ሉሲዎቹ የሴካፋ ዋንጫ ዝግጅታቸውን ዛሬ ጀመሩ

ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የሴቶች የሴካፋ ዋንጫ ተሳታፊ የሆኑት ሉሲዎቹ በዛሬው እለት ጥሪ ከተደረገላቸው 24 ተጫዋቾች መካከል 23ቱ በተገኙበት የመጀመርያ ልምምዳቸውን ጀምረዋል። በዛሬው ልልምምድ ላይ ያልተገኘችው የድሬዳዋ ከተማዋ ጸጋነሽ ወረቶ በዚህ ሁለት ቀን ውስጥ ከቡድኑ ጋር ተቀላቅላ ልምምድ የማትጀምር ከሆነ አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ በምትኩ ለሌላ ተጫዋች ጥሪ ታቀርባለች ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ ውድድር በቀጣይ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከአልጄሪያ ጋር ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ለሚደረገው የመጨረሻ ማጣርያ ወሳኝ ጨዋታ በቂ መዘጋጃ የሚሆን በመሆኑ ተሳታፊ መሆናችን ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግራለች።

ግንቦት መጨረሻ  ላይ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የሴቶች የሴካፋ ዋንጫ በሩዋንዳ አስተናጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን በቅርቡ የተሳታፊ ሀገራት ብዛት እና የምድብ ድልድሉ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ።

አምና በዩጋንዳ አስተናጋጅነት በተደረገው የሴቶች የሴካፋ ዋንጫ ላይ ሉሲዎቹ በአሰልጣኝ መሰረት ማኒ እየተመሩ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወቃል።