በፊፋ የሃገራት ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ አንድ ደረጃ ወርዳለች

ፊፋ በየወሩ የሚወጣው የኮካ ኮላ የሃገራት ደረጃ ዛሬ ከሰዓታት በፊት ይፋ ተደርጓል፡፡

ከኢንተርናሽናል ጨዋታዎች የራቀችው ኢትዮጵያ ካለፈው ወር አንድ ደረጃ ቀንሳ 146ኛ ሆናለች፡፡ ባለፈው ወር 145ኛ የነበረችው ኢትዮጵያ በታህሳስ 2010 በሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ ከዩጋንዳ ጋር 1-1 ከተለያየች በኃላ ጨዋታ አድርጋ ቆይታለች፡፡ ኢትዮጵያ በወሩ ያገኘችው ነጥብ 188 ነው፡፡

ብሄራዊ ቡድን ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስራቸውን ከለቀቁ በኃላ ያለአሰልጣኝ አመቱን እያጋመሰ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ምርጫ እና ሌሎች ወቅታዊ ችግሮች ለብሄራዊ ቡድኖቻችን የሚሰጠው ትኩረት እጅግ በጣም እንዲቀንስ አድርጎታል፡፡

ከአፍሪካ የሃገራት ደረጃ በፊፋ ካሌንደር የወዳጅነት ጨዋታዎችን ሲያደርግ የማይስተዋለው ብሄራዊ ቡድኑ 42ተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል፡፡ ቱኒዚያ የአፍሪካ አንደኛነቷን ስታስጠብቅ ሴኔጋል፣ ዲ.ሪ. ኮንጎ፣ ሞሮኮ እና ግብፅ ይከተላሉ፡፡ የዓለምን ደረጃ ጀርመን እየመራች ትገኛለች፡፡