የሴካፋ ሴቶች ቻምፒየንሺፕ የሚጀመርበት ቀን ተራዘመ

ሩዋንዳ የምታስተናግደው የሴካፋ ሴቶች ቻምፒየንሺፕ ከአራት ቀናት በኃላ ኪጋሊ ላይ እንደሚጀመር አስቀድሞ የወጣው መርሃ ግብር ቢጠቁምም የሩዋንዳ እግርኳስ ማህበር ውድድሩን ለማራዘም መገደዱን ለቢቢሲ ስፖርት አስታውቋል፡፡ የውድድሩ ሲራዘም ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡

የእግርኳስ ማህበሩ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ቦኒ ሙጋቤ ውድድሩ ለማራዘም የተገደዱት አስፈላጊውን የፋይናንስ ድጋፍ ከሴካፋ አለማግኘታቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ “ባለፈው ወር ከሴካፋ በተስማማነው መሰረት ውድድሩን ለማስተናገድ የሚስፈልገው በጀት አስካሁን አልደረሰንም፡፡ በተደጋጋሚ ከሴላፋ ጋር መልዕክቶችን ለመለዋወጥ ጥረት አድርገን ነበር፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አዘጋጇ ሩዋንዳን ጨምሮ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ቡሩንዲ እና ጅቡቲ በውድድሩ እንደሚካፈሉ የተረጋገጠበት ውድድር መቼ እንደሚጀመር አሁን ላይ የታወቀ ነገር የለም። በ2016 መስከረም ወር ላይ ዩጋንዳ ውድድሩን ካስተናገደች በኃላ የሴቶች ቻምፒየንሺፑ መዘጋጀት ከሚገባው ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ለውድድሩ እንዲረዳው ባሳለፍነው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ ዝግጅት መጀመሩ ይታወቃል፡፡