​ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | የግንቦት 6 ተስተካካይ ጨዋታዎች

ለሁለት ሳምንታት ተቋርጦ የቆየው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የአፍሪካ መድረክ ተሳትፏ ምክንያት 18ኛው እና 20ኛው ሳምንት ላይ በተስተካካይነት በተያዙት ጨዋታዎች የሚጀምር ሲሆን 17ኛው ሳምንት ላይ 45 ደቂቃዎች እየቀሩት በደጋፊዎች ረብሻ ምክንያት የተቋረጠው የወልዋሎ ዓ.ዩ እና መቐለ ከተማ ጨዋታም እንደሚቀጠል ይጠበቃል። እኛም በዛሬዎቹ ጨዋታዎች ዙሪያ የሚከተሉትን ነጥቦች አንስተናል።

አዳማ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

የ18ኛ ሳምንት መርሀ ግብር የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በወላይታ ድቻ አስገራሚ የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጉዞ የያንጋው የመጀመሪያ ጨዋታ ምክንያት በይደር የተያዘ ነበር። ጨዋታው ከተላለፈ በኃላ ሜዳው ላይ ካደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ስድስት ነጥቦችን የሰበሰበው አዳማ በ22ኛ ሳምንት ከጎንደር ይዞ የተመለሰውን አንድ ነጥብ ጨምሮ በ33 ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። እንደወትሮው ሁሉ ወጥነት የጎደለው የዋንጫ ፉክክር እያደረገ የሚገኘው አዳማ የሌሎች ተፎካካሪዎቹ ውጤት እንዳለ ሆኖ ከዛሬው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ካሳካ ወደ ሁለተኛነት ከፍ የሚልበት ዕድል ይኖራል። ከሊጉ መቋረጥ አስቀድሞ መቐለ ላይ የ 2-0 ሽንፈት የገጠመው ወላይታ ድቻ በበኩሉ በደረጃ ሰንጠረዡ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ ራሱን በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለማግኘት የግድ ያሉትን ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች አሸንፎ ነጥቡን ወደ 36 ከፍ ማድረግ ይኖርበታል። ይህ እንዲሆን ደግሞ ዛሬ ሜዳው ላይ የማይደፈረው አዳማ ከተማን የመርታት ግዴታ አለበት። 

በባለሜዳው አዳማ በኩል የጉዳት ዜና ባይኖርም በሀዋሳው ጨዋታ ላይ ቀይ ካርድ የተመለከተው ሲሳይ ቶሊን በቅጣት ምክንያት አያሰልፍም። ከዚህ በተጨማሪ ቡልቻ ሹራ እና ሱራፌል ዳኛቸው ከጉዳት መልስ ክለቡን እንደሚያገለግሉ ተሰምቷል። እንደተጋጣሚው ሁሉ የጉዳት ዜና የሌለበት ወላይታ ድቻ በዲሲፕሊን ምክንያት ለአንድ አመት የቀጣው ወንደሰን ገረመው ከቡድኑ ውጪ ሲሆን ፀጋዬ ብርሀኑ እና እርቂሁን ተስፋዬ ደግሞ ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኃሃ ወደ ሜዳ ተመልሰዋል፡፡

– ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ ሰባት ጊዜ ያህል የተገናኙ ሲሆን በአቻ ውጤት የተለያዩበት አጋጣሚ የለም። በዚህም መሰረት አዳማ ከተማ አራቱን በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ወላይታ ድቻ ቀሪዎቹን ሶስት  ጨዋታዎች አሸንፏል። በግብ ማስቆጠሩም በኩል እንዲሁ ተመጣጣኝ ቁጥር ያላቸው ሲሆን አዳማ 9 እንዲሁም ድቻ 8 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል። 

– አዳማ ላይ የተጋናኙባውቸን ሶስት ጨዋታዎች በሙሉ ባለሜዳው በአሸናፊነት ሲያጠናቅቅ  ወላይታ ድቻ አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ማስቆጠር የቻለው አንድ ግብ ብቻ ነው። 

– አዳማ ከተማ አሁንም ሜዳው ላይ የሚደፍረው አልተገኘም። ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ከአምስት ጨዋታዎች ከሰበሰባቸው ሰባት ነጥቦች ስድስቱን ያሳካው አዳማ ላይ ነበር።

