የአሰልጣኞች ገጽ – ወርቁ ደርገባ [ክፍል 1]

የአሰልጣኞቻችን የእግርኳስ አስተሳሰብ ፣ የስልጠና ሀሳብ ፣ የስራ ህይወት እና የውጤታማነት መንገድ ዙርያ ትኩረት በሚያደርገው ” የአሰልጣኞች ገጽ ” አምዳችን የዛሬ ተረኛ አድርገን ያቀረብናቸው አንጋፋው አሰልጣኝ ወርቁ ደርገባን ነው።


በአዲስ አበባ ከተማ ሰሜን ሆቴል አካባቢ የተወለዱት አሰልጣኝ ወርቁ ደርገባ በተጫዋችነት ዘመናቸው በ1970ዎቹ መጀመርያ ለቴዎድሮስ እና አብዮት ፍሬ እንዲሁም ከፍተኛ እና የዞን ቡድኖች መጫወት ችለዋል፡፡ በጊዜ ወደ አሰልጣኝነት ስራ በመግባትም በ1974 በጀርመን የ8 ወራት አሰልጣኝነት ኮርስ በመውሰድ አንበሳ ቡድንን በ1975 በማሰልጠን ጀምረዋል፡፡ ከዛም በኢትዮጵያ መድን፣ ባንኮች፣ ቡና ገበያ ፣ ድሬዳዋ ኮተን፣ አአ ፖሊስ፣ ኮምቦልቻ ጨጨ፣ ወንጂ ስኳር፣ ሐረር ቢራ፣ አየር ኃይል፣ ደደቢት፣ ባህርዳር ከተማ ፣ አል ዋሒዳ ሰንዓ፣ አአ ከተማ፣ ናሽናል ሴሜንት እንዲሁም በመጨረሻ ወሎ ኮምቦልቻን እስከ 2009 ድረስ አሰልጥነዋል፡፡ በቴክኒክ ደይሬክተርነት እና አማካሪነት ደግሞ ዳሽን ቢራ፣ ኬ ኤንድ ኤፍ እንዲሁም በኢትዮ-አሜሪካ ወጣቶች አካዳሚ ሰርተዋል፡፡

በ1980ዎቹ መጀመርያ በድጋሚ ወደ ጀርመን በማቅናት ከላይፕዚሽ ዩኒቨርሲቲ ለ2 አመት ተኩል ቆይተው በድህረ ምረቃ የሚሰጡ ኮርሶችን የወሰዱት አሰልጣኝ ወርቁ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ከ1983-1985 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ (የመንግስቱ ወርቁ ረዳት) ፣ በ1989 የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ፣ በ1996 የኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ (የስዩም አባተ ረዳት) በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከስፖርቱ በተጓዳኝም በአዲስ አበባ ንግድ ስራ ኮሌጅ (ኮሜርስ) በአካውንቲንግ የመጀመርያ ዲግሪ ያገኙ ሲሆን በባንክ አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅትም መደበኛ የባንክ ስራን ደርበው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡


የዛሬው የክፍል አንድ መሰናዷችን የአሰልጣኝ ወርቁ ጥቅል የአሰልጣኝነት ስራ ላይ ትኩረት አድርጓል። ለቃለ ምልልሱ እንዲያመችም ከ”አንቱ” ይልቅ “አንተ” በሚለው ተጠቅመናል።


በሚልኪያስ አበራ እና አብርሀም ገብረማርያም


በፕሪምየር ሊጉ በሚገኙ ክለቦች በአሰልጣኝነት ሙያ እያየንህ አይደለም፡፡ ምክንያቱ ምን ይሆን?

★ ‘የላይኛው አካባቢ በሞኖፖል ተይዟል!’ ብል ይቀለኛል፡፡ እንዲያው ዝም ብለህ የምትገባበት ቦታ አይደለም፤ ብዙ እጆች አሉበት፡፡ እኔ ደግሞ ሽሚያ ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡ ከስልጠናው እስካልወጣውና ስራው እስካለ ድረስ ታዳጊዎች ፕሮጀክትም ውስጥ ቢሆን ገብቼ እሰራለሁ፡፡ እኔ እንዲያውም ‘በእግርኳስ ስልጠና ውስጥ ወደፊት የምሰራው ለአንድና ለሁለት አመት ብቻ ይሆናል፡፡’ ብዬ ነው የማምነው፡፡ ከዚያ ውጪ በቴክኒካል ዳይሬክተርነት አልያም በታዳጊ ስልጠና ዘርፍ አለበዚያም በእግርኳስ ስነልቦና ላይ አጫጭር የሆኑ ኮርሶችን ለመስጠት አስባለሁ፡፡ ሲውዘርላንድ በሄድኩ ጊዜ “ሁኔታዎች ከፈቀዱ የፈለግከውን ትምህርት እናስተምርሀለን፡፡” ስላሉኝ እድሉን ለመጠቀምና በ Football Psychology  ዙሪያ ለመማር ጥያቄ ለማቅረብ አቅጃለሁ፡፡ ለክለቦችም ይሁን ለብሄራዊ ቡድኑ በሙያው ለማገልገል ሐሳቡ አለኝ፤ በስልጠናው አለም ረዘም ላለ ጊዜ ሰርቻለሁ፤ ስለተጫዋቾች ባህሪም በደንብ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ የእግርኳስ ስነልቦና ባለሙያ ሆኜ መስራት እፈልጋለሁ፡፡ በተለያዩ ኮርሶች ስለ Sport Psychology ተምረን ግንዛቤው አለን፡፡ ይህኛው ግን ብዙም ያላወቅነውና ያልሰራንበት ነው፡፡ በአውሮፓ በሰፊው እየተሰራበት ይገኛል፡፡ ‘ወደዚህ ሙያ ከአንድና ከሁለት አመት በኋላ እሄዳለሁ፡፡’ የሚል እቅድ አለኝ፡፡


ስላንተ ከሰማነው አሉታዊ ነገሮች አንዱ ” ወርቁ ተጫዋቾች አልያም የክለብ አመራሮች ሲያድሙበት ጥሎ ይሄዳል፡፡” የሚል ነው፡፡ ጫናን አለመጋፈጥ ወይስ ግፊትን መሸሽ ነው?

