ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ ደረጃውን ወደ 2ኛ ከፍ ያደረገበትን ድል አሳክቷል

የ20ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሀ ግብር የነበረው እና በተስተካካይነት ተይዞ ዛሬ 10፡00 ላይ የተደረገው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።  

ፕሪምየር ሊጉ ከመቋረጡ በፊት በ22ኛው ሳምንት ከተደረጉት ጨዋታዎች ጋር ሲትያይ ሁለቱ ቡድኖች በድምሩ የሰባት ተጨዋቾች ለውጥ አድርገዋል። ከዚህ ውስጥ ሶስቱን የሚወስደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲሆን ወልዲያን 1-0 ካሸነፈው ስብስቡ ውስጥ አምስት ቢጫ ካርድ ያለበት ሲሴይ ሀሰንን በግርማ በቀለ ፣ ጥላሁን ወልዴን ከቅጣት በተመለሰው በኃይሉ ተሻገር እንዲሁም የፊት አጥቂው ኃይሌ እሸቱን በዲዲዬ ለብሪ ተክቷል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ አስቻለው ታመነ ከጉዳት መልስ በሳላዲን ባርጌቾ ምትክ ጨዋታውን ሲጀምር አማካይ ክፍል ላይ ሙሉአለም መስፍን እና ጋዲሳ መብራቴ በናትናኤል ዘለቀ እና አዳነ ግርማ እንዲሁም ከፊት አሜ መሀመድ በአዲስ ፈራሚው ሪቻርድ አፒያ ተተክቷል።

በቅዱስ ጊዮርጊሶች ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያ ሙከራን ያስተናገደው ግን በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ነበር። ሙከራው 3ኛው ደቂቃ ላይ የግራ መስመር ተከላካዩ ስንታየው ሰለሞን ወደ ውስጥ ያሻማው ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሄዶ በሮበርት ኦዱንካራ ሲወጣ የታየ ነበር። ሆኖም ከሶስት ደቂቃዎች ቆይታ በኃላ አብዱልከሪም ኒኪማ በጫና ውስጥ ሆኖ ከቀኝ መስመር ያሻማው ኳስ በአዲስ ፈራሚው ሪቻርድ አፒያ አማካይነት ወደ ግብነት ተቀይሮ ፈረሰኞቹ ቀዳሚ ሆነዋል። ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የበላይነት መውሰድ የቻሉት ኤሌክትሪኮች በቅብብል ወደ ተጋጣሚያቸው ሜዳ ክልል በመግባት በግራ መስመር አድልተው ማጥቃት ቢጀምሩም ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችን መፍጠር ግን ተስኗቸው ታይተዋል። ይልቁኑም ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመልሶ ማጥቃት ይፈጥሯቸው የነበሩ ዕድሎች ለግብ የቀረቡ ነበሩ። በተለይም 13ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ አሰፋ ከአዳነ ግርማ ተቀብሎ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ የሞከረው እና ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ ተጠቃሽ ነው። 19ኛው ደቂቃ ላይም ጊዮርጊሶች በግራ መስመር በመሀሪ መና ከከፈቱ መልሶ ማጥቃት በሀይሉ አሰፋ የተወለትን ኳስ ተጠቅሞ አፒያ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ቢቃረብም ግብጠባቂው ሱሊማን አቡ ቀድሞ በመገኘት አድኖበታል። ሆኖም በዚህ ቅፅበት ሁለቱ ተጨዋቾች በመጋጨታቸው የከፋ ጉዳት የገጠመው አቡ እስከ 28ኛው ደቂቃ ድረስ የህክምና ዕርዳታ ቢደረግለትም ወደ ጨዋታው መመለስ ባለመቻሉ በዮሐንስ በዛብህ ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል።

ከቅያሪው በኃላ ጨዋታው ሲቀጥል ኤሌክትሪኮች አሁንም የተሻለ የበላይነትን ይዘው ታይተዋል። የቡድኑን ቁልፍ ተጨዋች አልሀሰን ካሉሻን ወደ ታፈሰ ተስፋዬ በማቅረብ ጫና ለመፍጠር ቢሞክሩም ከኃላ የሚመሰረተውን ጨዋታ ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል የሚያደርስ ተጨዋች አጥተው ለመልሶ መጠቃት ሲጋለጡ ይስተዋል ነበር። በዚህም 37ኛው ደቂቃ ላይ መሀሪ መና ከሳጥን ውስጥ በቀጥታ አክርሮ የሞከረው እና ተከላካዮች ተደርበው ያወጡበት እንዲሁም በሀይሉ አሰፋ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ የላከው ኳስ ሳጥን ውስጥ ጥሩ አቋቋም ላይ ለነበሩት ሶስት የጊዮርጊስ ተጨዋቾች ሳይደርስ የቀረበት ሂደት የኤሌክትሪክን ክፍተት እና የቅዱስ ጊዮርጊስን ፈጣን የማጥቃት ሽግግር የሚያሳዩ ሂደቶች ነበሩ። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተለይም የኢትዮ ኤሌክትሪክ የመስመር ተከላካዮች በማጥቃት ሂደት ላይ ክፍት የሚተውትን ቦታ በመጠቀም ተደጋጋሚ ጥቃት ሲሰነዝሩ ታይተዋል። 38ኛው ደቂቃ ላይ ስንታየሁ ሰለሞን በጥላሁን ወልዴ ተቀይሮ የወጣበትም ምንክንያት ከዚህ ጋር የተገናኘ ይመስላል። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በዚህ አጋማሽ የፈጠሩት ብቸኛ ዕድል 49ኛው ደቂቃ ላይ ዲዲዬ ለብሪ ከሳጥን ውስጥ ሞክሮት ወደ ውጪ የወጣው ኳስ ሲሆን ቡድኖቹ ወደ ዕረፍት ከማምራታቸው በፊት ናትናኤል ዘለቀ እና ምንተስኖት አዳነ ከበሀይሉ አሰፋ የተሻማን የማዕዘን ምት ወደ ግብ ለመቀየር ተቃርበው ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ በርካታ ሙከራዎች እና ጎሎችም ጭምር የታዩበት ነበር። ሆኖም የመጀመሪያው ትኩረት የሳበው ክስተት የሪቻርድ አፒያ 48ኛው ደቂቃ ላይ ተጎድቶ መውጣት ነበር። 51ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ዲዲዬ ለብሪ በቀኝ መስመር ሰብሮ በመግባት ረጅም ርቀት ኳስ ይዞ በመሄድ ከሮበርት ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችሏል። 60ኛው ደቂቃ ላይም  ታፈሰ ተስፋዬ ከተከላካዮች ጀርባ ካሉሻ አልሀሰን ያሳለፈለትን ኳስ በተመሳሳይ መልኩ ይዞ ወደ ሳጥን ውስጥ ከገባ በኃላ አገባ ተብሎ ሲጠበቅ ሮበርት አድኖበታል። በዚሁ ደቂቃ ላይ ከአቡ እና አፒያ በኃላ ግርማ በቀለ በጉዳት ተቀይሮ የወጣ ሶስተኛው ተጨዋች ሆኗል። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ጫናቸውን በቀጠሉባቸው ቀጣዮቹ ደቂቃዎች 64ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተጣለን ኳስ በሀይሉ ተሻገር በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ሰጥቶት ታፈሰ ከሳጥን ውጪ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። 63ኛው ደቂቃ ላይ አፒያ ቀይሮ የገባው አማራ ማሌ ከሳጥን ውስጥ አክርሮ የመታው እና ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣው ኳስ ግን ቅዱስ ጊዮርጊስን በድጋሜ መሪ ለማድረግ በእጅጉ የቀረበ ሙከራ ነበር።

