​ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና እና ጅማ አባ ጅፋር ነጥብ ተጋርተዋል

ከሳምንቱ ጨዋታዎች መሀከል ከፍ ያለ ግምት ተሰጥቶት የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና ጅማ አባጅፋር ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ቢደረግበትም ያለግብ ተጠናቋል። 

በሸገር ደርቢ ሽንፈት የገጠመው ኢትዮጵያ ቡና በዛሬው ጨዋታ የአራት ተጨዋቾች ለውጥ አድርጓል። በሰኞው ጨዋታ የተከላካይ ክፍሉ ላይ ከተጠቀመባቸው ተጨዋቾች መሀል ትዕግስቱ አበራ ፣ አስራት ቱንጆ እና ጉዳት የገጠመው አክሊሉ አያናው በወንድይፍራው ጌታሁን እና ኃይሌ ገብረትንሳይ ሲተኩ እያሱ ታምሩ የግራ መስመር ተከላካይነት ሚና ተሰጥቶታል። ከዚህ በተጨማሪም ወጣቶቹ ሚኪያስ መኮንን እና አቡበከር ነስሩም የመጀመሪያ ተሰላፊነት ዕድል አግኝተዋል። በጅማ አባ ጅፋር በኩል የታየው ብቸኛ ቅያሪ ቡድኑ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 4-0 ሲያሸንፍ ከጉዳት መልስ ከተቀያሪ ወንበር ላይ ተነስቶ ግብ ያስቆጠረው ተመስገን ገብረኪዳን ከፊት ሳምሶን ቆልቻን የተካበት ለውጥ ነው። 

ከጅምሩ በጥንቃቄ ተሞልቶ የተጠናቀቀው የቡድኖቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ፍልሚያ በርካታ ሙከራዎች ያልታዩበት ነበር። የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር አልፎ ግብ ለማስቆጠር የሚረዱ ቅብብሎችን ለማድረግ የተቸገሩት የዕለቱ ተጋጣሚዎች በመከላከል የጨዋታ ሂደት ውስጥ ሲገቡ የነበራቸው ትኩረት ከፍ ያለ ነበር። ልዩነት ሊፈጥሩ የሚችሉ የአማካይ ክፍል ተጨዋቾች በተጋጣሚዎቻቸው የተመሳሳይ ቦታ ተጨዋቾች ቁጥጥር ስር መውደቃቸው ለፊት አጥቂዎቻቸው ነገሮችን ከባድ አድርጎባቸዋል። ከሁሉም በላይ ትኩረት ይስብ የነበረው የመስመር ተከላካዮች እንቅስቃሴ እዚህ ላይ ተጠቃሽ ነው። በተለይ የጅማ አባ ጅፋሮቹ ኄኖክ አዱኛ እና ኤልያስ አታሮ የአቡበከር ነስሩን እና ሚኪያስ መኮንን እንቅስቃሴ እግር በእግር በመከተል እና የመስመር አጥቂዎቹ ከኳስ ጋር ሲገናኙ ፈጥኖ በመሸፈን ጥሩ መንቀሳቀስ ችለዋል። ጨዋታው ይህን አይነት መልክ የነበረው በመሆኑ እና ተጨዋቾች ኳስ በሚይዙበት አጋጣሚ በአቅራቢያቸው ያሉ የተቃራኒ ቡድን ተሰላፊዎች በሚወስዱት ፈጣን እርምጃ ምክንያት በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ተደጋጋሚ ግጭቶች እና የቅጣት ምቶችን የተመለከትንበት ነበር። 