★ስራውን ጥሎ መሄድ ላይ አስተያየቱ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ተጫዋቾች እኔ ላይ አድመውብኝ አያውቁም፡፡ ተጫዋቾችንና ቡድንን በማስተዳደር (Team Management) ረገድ ጥሩ ነኝ፡፡ እኔ ከተጫዋቾቼ የምጠብቀውን ነገር እንዲያሟሉልኝ ከፈለግኩ እነሱን በጥሩ ሁኔታ መያዝ ይኖርብኛል፡፡ በግል ከእያንዳንዱ ተጫዋች ጋር የመነጋገርና ውይይት የማድረግ ልምድ አለኝ፡፡ አንድ ተጫዋች ሚስጥሩን ሲያወጋኝ ማንም ሰው በአካባቢዬ እንዲኖር ስለማላደርግ ምክትሌ እንኳ ጎኔ አይቀመጥም፡፡ የተጫዋቾቹ ግላዊ ህይወት የራሳቸው በመሆኑ በዚያ መንገድ እቀርባቸዋለሁ፡፡ ተጫዋቾቼን የምፈልጋቸው ለስራ እስከ ሆነ ድረስ እንዲማሩና በግልጽነት ስለቤተሰቦቻቸው እንዳውቅ እፈልጋለሁ፡፡ ስለ ሚስቶቻቸው፣ የፍቅር አጋሮቻቸው፣ እናቶቻቸውና አባቶቻቸው እንዲሁም በህይወት ስለሌሉት የቅርብ ሰዎቻቸው ለማወቅም እጠይቃለሁ፡፡ ለምሳሌ የተጫዋቹ አባት ሞተው ከሆነ ሀዘንህን ትገልጽና በቀሪው ጊዚያት እንደ አባት ሆኜ ለመገኘት እጥራለሁ፡፡ ስለዚህ እኔ ላይ ተጫዋቾች አድመውብኝ አያውቁም፡፡ የክለብ አመራሮችን ግን በጣልቃ ገብነት ጉዳይ ‘አይሆንም!’ እላቸዋለሁ፡፡ ተጫዋቾቼን ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ እንዲቀርቡብኝ አለመፈለጌን አይወዱትም፡፡ በዚህ ምክንያት የሆነ ነገር ሊጀምሩብኝ ይፈልጉና የምጠይቃቸውን ነገሮች ወደ አለማሟላት ይሄዳሉ፡፡ እኔም ችግሩን በደብዳቤ አሳውቄ ምላሽ እጠብቃለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ‘ቻው!’ ይሄ አይነቱ አካሄድ መለመድም አለበት፡፡ ሁሉን ነገር ዝም ብሎ <አሜን> በማለት መቀበል አይኖርብንም፡፡ አሁን አሁን የተጀመረው ነገር ይሄ ነው፡፡ “ብር ተቀብያለው፤ ክፍያዬን ወስጃለሁና እንደፈለገ ይውጣብኝ፡፡” አይሆንም፡፡ ከአመራሮች ጋር የምለያየው በዚህ መንስኤ እንጂ በውጤት ደረጃ ቡድን አውርጅ አላውቅም፤ በታማኝነትና ንጽህና ጉዳይ ጥያቄ ተነስቶብኝ አያውቅም፡፡ ተጫዋቾቼን አከብራለሁ፤ ከስርዓት ውጪ ሲሆኑ ግን ለብቻቸው እየጠራሁ እመክራቸዋለሁ፡፡


መንግስቱ ወርቁና ስዩም አባተን ከመሳሰሉ አንጋፋ አሰልጣኞች ስር ሰርተሀል፡፡ ሌሎች ትልልቅ የእግርኳስ ስብዕና ካላቸው ባለሙያዎች ጋር የመስራት አጋጣሚውስ ነበረህ?

★በእነዚህ ትልልቅ ባለሙያዎች ስር ነው የሰራሁት፡፡ ከመንግስቱ ወርቁ ጋር በዋናው ብሄራዊ ቡድን ከ1983-1985፣ ከስዩም አባተ ጋር ደግሞ በኦሎምፒክ ቡድኑ በ1996 ሰርቻለሁ፡፡ ባሰለጠንኳቸው ሁሉም ክለቦች በዋና አሰልጣኝነት ነው የቆየሁት፡፡


እንዲህ እንዳሁኑ ክለቦችን በማታሰለጥንባቸው ወቅቶች ምን አይነት ነገሮችን ትከውናለህ?