68ኛው ደቂቃ ላይ አሜ መሀመድ አዳነ ግርማን ቀይሮ ከገባ በኃላ አቡበከር ሳኒን ወደ አማካይ ክፍል በማምጣት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከኃላ ኳስ እንዳይመሰርቱ በከፍተኛ ፍጥነት ጫና መፍጠር የቻሉት ጊዮርጊሶች ለቀጣዮቹ አስር ደቂቃዎች እጅግ አደገኛ ሆነው ታይተዋል። በነዚህ ደቂቃዎች ካገኙት ብልጫም 70ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም መሀመድ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ አክርሮ ሞክሮት ዮሀንስ በዛበት ያወጣበት ድንቅ ሙከራ ተጠቃሽ ነበር። በዛው ቅፅበት የተገኘው የማዕዘን ምት ወደ ግብ ከተሞከረ በኃላ ዮሀንስ ሲያወጣው በአቅራቢያው ይገኝ የነበረው አማራ ማሌ ወደ ግብነት ቀይሮታል። በቀጣይ ታደለ መንገሻን በበሀይሉ አሰፋ ቀይረው ያስገቡት ጊዮርጊሶች አልፎ አልፎ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ከመጠቀም ባለፈ ጨዋታውን ወደ ጀመሩበት አኳኃን በመመለስ ፍጥነቱን ቀንሰው ለመጨረስ ያደረጉት ጥረት ፍሪያማ ሆኗል።  

ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው ዲዲዬ ለብሪ በነበረበት የቀኝ መስመር አድልተው ጫና መፍጠራቸውን ሲቀጥሉ 88ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ አቅጣጫ ከተከፈተ ጥቃት ለብሪ ወደ ውስጥ ለመግባት ሲሞክር አቡበከር ሳኒ ጥፋት ሰርቶበት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ሆኖም ካሉሻ አልሀሰን ከማዕዘን ምት ከተሻገር ኳስ በግንባሩ ሞክሮ ሮበርት ካወጣበት አጋጣሚ በቀር ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የቁጥር ብልጫውን መጠቀም ሳይችሉ ጨዋታው ተጠናቋል። በውጤቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 36 አድርሶ ወደ 2ኛነት ከፍ ሲል ኢትዮ ኤሌክትሪክ በነበረበት 13ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል። 

የአሰልጣኞች አሰተያየት

ም/አሰልጣኝ ቦጋለ ዘውዴ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ 

ሶስት ነጥብ አሳክተን ደረጃችንን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት አድርገናል። ሆኖም በጥቃቅን ስህተቶች ዋጋ ከፈለን ነጥብ ልናጣ ችለናል። እድለኞች አልነበርንም። በጉዳት ምክንያት ያደረግናቸው አስገዳጅ ቅያሪዎችም ዋጋ አስከፍለውናል። የአጨራረስ ችግራችንን ለመፍታት ልምምዶችን ስንሰራ ነበር። በተለይ የታፈሰ ኳስ ቢገባ ኖሮ ነገሮች ይቀየሩ ነበር። በቀሩን ሰባት ጨዋታዎች ተሻሽለን ለመምጣት እንሞክራለን። 

አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ – ቅዱስ ጊዮርጊስ 

እንደማስበው ጨዋታው ሶስት የተለያዩ ክፍሎች ነበሩት። የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ነበር። ከአንድ በላይ ጎል ለማስቆጠር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ፈጥረናል። ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር እና ግብ ሲቆጠርብን ደግሞ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች በራስ መተማመናችን ወርዶ ነበር። በጉዳት እና በቀይ ካርድ ተጨዋቾችን ብናጣም በድጋሜ መሪ ከሆንን በኃላ ግን ጨዋታውን መቆጣጠር ችለናል። ማሸነፍ መቻላችንም በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ለሚኖረን ቦታ እና ለራስ መተማመናችንም ጥሩ ነው።