደድ ሀዋሳ ለአንድ አመት የቆየውን ከሜዳ ውጭ ሦስት ነጥብ እየናፈቀ መዝለቁን ቀጥሎበታል።

አሰልጣኞች አስተያየት 

ውበቱ አባተ 

ጨዋታው ጥሩ ነበር በመጀመርያው አጋማሽ እንደወሰድነው ብልጫ ጨዋታውን ገድለን መውጣት ነበረብን። ያን ባለማድረጋችን ከእረፍት መልስ ተጭነው ብልጫ የወሰዱት ድሬዎች ነጥብ ተጋርተውናል። በጨዋታው ባልደሰትም አልተከፋውም።

* አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ ድህረ ጨዋታ አስተያየት ሳይሰጡ ቀርተዋል።