★ ብዙ ጊዜዬን በቤት ስለማሳልፍ ከውጪ አገር የማገኛቸውን እግርኳሳዊ የሆኑና ሌሎች ብዙ አይነት መጽሀፎችን አነባለሁ፡፡ማንበብ ትምህርትና እውቀት ስለሆነ የግድ ያስፈልጋል፡፡ መጽሀፍ እኮ አይሰለችም፡፡


ከማስተር ቴክኒሻን ሐጎስ ደስታ ጋር በነበረህ ጥሩ ቅርበት በአሰልጣኝነት ሙያ ዘርፍ ብዙ ውይይቶችን ታደርጉ ነበር፡፡እንዲያውም ከዩኒቨርሲቲ የሚመጡ የስልጠና ባለሙያዎችን “እነሱ አስተማሪዎች እንጂ አሰልጣኞች አይደሉም!” የሚል አቋም እንደነበራችሁ ሁሉ ይነገራል፡፡ የስፖርት ሳይንስ ምሩቃን አሰልጣኞች “አሰልጣኞች” የማይሆኑበት ምክንያት ምንድን ነው?

★ እንግዲህ የእኔ አቋም በስፖርት ሳይንስ ዘርፍ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡ ባለሙያዎችን “አሰልጣኞች አይደሉም!” የሚል ሳይሆን “በአሰልጣኞች ቡድን (Coaching Staff) ውስጥ የራሳቸው ድርሻ የሚኖራቸው አባላት ናቸው፡፡” የሚል ነው፡፡ በአሰልጣኞች ቡድን ውስጥ ብዙ ስራ አለ፡፡ ሆኖም በእኛ አገር እግርኳስ የአሰልጣኙ አጋዥ ባልደረቦች ከሶስት አይበልጡም፤ ዋናው አሰልጣኝ፣ ምክትል አሰልጣኙ እና የበረኞች አሰልጣኝ ናቸው፡፡ ነገርግን ስራው ሌሎች ባለሙያዎችን ይፈልጋል፡፡ በአሰልጣኞች ቡድን ውስጥ የስነ ልቦና፣ የምግብ  ክትትልና ቁጥጥር አድራጊ፣ የህክምናና ተያያዥ ጉዳዮች ባለሙያን ማካተት የግድ ነው፡፡ እነዚህን የተማሩ ባለሙያዎች በተገቢው ቦታ ብትመድባቸውና አብረሃቸው ብትሰራ የምታገኘው ጥቅም የጎላ ነው፡፡ አሰልጣኙ በሚፈልገው ነገር ላይ ሀላፊነት እየሰጠው ቢያሰራው የተሻለ አትራፊ ይሆናል፡፡ ስራው የግድ ሜዳ ላይ ገብቶ ማሰልጠኑ አይደለም፡፡ አልፎ አልፎ ከምሰማው ነገር መጠነኛ ቅር የመሰኘት ስሜት ሳይኖር አይቀርም መሰለኝ   “እንዲህ አድርጉ እንባላለን!” ብለው በሬዲዮ ትችት ሲያቀርቡ አስተውላለሁ፡፡ አሰልጣኝነቱ ላይ ሳይሆን የአሰልጣኙን ስራ የሚያግዙ የራሳቸው ኃላፊነት የሚኖራቸው ሙያተኞች የመሆን እድሉ አላቸው፡፡


“እውቀታቸው አሰልጣኙን በተለያዩ ዘርፎች ሊያግዝ የሚያስችል በመሆኑና ለዚያ የሚያበቃ ትምህርት ስላላቸው <አጋዥ> መሆን ይችላሉ፡፡” ማለትህ ይሆን?

★ በትክክል! ባላቸው የትምህርት ዝግጅትና እውቀት መሰረት በአሰልጣኞች ቡድን አባልነት የዋና አሰልጣኙ አጋዥ በመሆን ማገልገል ይችላሉ፡፡ ምንም የሚያጣላ ነገር የለም፤ ምንም! ቀድሞም ቢሆን ለምን እንደማንስማማ አይገባኝም ነበር፡፡


በእናንተ ቀደምት የአሰልጣኝነት ጊዜ “የአሰልጣኝነት መንበሩን” እየተረከቡ ትቸገሩ ነበር? ስራችሁና ውሳኔዎቻችሁ ላይ ጣልቃ የመግባት አዝማሚያ አሳይተውስ ይሆን አለመስማማቱ የተፈጠረው?

