ኡመድ ቋሚ በነበረበት የግብፅ ዋንጫ ፍፃሜ ስሞሃ ተሸንፏል

በግብፅ ዋንጫ ፍፃሜ ስሞሃ በዛማሌክ በመለያ ምቶች ተሸንፎ በታሪኩ ለመጀመሪያ ግዜ የዋንጫ ባለቤት የመሆን እድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ የፊት መስመር ተሰላፊው ኡመድ ኡኩሪ በፍፃሜው ላይ የተጫወተው ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ መሆን ቢችልም ድሉን ግን ማጣጣም የቻለው የካይሮው ሃያል ዛማሌክ ነው፡፡

በቦርግ ኤል አረብ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ገና በአምስተኛው ደቂቃ ነበር ስሞሃ ቀዳሚ መሆን የቻለው፡፡ መሃመድ ሃምዲ ዛኪ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ሆሳም ሀሰን ሰማያዊ ሞገዶቹን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ያልተጠበቀ ግብ ያገኙት ስሞሃዎች በመልሶ ማጣቃት ለመጫወት ሲጥሩ ዛማሌኮች በይበልጥ ተጭነው ተጋጣሚያቸውን ሲያስጨንቁ አምሽተዋል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የዲ. ሪ. ኮንጎ አጥቂ የሆነው ካቦንጎ ካሶንጎ ኳስ እና መረብን ማገናኘቱ በፊት የስሞሃ ተከላካዮች ኳስን አውጥተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የዛማሌክ ብልጫ የቀጠለ ሲሆን የስሞሃ በመልሶ ማጥቃት በሚያገኛቸው እድሎች ላይ ደካማውን የዛማሌክ የተከላካይ ክፍል መፈተን አልቻለም፡፡ ኡመድ በፊትኛው የሜዳ ክፍል ተነጥሎ በረጅሙ የሚጣሉ ኳሶችን ለመጠቀም ያደረግ የነበረው ጥረት በዛማሌክ ተከላካዮች በቀላሉ ነበር ሲበላሽበት የሚታየው፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 20 ደቂቃ ሲቀረው ግብ አስቆጣሪው ሀሰን በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተሰናብቷል፡፡ በ80ኛው ደቂቃ አሰልጣኝ ሚሚ አብደራዛቅ ውጤቱን ለማስጠበቅ በማሰብ ተከላካዩን ኤል ሳኢድ ፋሪድን በኡመድ ቀይረው ወደ ሜዳ አስገብተዋል፡፡ ሆኖም በ85ኛው ደቂቃ ካሶንጎ ከቅጣት ምት የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት የአቻነቷን ግብ አስገኝቷል፡፡

በጭማሪው 30 ደቂቃ ዛማሌክ ይበልጠ ግብ የማስቆጠር እድል የነበረው ቢሆንም የተጠና የማይመስለው የማጥቃት ሽግግሩ ቡድኑ ግብ እንዳያስቆጥር አግዶታል፡፡ የስሞሃ ተከላካዮችም የሚፈጠሩ እድሎች ለማበላሸት ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው ወደ መለያ ምት አምርተዋል፡፡ በተሰጠው መለያ ምት ዛማሌክ 5-4 ማሸነፍ ችሏል፡፡ በ2018/19 የካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ተሳታፊ መሆኑንም ማረጋገጥ ችሏል፡፡

ስሞሃ በ2014 በዛማሌክ በተመሳሳይ ውድድር የተሸነፈ ሲሆን በፍፃሜ የተረታበት ጨዋታ ወደ ሁለት ከፍ ብሏል፡፡ በ2013 ሳላዲን ሰዒድ ይጫወትበት የነበረው ዋዲ ደግላ ለግብፅ ዋንጫ ፍፃሜ ደርሰው በዛማሌክ 3-0 ተረተው ዋንጫ ማጣታቸው የሚታወስ ነው፡፡ አሁን ላይ ኡመድ ቡድኑ የፍፃሜ ተፋላሚ ሆኖ ቢቀርብም ዋንጫው ሳያሸንፍ ቀርቷል፡፡ ሳላዲን በ2014 ከአል አህሊ ጋር የሱፐር ካፑን ያሸነፈ ሲሆን በግብፅ የክለቦች እግርኳስ ታሪክም ዋንጫ ያሸነፈ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