ሉሲዎቹ ሐሙስ ወደ ሩዋንዳ የሚያደርጉት ጉዞ ተሰረዘ 

እንደ አባል ሀገራቱ ሁሉ ውድድሮችን የመምራት ደካማ አቅም እንዳለው በተደጋጋሚ እያሳየን የሚገኘው ሴካፋ ለአዘጋጇ ሀገር ሩዋንዳ መክፈል የሚገባውን ክፍያ አስቀድሞ ባለማጠናቀቁ የተነሳ በወጣለት መርሀግብር መሰረት ሳይካሄድ ቀርቷል። በቅርቡ ሴካፋ ከአዘጋጇ ሀገር ጋር የተፈጠረውን አለመግባበት ፈትቶ ከግንቦት 10 – 20 ውድድሩ እንደሚጀመር ለተሳታፊ ሀገራት ያሳወቀ በመሆኑ ሉሲዎቹ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ስፍራው ሊያቀኑ አንድ ቀን ሲቀረው እስካሁን ሴካፋ ማረጋገጫ አለመስጠቱን ተከትሎ የውድድሩ አለመካሄድ እርግጥ እየሆነ መጥቷል ።

ከሚያዚያ 23 ጀምሮ ዝግጅታቸውን በአሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ እየተመሩ ያደረጉት ሉሲዎቹ 20 ተጨዋቾችን በመያዝ ሐሙስ ወደ ሩዋንዳ ያቀናሉ ተብሎ በሚጠበቅበት ሰዓት ሴካፋ ምንም አይነት ማረጋገጫ ባለመስጠቱ ጉዟቸው መሰረዙን ማረጋገጥ ችለናል። ሉሲዎቹ ከሩዋንዳ የሴካፋ ዋንጫ በተጓዳኝ ለአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ የማጣርያ ጨዋታ ከአልጄርያ ጋር የሚደረገው ጨዋታ የ15 ቀናት እድሜ መቅረቱን ተከትሎ እስካሁን  ከፌዴሬሽኑ ምንም እንኳን ማረጋገጫ ባናገኝም በዛው በሆቴል በመቆየት ዝግጅታቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ ተብሎ ይገመታል።

ምንም አይነት የተጨዋች ለውጥ ባለማድረግ በ23 ተጨዋቾች አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ልምምዳቸውን እየሰሩ የሚገኙት ሉሲዎቹ አጥቂዋ ሎዛ አበራ ካጋጠማት መጠነኛ ጉዳት በስተቀር  ሁሉም ተጨዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛሉ። የአሰልጣኝ አባላት ባወጡት መርሀ ግብር መሰረትም በአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ቡድኑን ለማዋሀድ እንደተዘጋጁ ሰምተናል።

የሴቶች ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ዲቪዚዮን ከተቋረጠበት በመቀጠል ዛሬ ሲጀምር እስካሁን መጀመር ያልቻለው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዲቪዚዮን መቼ እንደሚጀመር አለመገለፁ የውድድሩን መንፈስ እንዳያቀዘቅዘው ተሰግቷል።