★ በእርግጥ አሰልጣኝ የሆኑ ሰዎች ነበሩ፡፡ አሰልጣኝነትን ሞክረውና ሰርተው ሲያቅታቸው ትተውታል፡፡ ያኔ <የአሰልጣኞች ቡድን አባል> ሆኖ የመስራት ሀሳብና አዎንታዊ አመለካከቱ አልነበረም፡፡ “በዚህ መንገድ አብረን እንስራ፡፡” የመባባሉ ነገርም አይታይም፡፡ ነገሩ ወደ ጥላቻና በራስ ያለመተማመን ሁኔታ ያመራና “አሰልጣኞች እንዳንሰራ አደረጉን!” የሚል እምነትን ፈጠረ፡፡ ለምን? የስልጠና ሙያ እኮ ብዙ የስራ ዘርፎች አሉት፡፡ በዘመናዊ እግርኳስ እነ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ከ20-30 ባለሙያ አይደለም እንዴ ይዘው የሚሰሩት? ይህ ሁሉ አባል የማይበቃቸው ጊዜም አለ፡፡ በማይሆን አመለካከት እና እይታ ዝም ብለን ነው የምንጣላው እንጂ ምሁራኑ መስራት የሚችሉበት ቦታ ክፍትና በርካታ ነው፡፡ ለምሳሌ በብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ የአሰልጣኞች ቡድን አባላቱ ቁጥር በጣም ትንሽ ነው፡፡ ለቦታው አምስትና ስድስት የሚደርሱ የተመረጡ ባለሙያዎችን በማስቀመጥ ሰዎቹ የራሳቸውን ስራ እየሰሩ ለቡድን ስራ ደግሞ ውይይትና ምክክር በማድረግ ሐላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ ይህም የአሰልጣኙን ስራ በእጅጉ ያቀለዋል፡፡ ለአንድ ዋና አሰልጣኝ ምክትልና የበረኛ አሰልጣኝ ሰጥተህ ማስራት ከባድ ነው፡፡ እንዲያውም አሁን አሁን ሁለት ሶስት እየተደረገ ነው፡፡ በፊት እኛ ብቻችንን አንድ ሆነን ነበር የምንሰራው፤ በረኛውን፣ ተከላካይ ክፍሉን፣ አማካዩንና የአጥቂ መስመሩን ዋናው አሰልጣኝ ነበር የሚያሰለጥነው፡፡ የማይቻል፣ ከባድና የውሸት ስራ ስለሚሆን በዚህ መንገድ የተሟላ ስራን አንሰራም፡፡ በህብረት ተጋግዘህ ስትሰራ ግን በጋራ ፕሮግራሞችን ታወጣለህ፤ ስለሚቀነሱና ስለሚጨመሩ የልምምድ አይነቶች ውይይት ታደርጋለህ፤ ውጤታማም ትሆናለህ፡፡ በብሄራዊ ቡድን የተጫዋቾች ምርጫ ጉዳይ ላይ አንድ የተለመደ ነገር አለ፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ምክትሉን ራሱ እንዲመርጥ ይደረጋል፡፡ እኔ ይህን አሰራር የማልቀበልበት ምክንያት አለኝ፡፡ “ተግባብቶ ለመስራት” በሚለው ታሳቢ መደረጉ ጥሩ ቢሆንም በእግርኳሳችን ደረጃ ዋናውን አሰልጣኝ በተለያዩ መስፈርቶች እንደሚመርጥ ሁሉ ምክትሉንና ሌሎቹን የአሰልጣኝ ቡድን አባላትም  እንዲሁ በተወሰኑ መመዘኛዎች አወዳድሮ ብቁና ጠንካራ ሰው ማቅረብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በውጪዎቹ አሰልጣኞች መካከል ያለው መግባባት ከፍተኛ ነው፡፡ እኛም በዚያ ደረጃ እስከምንደርስ ድረስ በእንዲህ አይነቱ ስልት ብንጓዝ የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ግዴታነቱ መለመድ አለበት፡፡ “አልወደውም፤ አላውቀውም፤…” አይሰራም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ እና ከዋናው ጋር ምናልባት የተመጣጠነ የስራ ልምድ ያለው ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ሐላፊነት የሚሰማውና ብቁ የሆነ ሰው በመምረጥ ለስራው መመደብ አስፈላጊ ነው፡፡ ሌላው እዚሁ መነሳት ያለበትን የእግርኳስ ችግራችንን ልጥቀስላችሁ፦ ዋናው አሰልጣኝ ምክትሉን ሲሾም በምንም መስፈርት ሳይሆን በትውውቅ ላይ በተመሰረተ ሒደት ላይ ነው የሚመረኮዘው፡፡ ያ ችግር አለው፤ ሰውየው የሚፈለገውን ስራ ይሰራል? አይሰራም! ለምን እንደዚያ ይሆናል? ስለዚህ ፌዴሬሽኑ ለብሄራዊ ቡድኑ የአሰልጣኞች ብዛትን ከወሰነ በኋላ  ሊሰሩ የሚችሉ ሰዎችን በመስፈርት መምረጥ ይኖርበታል፡፡ ከዚያ ዋናው አሰልጣኝ የረዳቶቹን ሐላፊነት ይወስንና በችሎታቸው ልክ ይመድባቸዋል፡፡ ሁሉም ታምኖባቸው በውድድር የተመረጡ በመሆናቸው የተሻለ ስራ ይሰራሉ፡፡


“ወርቁ ተጫዋቾች የከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ላይ እንዲተጉ ያደርግና ይመክር ነበር፡፡ እኛም ተጫዋቾች እያለን የዩኒቨርስቲ ትምህርታችን ላይ ትኩረት እንድናደርግ ፈቃድ በመስጠት አግዞናል፡፡” ያሉን የቀድሞ ተጫዋቾችህ አሉ፡፡

