የሉሲዎቹ ዝግጅት ለተወሰኑ ቀናት ሊቋረጥ ይችላል

በሩዋንዳ አስተናጋጅነት በዚህ ሳምንት እንደሚጀመር ተጠብቆ ሴካፋ ለሩዋንዳ መስጠት የሚገባውን ገንዘብ ባለመስጠቱ አዘጋጇ ሩዋንዳ ጥያቄዋ እስካልተሟላ ድረስ ውድድሩን ለመጀመር እንደምትቸገር በመግለጿ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል። 

የውድድሩ መራዘም ቢታወቅም የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዛሬም ዝግጅታቸውን በተሟላ ሁኔታ በአዲስ አበባ ስታድየም እንደቀጠሉ ለመመልከት ችለናል። ሆኖም ኢትዮጵያ የሴካፋ ዋንጫ በቶሎ የማይካሄድ ከሆነ ሌላ ጨዋታ ለማድረግ 25 ቀናት በኋላ ከአልጄርያ ጋር የሚደረገውን የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ትጠብቃለች። ይህን ተከትሎም የጨዋታ ቀናቶች እስኪቃረቡ ድረስ ብሔራዊ ቡድኑ ሊበተን እንደሚችል ተነግሯል።


ኢትዮጵያ ከአልጄርያ ጋር እስከምታደርገው ጨዋታ ድረስ በመሀል ቡድኑ ለተወሰኑ ቀናት የሚበተን ከሆነ በጨዋታው እንደሚቸገሩ በመግለፅ በሆቴል ተሰባስበው መቆየት እንዳለባቸው በብሔራዊ ቡድኑ የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ዘንድ እየተነሳ ይገኛል። በአንፃሩ ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ የበጀት እጥረት ያለበት በመሆኑ ከዚህ በኋላ ለ25 ቀናት ብሔራዊ ቡድኑን ለማቆየት እንደሚቸገር እና የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በመቋረጡ ወደ ውድድር እንዲገባ እንደሚፈልግ እየተገለፀ ይገኛል። በሉሲዎቹ እና በፌዴሬሽኑ መካከል ያለው ሀሳብ በቀጣይ በምን መልኩ ይታረቃል የሚለውን በሂደት የሚታይ ይሆናል።