አሰልጣኝ ስዩም አባተ ለህክምና ወደ ታይላንድ ያመራሉ

አንጋፋው አሰልጣኝ ስዩም አባተ ባደረባቸው ህመም ምክንያት ለወራት የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ አሰልጣኝ ስዩም ህመማቸው አገርሽቶ ዳግም ወደ ሆስፒታል ከገቡ በኃላ መሻሻሎችን ቢያሳዩም ለተሻለ ህክምና በመጪው ሰኞ ወደ ባንኮክ ታይላንድ እንዲሚያመሩ ሰምተናል፡፡

አሰልጣኝ ስዩምን ለማሳከም እየተንቀሳቀሰ ያለው ኮሚቴ አባል የሆኑት አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ለህክምና ወጪ የሚውል ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ማሰባሰብ ባይቻልም ባንኮክ ህክምናውን እየተከታተሉ ቀሪውን እርዳታ ለማሰባሰብ መታቀዱን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ “የህክምናውን ሙሉ ወጪ አሁን ላይ ኮሚቴው ባሰባሰበው እርዳታ ነው የሚሸፈነው፡፡ የደርሶ መልስ ትኬቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው የተባበረን፡፡ አብረውት እንግዲ ወንድሙ አቶ ሰለሞን፣ ልጁ እዝራ እና ከፍተኛ ትብብር ሲያደርግልን የነበረው አቶ ኤፍሬም ወደ ባንኮክ ይሄዳሉ፡፡” ብለዋል፡፡

አሰልጣኝ አስራት ሲቀጥሉ “አሁን ጥሩ ሁኔታ ላይ ያለው፡፡ ባንኮክ ለምርመራ የተላከው በቂ ስላልሆነ ወደ ስፍራው ማቅናት አለበት በሚል ነው ይህ ጉዞ የተዘጋጀው፡፡ ምርመራው እራሱ ወደ አምስት ቀን ይፈጃል፡፡ የተወሰኑ የሰውነቱ ህዋሳት ወደ 150 ሚሊየን የሚሆኑት እንዲቀየሩ እና በአዲስ መተካት አለበት የሚል ነገር ተነግሮናል፡፡ ህክምናው ጠንከር ያለ እንደሆነ እናውቃለን፡፡” ብለዋል።

ኮሚቴው ለህክምናው ከሚያስፈልገው 1 ሚሊየን ብር ውስጥ ከ 600ሺ ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን የተናገሩት አሰልጣኝ አስራት ቀሪ ወጪውን አንጋፋው አሰልጣኝ ስዩም በህክምና ላይ እያሉ ለመሰብሰብ እንደታቀደ ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም እኚህን የኢትዮጵያ እግርኳስ ባለውለታ ለመርዳት እጃቸውን የዘረጉት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን፣ የኢትዮጵያ ቡና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የአሰልጣኙ አድናቂዎች እና ወዳጆች እንዲሁም ሌሎች በርከት ያሉ ግለሰቦችን አመስግነዋል፡፡

አሰልጣኝ ስዩም ወደ መልካም ጤንነት እንዲመለሱ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በፀሎት እንዲያግዛቸውም አሰልጣኝ አስራት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