★ እግርኳስ በራሱ ትምህርት ከመሆኑ በተጨማሪ   በእውቀት የምታካሂደው ጨዋታ ነው፡፡ እኛ አገር በተለይ በተጫዋቾች ዘንድ ሁላችንም የምናውቀው በጉልህ የሚታይ ችግር አለ፡፡ በክፍል ውስጥ ሰሌዳ ላይ የሚሰጡ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎችን የሚመለከቱ ትምህርቶችን ስንሰጥ የሚያንቀላፉ፣ የሚሰለቻቸውና ደስተኛ የማይሆኑ ተጫዋቾች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ትምህርታዊ አመጣጣቸው ጥሩ ስላልሆነ ለመረዳት ሲቸገሩም እናስተውላለን፡፡ ስለዚህ አሰልጣኙ የሚሰጠውንም በአግባቡ እንዲቀበል መሰረታዊ ትምህርት ያስፈልጋል፡፡ በየትኛውም የስራ መስክ እውቀት የግድ ነው፡፡ እኔ ባንክና መድን እያለው የሁለቱንም ተቋማት የሚያገናኝ የኢንደስትሪው ኮሌጅ ነበር፡፡ ተጫዋቾች በግዴታ ት/ቤቱን እንዲቀላቀሉ እናደርጋቸዋለን፡፡ እዚያ ተምረው በአሁኑ ወቅት ትልልቅ የባንክ አስተዳዳሪዎች የሆኑ አሉ፡፡ አቶ ደጀኔን ታውቁት ይሆናል፤ በሊቤሮ ቦታ ይጫወት ነበር፤ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የህብረት ባንክ ስራ አስኪያጅ ነው፡፡ ሌሎችም እየተጫወቱና እየተማሩ የተመረቁ ብዙ አሉ፡፡ የተጫዋቹ መማር በበርካታ ነገሮች ሊጠቅመው ይችላል፡፡ ትምህርት ለተጫዋቾቹ ቀጣይ የህይወት መስመርራቸው ማስተካከያ ከመሆኑም በላይ መሰረታዊ የቀለም እውቀት ሲኖራቸው የአሰልጣኞች ስራም ይበልጡን እየቀለለ ይሄዳል፡፡ በደብረዘይቱ የታዳጊዎች ፕሮጀክት ላይ ስንሰራ አንድ ሰልጣኝ በትምህርት ድክመት ሲያሳይ ከልምምድ እናግደዋለን፡፡ ከቤተሰቦቹ ጋር ተስማምተን ባደረግነው ውል መሰረት ውጤቱ መሻሻል እስኪያሳይ ድረስ አንመልሰውም፡፡ ይህንን በአስገዳጅነት የምናደርግበት ዋነኛ ምክንያትም ታዳጊዎቹ ስልጠናውንና ትምህርታቸውን አብረው የማስኬድ አእምሮአዊ ዝግጅት እንዲኖራቸው በማሰብ ነው፡፡ በትምህርታቸው በሚያስመዘግቡት ውጤትም ማበረታቻ ሽልማት እንዲሰጣቸው እናደርግ ነበር፡፡ አልተሳካም እንጂ ወደ አሜሪካ ሁሉ ሊጓዙ እድል ያገኙ ልጆችም ነበሩ፡፡ ስለዚህ አዋቂዎቹ ተጫዋቾችንም ቢሆን እንዲማሩ ጫና ማሳደር አለብን፡፡ ኳስን መጫወት ብቻ እኮ ማወቅ ማለት አይደለም፡፡ ተጫዋቾቻችንን መሀይም አድርገን ማስቀረት የለብንም፡፡ ከጥቅሙ አንጻር በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ  ለተጫዋቾች ይሰጥ የነበረው ነጻ የትምህርት እድል መቅረቱን ስሰማም በጣም አዝኛለሁ፡፡



በበርካታ ክለቦች ቆይታ አድርገሀል፡፡ በ1980ዎቹ አጋማሽ በቡና የመጀመሪያህ ቆይታ ማጥቃት ላይ የተመሰረተ የአጨዋወት ስልት ተከታይ ነበርክ፡፡ ሁሌም ማጥቃትን የመጀመሪያ ምርጫህ የምታደርግ አሰልጣኝ ነህ ወይስ እንደምትረከባቸው ክለቦች የሚወሰን አቀራረብን ትመርጣለህ?

★ የእኔ እምነት “አንድ አሰልጣኝ በመጀመሪያ ማጥቃትን መምረጥ አለበት፡፡” የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ሁለተኛውን የመከላከል ስራ በዚያው የማጥቃት ሒደት ትጨርሰዋለህ፡፡ አንተ ከሄድክበት ማን ይመጣብሃል? ጥሩ እግርኳስ ስለምወድ አሁንም ድረስ ፍላጎቴ ይህ ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ጥሩ እግርኳስ ለመጫወት ጠንካራ መሆን አለብህ፡፡ በውጪው እግርኳስ ከነ ማንችስተር ሲቲና ሊቨርፑል የምናየውም በተከታታይነት አንተው ሜዳ ላይ የሚሆኑት ጥሩ የአካል ብቃት ደረጃ ስላላቸው ነው፡፡ መከላከልን ስታስቀድም ከተጋጣሚህ እየሸሸህ ነው ማለት ይሆናል፡፡ እንደ መርህ መውሰድ የሚገባን <የባላጋራ ቡድን አንተ ያለህበት እንዳይመጣ ጦርህን ይዘህ እዚያው ሂድ፡፡> የሚል ሲሆን እስካሁንም፣ ነገና ከነገ ወዲያም የምጠቀምበት ነው፡፡ በርግጥ ተጫዋቾች አንተ እንደምትፈልገው አይሆኑልህም፤ የምትፈልገውንም አታገኝም፡፡ በተለይ ለማጥቃት አጨዋወት እንደምትፈልገው የሚሆኑ ልጆች አይኖሩህም፡፡ በገባሁባቸው ክለቦች የገጠመኝ ችግር ተጫዋቾችን የምታመጣቸው በቀረበልህ ገንዘብ ልክ ነው፡፡ ስለዚህ የአቅም ጉዳይ ይወስንሀል፡፡ ያው በተቻለ መጠን በምትፈልገው አጨዋወት እንዲሰለጥኑ ታስተምራለህ፡፡


በ1980ዎቹ መጨረሻ በቡና ሁለተኛ ቆይታህን ለአጭር ጊዜ ካደረግክ በኋላ የባንክን B ቡድን ወደ ማሰልጠኑ ነው የሄድከው፡፡

★ በ1988 ለሶስት ወር ቡናን ካሰለጠንኩ በኋላ ባንኮች ጠሩኝና ” የተስፋ ቡድኑን ያዝልን፡፡” አሉኝ፤ እዚያው ቀጠልኩ፡፡


ከዚያ በቀደሙት ጊዜያት ትልቅ ስም አትርፈህና በተለያዩ ክለቦች በዋና አሰልጣኝነት የማሰልጠን ልምዱ ኖሮህ እንዴት ወደ ባንኮች B ቡድን “ወርደህ” መስራቱን መረጥክ?