እንደወትሮው መሀል ሜዳ ላይ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ማሳካት ያልቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች የአሚኑ ነስሩ እና ይሁን እንዳሻውን ጥምረት አልፈው በተጋጣሚያቸው የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ለመገኘት የቻሉባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ነበሩ። 19ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳኑሚ ከመስዑድ መሀመድ ተቀብሎ የሞከረው ኳስ ቡድኑ ወደ ግብ የቀረበበት የመጀመሪያ አጋጣሚ ሲሆን አዳማ ሲሶኮ ተደርቦ አውጥቶበታል። ከአንድ ደቂቃ በኃላ ደግሞ ሚኪያስ መኮንን በቀኝ መስመር በኩል የጅማን ተከላካዮች በአደናቂ ሁኔታ አልፎ በመግባት የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጃዬ አድኖበታል። እንደ ኢትዮጵያ ቡና ሁሉ የተረጋጋ የኳስ ቁጥጥርን ማሳካት ያልቻሉት ጅማዎች በዋናነት በግራ መስመር አማካይነት ወደ ተሰለፎ ወደነበረው ዮናስ ገረመው ከሚያደርሷቸው ኳሶች መነንነት ጥቃት ለመሰንዘር ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውለዋል። የ28ኛው ደቂቃ የዮናስ የርቀት ሙከራ እና 40ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ገብረኪዳን ከኄኖክ ኢሳያስ የተቀበለውን ኳስ ሞክሮ ኢላማውን ሳይጠብቅ የቀረበት እንዲሁም ሌላኛው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ 41ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማን ኳስ በግንባሩ የሞከረበት አጋጣሚ የሊጉ መሪዎች የተሻሉ ሙከራዎች ነበሩ። 

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው የተለየ መልክ ነበረው። ቡድኖቹ ለማጥቃት በመረጡባቸው መንገዶች ጥሩ የሚባሉ ክፍተቶችን ያገኙበት ፣ የጨዋታው ፍጥነት ጨምሮ የታየበት እና በርከት ያሉ ሙከራዎች የተደረጉበትም ጭምር ነበር። ኢትዮጵያ ቡና የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በተሻለ መልኩ ባገኘበት በዚሁ አጋማሽ 48ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳኑሚ ከተከላካዮች ጀርባ ተጥሎለት በቀጥታ በሞከረው ኢላማውን የጠበቀ ኳስ አደጋ መፍጠር ጀምሯል። የጅማ አባጅፋር የመሀል አማካዮች በደከሙባቸው እና ከትኩረት በወጡባቸው አጋጣሚዎች በፍፁም ቅጣት ምት ውስጥ የመገኘት አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻሉት ቡናማዎቹ በሳሙኤል ሳኑሚ እና ተቀይሮ በገባው አስራት ቱንጆ አማካይነት ያደረጓቸው ሙከራዎች በሚያስቆጭ መልኩ ኢላማቸውን መጠበቅ ሳይችሉ ቀርተዋል። ቡድኑ በተለይ በግራ መስመር ባደላ እንቅስቃሴ ወደ ውስጥ ለመግባት ያደርጋቸው የነበሩት ሌሎች ሙከራዎችም ንቁ በነበሩት የአባ ጅፋር ተከላካዮች ጥረት ወደ መጨረሻ የግብ ዕድልነት ሳይለወጡ ቀርተውል። ከዚህ ውጪ ኢትዮጵያ ቡና በበርካታ አጋጣሚዎች ይገኙ የነበሩ የቆሙ ኳሶችን መጠቀም አልቻለም። በቀጥታ ወደግብ ከተሞከሩት የክሪዚስቶንም ንታንቢ እና መስዑድ መሀመድ ቅጣት ምቶች በተጨማሪ ከመስመር ወደ ውስጥ ይጣሉ የነበሩትም የጎን ቅጣት ምቶች ሲባክኑ አምሽተዋል። የአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ የመጨረሻ ደቂቃ አማራጭ የሆነው እና መሰል አጋጣሚዎችን የመጠቀም ብቃት ያለው ባፕቲስቴ ፋዬ ዛሬም በጨዋታው መገባደጃ ላይ ተቀይሮ የገባ ቢሆንም ግብ ሳይቀናው ቀርቷል። 

የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌው አባ ጅፋር ከእረፍት መልስ ሙሉ ትኩረቱን ለመልሶ ማጥቃት ሰጥቷል። ኦኪኪ አፎላቢን ከፊት በማድረግ ሁለተኛ አጥቂው ተመስገን ገብረኪዳን ወደ ቀኝ መስመር አድልቶ ለዮናስ በመቅረብ በኢትዮጵያ ቡና ተጨዋቾች ላይ በሚፈጥረው ጫና ቡድኑ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሞክሯል። ይሁን እንዳሻው ለአሚኑ ነስሩ ቀርቦ በተጫወተበት እና የአማካይ ክፍሉ በብዛት ጥንቃቄን በመረጠበት ሁለተኛው አጋማሽ ነጂብ ሳኒ መላኩ ወልዴን ቀይሮ በመግባት በግራ መስመር ተከላካይነት ቦታ የተጫወተ ሲሆን ኤልያስ አታሮ ከዚህ ቦታ ወደ መላኩ የመሀል ተከላካይነት ሚና ተሸጋግሯል። በሁሉም አቅጣጫዎች የሚመጡ የኢትዮጵያ ቡናዎችን ጥቃት በመመከት ላይ ትከረት ያደረጉት ጅማዎች በሁለት አጋጣሚዎች ንፁህ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን አግኝተው ነበር። 78ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ በኦኪኪ የተጀመረው መልሶ ማጥቃት ግንባር ቀደሙ ሲሆን ኳሱን ተቀብሎ በግራ በኩል ነፃ ሆኖ ቀጥተኛ ሩጫ ያደረገው ተመስገን በቀኝ በኩል ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ለገባው ኄኖክ ኢሳያስ ለማድረስ የሞከረው ኳስ በሀሪሰን ጥረት ከሽፏል። ከሶስት ደቂቃዎች በኃላ ደግሞ በድጋሜ በታታሪነት ሲጫወት ያመሸው ተመስገን በቀኝ መስመር በኩል ካገኘው የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ያሳለፈው ኳስ ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል። ከሁለቱ አጋጣሚዎች ውጪ በጅማዎች በኩል የሚጠቀሰው ኦኪኪ 87ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የሞከረው ኳስ ሲሆን ሀሪሰን በቀላሉ ሊቆጣጠረው ችሏል።

በዚህ መልኩ ጨዋታውን ለማሸነፍ የሞከሩት ሁለቱ ክለቦች ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ተጠቃሚ የማያደርጋቸውን የአቻ ውጤት ይዘው ከሜዳ ወጥተዋል። በመሆኑም ጅማ አባጅፋር በ39 ነጥቦች ሊጉን መምራት ሲቀጥል ኢትዮጵያ ቡና 33 ነጥብ ካላቸው አምስት ቡድኖች መሀል አንዱ በመሆን በግብ ክፍያ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ – ኢትዮጵያ ቡና

ጨዋታው ጥሩ ነበር። ጨዋታውን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥረን ነበር ፤ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ። ሆኖም በቅብብሎቻችን ክፍተትን ለማግኘት ይበልጥ ታጋሽ መሆን ነበረብን። በወጣት ተጨዋቾች መጫወታችን ደግሞ ለቡድኑ የወደፊት ተስፋ ነው።  ማሸነፍ ባንችልም በተጨዋቾቼ ኮርቻለው። ማሸነፍ ቢገባንም ብዙ ዕድሎችን አባክነናል። በግብ ፊት ባለብን ድክመት ላይም ብዙ መስራት አለብን። 

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ጅማ አባ ጅፋር

ከተቻለ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ካልሆነ ደግሞ አቻ ለመውጣት ነበር የመጣነው። ጨዋታው ትንሽ አስቸጋሪ ነበር። ጥንቃቄ የተሞላበት የነበረ በመሆኑም ብዙ የግብ ዕድሎችን መፍጠር አልቻልንም። ነገር ግን የምንፈልገውን ነጥብ አግኝተናል። ይህ መሆኑ በቀጣይ ጨዋታዎች ሞራላችን ተጠብቆ እንድንቀጥል ያደርገናል። ያለመሸነፍ ጉዞን ማስቀጠል በራሱ አንድ ነገር ነው። ቡናም የሕዝብ ክለብ በመሆኑ እና በከፍተኛ ድጋፍ የሚጫወት ከመሆኑ አንፃር ውጤቱ ጥሩ ነው።