– ወላይታ ድቻ በሁለተኛው ዙር ከሜዳው ውጪ የሚወጣበት ሁለተኛው ጨዋታ ሲሆን 22ኛው ሳምንት ላይ ወደ መቐለ ተጉዞ 2-0 ተሸንፏል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫው ከወረደ በኃላ ካራ ብራዛቪልን በመልሱ ጨዋታ ለመግጠም ወደ ኬንጎ ባቀናበት ወቅት ነበር ይህ ጨዋታ ሳይካሄድ የቀረው። ሁለቱ ክለቦች ላለመውረድ እና ለሻምፒዮንነት በሚደረጉት ፍልሚያዎች ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንደመሆናቸውም የጨዋታው ተጠባቂነት ከፍ ያለ ነው። በተስተካካይ ጨዋታዎቹ ውጤት ከመሪው ጋር በነጥብ የመስተካከል ዕድል ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደካማውን የውድድር አመቱን አስተካክሎ በቀሪዎቹ ጨዋታዎች በሊጉ አናት ላይ ለመቀመጥ የዘሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ወሳኝ ይሆንለታል። ቡድኑ አርባምንጭ ላይ ከደረሰበት ከባድ ሽንፈት በኃላም ወደ ድል ለመመለስ እንደሚፋለም ይጠበቃል። በወልዲያ ላይ ባሳካው ድል ከወራጅ ቀጠናው ለወጣው ኢትዮ ኤሌክትሪክም የጨዋታው ትርጉም ከፍ ያለ ነው። አሁንም ውሉ ባለየለት የታችኛው ሰንጠረዥ ፉክክር ውስጥ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከብቸኛው ተስተካካይ ጨዋታው ሙሉ ነጥብ ማሳካት ከቻለ በሊጉ ለመቆየት በሚያደርገው ትግል ውስጥ መጠነኛ መሻሻልን ሊያገኝ ይችላል።

ሁለቱ ተጋጣሚዎች ብዙም የጉዳት ዜና የለባቸውም። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ሁሉም ተጨዋቾች ለጨዋታው ብቁ ሲሆኑ ሴራሊዮናዊው የመልሀ ተከላካይ ሲሴ ሀሰን ግን በ 5 ቢጫ ካርድ ምክንያት የማይሰለፍ ይሆናል። ሊጉ በተቋረጠበት ወቅት ጉዳት የነበረባቸው ተጨዋቾቹ የተመለሱለት ቅድስ ጊዮርጊስ ስላዲን ሰይድን ብቻ የሚያጣ ሲሆን የአበባው ቡታቆ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።

– ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዘንድሮ ከመዲናዋ ክለቦች ጋር በተገናኘባቸው አጋጣሚዎች ያለው ሪከርድ በእጅጉ ደካማ ነው። ከስስድስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ሽንፈት ካስተናገደባቸው አራት ጨዋታዎች በሶስቱ በተመሳሳይ የ3-1 ውጤት ነበር የተሸነፈው። ከነዚህ ሽንፈቶች አንዱ የደረሰበት ደግሞ በዛሬ ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። 

– ከአዲስ አበባ ክለቦች ጋር ሲገናኝ ከተጋጣሚው በጣም የተሻለ ውጤት ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአምስት ጨዋታዎች ያሳካው 9 ነጥቦችን ቢሆንም በ2 ድል እና በ3 የአቻ ውጤቶች ሽንፈት አልባ ጊዜ ነበረው። ሆኖም አንድ ነጥብ ይዞ የወጣባቸው ሶስቱም ጨዋታዎች ያለግብ የተጠናቀቁ ነበሩ። 

ሶስተኛው የዛሬ ጨዋታ ሽረ ላይ እንዲደረግ የተወሰነው የወልዋሎ ዓ.ዩ እና መቐለ ከተማ ሁለተኛ አጋማሽ ነው።  በ32ኛው ደቂቃ አሳሪ አልመሀዲ ባስቆጠረው ጎል በወልዋሎ1-0 መሪነት በተቋረጠው የመጋቢት 21 ጨዋታ ላይ የነበሩት የተጋጣሚዎቹ ተሰላፊዎች ወደ ሜዳ የሚገቡበት የዚህ ጨዋታ ውጤት ለሁለቱም እጅግ ወሳኝ ይሆናል። መቐለ ከተማ ከመሪው ጋር ያለውን ልዩነት ወደ አንድ ዝቅ ለማድረግ እንዲሁም ወልዋሎ ዓ.ዩ ነጥቡን 23 በማድረስ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በቀራቸው 45 ደቂቃ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።