★ በመጀመሪያ መታወቅ ያለበት ባንክ የቆየሁበት ክለብ ነው፡፡ ጀርመን ሄጄ በምማርበት ወቅት ያስተማረኝ፣ እኔ እየተማርኩም በባንክ የቋሚ ሰራተኛነት ደመወዜን እየከፈለኝ ቆይቷል፡፡ ከጀርመን ስመለስ “የአሰልጥንልን” ጥያቄ አቀረቡ፡፡ በጊዜው አቶ መንግስቱ ወርቁ የታዳጊ ቡድኖች በየክለቡ እንዲዋቀሩ ያደርግ ነበር፡፡ ይሄ በባንክ የሚገኘው የተስፋ ቡድንም በዚያ ጊዜ የተመሰረተ ነበር፡፡ እኔ በታዳጊና ወጣት ፕሮጀክቶች ላይ መስራት እወዳለሁ፡፡ በጀርመን ስማር በተመረጠ ርዕስ ላይ አንድ  “ፕሮፖዛል ሰርተህ አቅርብና እኛ እንረዳሀለን፡፡” ይሉሀል፡፡  እኔ በታዳጊዎች ፕሮጀክት ላይ አቀረብኩ፡፡ ፕሮፖዛሉ ላይ የማስተካከያ እርማቶች ሲሰጡ አንድ አመት የሚጠጋ ጊዜ ወሰደ፡፡ በ1999 ዓ.ም በደብረዘይት በሁለት የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተከፈተ Ethio America Youth Soccer Academy የሚባል ማሰልጠኛ ማዕከል ነበር፡፡ ሪኮ ጂላርዲና ኢንጅነር በኃይሉ የማዕከሉ መስራቾች ነበሩ፡፡ እኔም የማሰልጠኛው ሐላፊ ሆኜ ተሹሜ ለሁለት አመት ሰርቻለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ በወጣቶች ላይ የመስራት ፍላጎቱ ስላለኝ ከመጀመሪያው ጀምሮ እድሉን ሳገኝ እጠቀምበታለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ እስከዛሬ ያልገለጽኩትን ነገር ላንሳ፦ በ2001 ዓ.ም ይመስለኛል፤  ስለ ሰራሁት Youth Training Proposal ሰምቶ አቶ አብነት ገ/መስቀል  አስጠሩኝና የፕሮፖዛሉን ኮፒ ይዤ ሸራተን ሄድኩኝ፡፡ አቶ አብነትም “ልየውና እኛ ጋር ትሰራለህ፡፡” ሲሉኝ እኔም ‘በጣም ደስ ይለኛል፤ የገንዘብ አቅሙ ስለሌለኝ እኔ በእውቀቴ እናንተ ደግሞ በሚያስፈልገው ወጪ በዚህ የYouth Training ዙሪያ እንሰራለን፡፡”  አልኳቸው፡፡ አቶ አብነትም “እኔ ጊዜ ስለማይኖረኝ እንዲያስታውሱኝ!” ብሎ የተወሰኑ ሰዎችን አስተዋወቀኝ፡፡ለስራ አስኪያጆች፣ ለሚመለከታቸውና ለሚቀርቡት ሰዎች ሁሌ እናገራለሁ፡፡ ይቅርታና ምንም ነገር ሳይኖር ይኸው ሁኔታው ዘጠኝ አመት ሞላውና በዚያው ቀረ፡፡ በመጨረሻም ሰዎች የቦርዱ ጸሀፊ አቶ ነዋይ ጋር ላኩኝና ሄጄ ሳናግራቸው “አልረሳነውም፤ ነገር ግን አንዳንድ ጉዳዮች ይዘውን ነው፡፡” የሚል ጥሩ መልስ ሰጠኝ፡፡ እንደገና ከሰባት አመት በፊት ወደ የመን ስሄድ ‘ ከዚህ ቀደም እኔ ራሴ ሳልጠይቅ እናንተ ነበር የጠየቃችሁኝ፤ አካዳሚ ልትከፍቱ ስለሆነ በዚያ ማሰልጠኛ ማዕከል ውስጥ የመስራት እድሉን ባገኝ ለመስራት ዝግጁ ነኝ፡፡’ አልኳቸው፡፡ ከዚያ በፊትም ኢትዮጵያ ቡና በታዳጊዎች ላይ ለመስራት ክፍለከተሞችን እየሰበሰበ ነበር፡፡ ጸሀፊው አቶ ተስፋዬ ካህሳይ ጠርቶኝ “በቡና ስም ክፍለከተሞችን አደራጅተን አካዳሚ እንከፍታለን፡፡” ብሎኝ ከሱ ጋርም ሀሳቡን ጀምረን ነበር፤ ሆኖም እሱ ተነሳና ጉዳዩም በዚያው ቀረ፡፡ ብዙ ጊዜ በታዳጊዎች ስራ ለመስራት ይከብዳል፤ በክለብ ግን ያን ያህል አይደለም፡፡ በቅርቡ በመድን ስሰራ ፌዴሬሽኑ መልቀቂያ አልሰጠኝም ነበር፡፡ መልቀቂያ ባለማግኘቴ ምክንያት በመድን ከስድስት ወር በላይ መስራት አልቻልኩም፡፡ ፌዴሬሽኑ ምንም ነገር ሳይኖርብኝ የመልቀቂያውን ነገር “እምቢ” አለኝ፡፡ሆኖም ግን ድሬደዋ ላይ ከአቶ አበበ ጋር በተፈጠረ <ኬዝ> ከፌዴሬሽኑ ጠርተውኝ “በቃ ምንም ነገር የለም- ጨርሰሀል፤ ስለዚህ መልቀቂያህ ይሰጥሀል፡፡” ብለውኝ ብጠብቅ ብጠብቅ አይሰጡኝም፡፡ ከዚያም ከመድን አቶ ጌታሁን “መልቀቂያ ማምጣት ስላልቻልክ…፡፡” ብሎ ደብዳቤ ሲጽፍብኝ ስራውን ተውኩት፡፡ ወዲያውኑ በቡና ገበያና ከመንግስቱ ጋር ደግሞ በብሄራዊ ቡድን የማውቀው አሰግድ ተስፋዬ( ነፍሱን ይማረውና!) መጥቶ ” ወርቁ ቴክኒካል እገዛ የሚያደርግልኝ ሰው የለምና እርዳኝ!” አለኝ፡፡ እኔም በቀጥታ ገባሁና ወደ ስድስት ወር ሰራሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ኮምቦልቻ ሄድኩ፡፡ በማንኛውም ሰዓት ከታዳጊዎች ጋር የመስራት ፍቅሩ ስላለኝ ነገም ይሁን ከነገ ወዲያ በፍላጎት እሰራለሁ፡፡ ለወደፊቱም ቢሆን ከአንድ ሰው ጋር በመሆን አካዳሚ ከፍቼ የምሰራበት ሁኔታ ይኖራል የሚል እምነት አለኝ፡፡


