ስሞሃ ከግብፅ ዋንጫ ፍፃሜ ራሱን አግልሏል

አሌክሳንደሪያ ከተማው ክለብ ስሞሃ ከግብፅ ዋንጫ ፍፃሜ ራሱን ማግለሉን የቡድኑ ፕሬዝደንት መሃመድ ፋራግ አምር በግል የፌስቡክ ገፃቸው አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ኡመድ ኡኩሪ የሚጫወትበት ስሞሃ ባሳለፍነው ማክሰኞ አልአስዮትን በመለያ ምት 4-3 በማሸነፍ ነበር ከዛማሌክ ጋር በመጪው ማክሰኞ ለሚደረገው ፍፃሜ ማለፍ ችሎ የነበረው፡፡ የክለቡ ፕሬዝደንት እና ቱጃር አምር የግብፅ እግርኳስ ማህበር ለፍፃሜው ጨዋታ ከውጪ ሃገር አርቢትሮችን እንዲያመጣ ያነሱት ጥያቄ ተቀባይነትን አላገኘም፡፡ የእግርኳስ ማህበሩም የፍፃሜው ጨዋታን ግብፃዊያን ዳኞች እንደሚመሩ ያስታወቀ ሲሆን ውሳኔው ሰማያዊ ሞገዶቹን አላስደሰተም። የእግርኳስ ማህበሩ በቅርቡ በታላቁ የካይሮ ደርቢ አል አሃሊ እና ዛማሌክ ያደረጉትን ጨዋታ ከረጅም ዓመታት በኃላ ግብፃዊያን አርቢትሮች መምራታቸው ይታወቃል፡፡

በግብፅ እግርኳስ የክለብ ፕሬዝደንቶች የሚወስኗቸው አንዳንድ ውሳኔዎች አግራሞትን ሲያጭሩ ይስተዋላል፡፡ ከዚህ ቀደም የዛማሌክ አወዛጋቢ ፕሬዝደነት ሞርታዳ መንሱር ክለባቸው ከአፍሪካ የክለቦች ውድድር ባልተጠበቀ ሁኔታ በወላይታ ድቻ ሲሰናበት የግብፅ የስፖርት ሚኔስቴርን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን በተደጋጋሚም የሊግ ውድድርን እንደሚያቋርጡ ሲዝቱ ይስተዋላል፡፡

ስሞሃ በውሳኔው ከፀና አስከፊ የውድድር ዓመትን ያሳለፈው የአምስት ግዜው የአፍሪካ ቻምፒዮን ዛማሌክ የግብፅ ዋንጫ የሚያሸንፍ ሲሆን በ2018/19 የካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ላይም ተሳታፊ የሚሆን እድልን በእጁ ይጨብጣል፡፡ ኡመድ በፍፃሜው ላይ የተጫወተ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ የመሆን እድልም በውሳኔው ላይ የስሞሃ ቦርድ መለሳለስን ካላሳየ የሚበላሽ ይሆናል፡፡፡