በተለያዩ ክለቦች በአንጋፋነት ስትሰራ የቆየህ አሰልጣኝ በመሆንህ በታዳጊዎች ዙሪያ ማሰልጠንን መርጠህ ስትሰራ እንደ “መውረድ”  ተደርጎ ስለሚታሰብ ያንን ግልጽ እንድታደርግልን ነው፡፡

★ አይደለም! ለእኔ እንዲያውም ምንም የማታፍርበት፣ ትልቁና የሚያረካው በወጣቶች ላይ የሚሰራው ስራ ነው፡፡


ብዙውን ጊዜ አሰልጣኞች ባልሰሩት ቡድን ላይ ሲቀጠሩ ይታያል፡፡ በተለመደው አካሄድ ተጫዋቾች ከተገዙ በኋላ ነው አሰልጣኞች ቡድን እንዲረከቡ የሚደረገው፡፡ አንተ ግን ለሚፈልጉህ ክለቦች የሰጠኸው የተለየ መልስ ነበር፡፡ በዚህ ላይ የምትለን ነገር ካለ…

★ ያልቆየህበትን ቡድን ስትይዝ ታበላሸዋለህ፡፡ በአሰልጣኝነት ቅጥር ስትፈጽም የምትይዘውን ቡድን በደንብ ማወቅህን፣ ተጫዋቾቹ አንተ ለምትፈልገው አጨዋወት አመቺ ስለመሆናቸውና በአመራሮቹ ላይ ስለምታሳድረው እምነት እርግጠኛ ልትሆንባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ቡድኑን ካወቅከው እንደ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሆነህም ልትሰራ ትችላለህ፡፡ በምንም ነገር ላይ ያንተ ተሳትፎ ሳይኖርና መረጃ ሳትይዝ ቡድን ስትቀበል ራስህን፣ ቡድንህን፣ ተጫዋቾችን እና እግርኳሱን ትጎዳለህ፡፡ ባልጀመርከው ስራም Risk መውሰድ ይከብዳል፡፡ በወንጂ እያለሁ ከአዳማ ከተማም እንዲሁ ተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦልኝ ነበር፡፡ “ቦታ እንሰጥሀለን፡፡” ሁሉ ብለውኝ አልተቀበልኩም፡፡ በዚያን ጊዜ የአዳማ ቡድን ከደጋፊዎቹ ጋር የነበረው ግንኙነት ጥሩ ስላልነበረ ‘የምትሰጡኝ ቦታ መቀበሪያዬ እንዲሆን አልፈልግም፡፡’ የሚል መልስ ሰጥቼ ከሀላፊዎቹ ጋር መጠነኛ አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር፡፡ የነበረውን ሁኔታ በደንብ አውቀው ስለነበር እንደማባበያ የበረበልኝን ስጦታ ‘ይቅርብኝ!’ አልኩ፡፡


አንድን ቡድን ለማሰልጠን ከመስማማትህ በፊት “አውቀዋለሁ፡፡” ለማለት እንደ መስፈርት የምታስቀምጣቸው ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

★ በመጀመሪያው የቅድመ ውድድር ዘመን የዝግጅት ስራዎችን እንደማሰራ እርግጠኛ መሆን ይኖርብኛል፡፡ ባሉት ተጫዋቾና ቡድን የምፈልገውን ለመስራት እንደምችል ማወቅ፣ የተጫዋቾቹን ችሎታን መለየትና ለእያንዳንዳቸው በተናጠል  የሚያስፈልጋቸውን ስነ ልቦናዊ፣ ታክቲካዊና ሌሎችንም ዝግጅቶች ማሳወቅ  ይጠበቅብኛል፡፡  ከ<ፕሪ ሲዝን> ዝግጅት በኋላ ቡድን ስትይዝ ምን ልትሰራ እንደምትችል እንኳ አታውቀውም፡፡ በእርግጥ የሁለተኛው ዙር የውድድር ዘመን ከመጀመሩ በፊት መጠነኛ የእረፍትና ዝግጅት ጊዜ ቢኖርም በቂ ግን አይደለም፡፡ ከውድድሮች መጀመር በኋላ ቡድን ስትይዝ የምትሰራው ጎዶሎ ስራ ነው፡፡ በርግጥ በዚህ የተለመደ አሰራር አሰልጣኞች ብዙ ጊዜ ቡድን ሲረከቡ እናያለን፡፡ አጠቃላዩን የቡድን መረጃ ሳልይዝ ሳሰለጥን  ለሁሉም ተጫዋቾች አንድ አይነት ነገር ልሰጥ እገደዳለሁ፡፡ ትልቁ መስፈርት መሆን ያለበትም ተጫዋቾችን በደንብ ለማወቅ የሚያስችል ጊዜ እንዳለህ መረዳቱ ላይ ነው፡፡ እንደ ቡድንም ሆነ በተናጠል ደካማና ጠንካራ ጎኖችን መለየት መቻል አለብህ፡፡ Individual እና Special ልምምዶችን አዘጋጅተህ ስራህን ትቀጥላለህ፡፡ ካልሆነ ግን የጅምላ ስራ ይሆንና አደጋውና ተጠያቂነቱ አንተ ላይ ይመጣል፡፡


በ1985 ዓ.ም የጀመረው የቡና የመጀመሪያ ቆይታህ ጥሩ ሲሆን የ1988ቱና ሁለተኛው ጊዜህ ግን የሶስት ወር ብቻ ነበር፡፡ “ውለታ በሎቹ አመራሮች” በሚል እንደ ምክንያት ያነሳኸው ችግር ነበር፡፡ የምን ውለታ ነው የተበላብህ?

★ በቡና የመጀመሪያዎቹ ሁለት አመታት ስራዬ አሪፍ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሻምፒዮናም ሁለተኛ ሆነናል፡፡ ቡና በአፍሪካ ሻምፒዮና መወዳደር የቻለውም ለመጀመሪያ ጊዜ ከአልሙራድ ጋር ባደረግነው ጨዋታ ነው፡፡ ይህን ያልኩትም ያን ውጤት እንደ <ክሬዲት> ሊያዩልኝ ስላልቻሉ ነው፡፡ እስካሁንም ሲያነሱት አልሰማም፤ በጣም አዝናለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ስላሉት ድሎች ብቻ ነው የሚነሳው፡፡ በከፍተኛ የገንዘብ እጦት ምክንያት ቁርስ የማይበሉበትና ሻይ የማይጠጡበት ጊዜ እያለም ሁለቱን አመት በደንብ ነበር የሰራነው፡፡ የዛን ዘመን ተጫዋቾች ብትጠይቁ ይነግሯችኋል፡፡ ልጆቹን እያባበልንና በጋራ <Get Together> ነገሮችን እየፈጠርን ስለነበረው ችግር እንዳያስቡ እናደርግ ነበር፡፡ አመቱን ሙሉ በሁለት ኳስ ብቻ ተጠቀምን የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ደረስን፡፡  ጥያቄዎች ስናነሳ “ገንዘብ የለም፡፡” እየተባልን ቆይተን በመጨረሻም ማግኘት የሚገባንን ነገር በሙሉ ሳናገኝ ቀረንና ተበተንን፡፡ እኔም የቡናን ሁለት አመት ኮንትራት ጨርሼ በ1987 ዓ.ም ወደ ድሬደዋ ሄድኩ፡፡ በ1988 “አደረጃጀቱ በአዲስ መልክ ሊዋቀር ነው፡፡” ተባለና ተጫዋቾች ሲሰባሰቡ እኔ ከድሬዳዋ መጣሁ፡፡ የክለቡ ሰዎችም “እባክህ እርዳን፤ ከበፊቱ የተሻለ የፋይናንስ ሁኔታ አለን፡፡” ሲሉኝ ‘ቡድኔ ነው፤ ልጆቹንም አውቃቸዋለሁ፤ በዚህ ላይ በቂ የዝግጅት ጊዜ አለን፡፡ ስለዚህ ለሁለት-ሶስት ወር ሳልፈርም እረዳችኋለሁ፡፡’ አልኳቸው፡፡ ያ የሶስት ወር ጊዜ ማለቂያው ሲቃረብ ያለመፈረሜን አደነቅሁ፡፡ ምክንያቱም ደጋፊዎች የሚፈልጓቸውን የራሳቸው ተጫዋቾች አምጥተው ሳይሰለፉ ሲቀሩ የኩርፊያ አዝማሚያዎች መምጣት ጀመሩና ሁኔታዎች እየተበላሹ ሄዱ፡፡ ‘ አዝናለሁ፤ የያዝነው “የክለብ ቡድን” ሳይሆን “የደጋፊዎች ቡድን” ነው፤ አመሰግናለሁ፡፡” ብዬ አበቃሁ፡፡


በ2002 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ቡና የ” አሰልጥንልን! ” ጥያቄ ቀርቦልህ አልተቀበልክም ነበር፡፡ ምክንያትህ ጥያቄው በደጋፊዎች የመጣ ስለነበረ ነው?

★አይደለም! አይደለም! ‘በቡና ገበያ ቆይታዬ የማላፍርበትን ስራ ሰርቼ ከደጋፊዎች ትልቅ ክብርን አግኝቻለሁ፡፡ ያንን ክብር መልሼ ማበላሸት አልፈልግም፡፡ ስለዚህ “የአሰልጥንልን” ጥያቄውን አልቀበልም፡፡ እንደ ቴክኒክ አማካሪነት ወይም ዳይሬክተርነት ባለ ሌላ ሙያ ግን ለመስራት ፈቃደኛ ነኝ፡፡’ ብዬ ለመጡት ሰዎች ምላሽ ሰጥቻለሁ፡፡