ተቋርጦ የቆየው የ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ተጀምሯል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ በዛሬው እለት በተደረጉ የ11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ለሁለት ሳምንታት ያህል ከተቋረጠበት ቀጥሎ ከሜዳቸው ውጪ የተጫወቱት ጭላሎ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ሲዳማ ቡና ሲያሸንፉ ቅዱስ ጊዮርጊስም ድል አስመዝግቧል።

ምድብ ሀ

05:00 ላይ በመከላከያ ሜዳ የተካሄደው የመከላከያ እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። በመጀመርያው አጋማሽ የተሻሉ የነበሩት ባለሜዳዎቹ መከላከያዎች በጨዋታው መጀመርያ ላይ ፍ/ቅ/ምት አግኝተው ዘሪሁን አብይ ቢመታውም የአዳማው ተስፈኛ ግብ ጠባቂ ሔኖክ ቃሲም በጥሩ ብቃት አድኖበታል ። ብዙም ሳይቆይ አጥቂው ዘላለም በየነ ከርቀት ጥሩ ጎል አስቆጥሮ መከላከያዎችን ቀዳሚ ማድረግ ቢችልም አዳማዎች ለእረፍት ከመውጣታቸው በፊት ከማዕዘን ምት ብሩክ ቦጋለ ባስቆጠረው ጎል አቻ መሆን ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽም እንደ መጀመርያው ሁሉ ባለሜዳዎቹ መከላከያዎች ብልጫ ወስደው የተጫወቱ ሲሆን የመስመር አጥቂያቸው ይታጀብ ገብረማርያም ለአጥቂዎቹ ዘላለም በየነ አና ዮሀንስ ደረጄ በተደጋጋሚ የጎል ዕድል ቢፈጥርላቸውም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተው ነጥብ ተጋርተው ሊወጡ ችለዋል። (በዳንኤል መስፍን)

በዚሁ ምድብ ረፋድ 5:00 ላይ ወደ መድን ሜዳ ተጉዞ ኢትዮጵያ መድንን የገጠመው ጭላሎ ፉድስ 1-0 አሸንፎ ሲመለስ ወደ ድሬዳዋ ያቀናው ኢትዮጵያ ቡና 08:00 ላይ ድሬዳዋ ከተማን ገጥሞ 2-0 በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል። በአካዳሚ ሜዳ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ከጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ያደረጉት ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል።

 ምድብ ለ

08:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ደደቢትን 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በበርካታ ተመልካች ታጅቦ ከፍተኛ የመሸናነፍ ፉክክር በታየበት ጨዋታ በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ ከፍተኛ ፍጥነት እና በርካታ የግብ ሙከራ የነበረበት ነበር። በ6ኛው ደቂቃ ምስጋናው መኮንን ከመሐል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ አምልጦ በመውጣት ከግብ ጠባቂው ፊት ለፊት ተገናኝቶ ያመከነው በደደቢት በኩል ፤ በ9ኛው ደቂቃ ዳግም አርዓያ ከግራ መስመር በመግባት የመታውና የውጪውን መረብ ታኮ የወጣበት ኳስ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በመጀመርያዎቹ 10 ደቂቃዎች የታዩ ሙከራዎች ነበሩ። በ22ኛው ደቂቃ ከመሐል ሜዳ መሬት ለመሬት የተሻገረውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ አምልጦ በመውጣት ራሱን ነፃ ያደረገው ኢብራሒም ቢያኖ ቅዱስ ጊዮርጊስን ቀዳሚ ሲያደርግ ከ10 ደቂቃዎች በኋላ ከግብ ጠባቂው ጎዳና ሙሉ በቀጥታ የተለጋውን ኳስ የደደቢቱ ተከላካይ ዳግም ለማውጣት ሲጥር ሳይሳካ በመቅረቱ ዳግም አርዓያ በአግባቡ ተቆጣጥሮ የቅዱስ ጊዮርጊስን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።

ከጎሎቹ መቆጠር በኋላ ደደቢቶች በ39፣ 40 እና 42ኛው ደቂቃዎች ሦስት ጎል መሆን የሚችሉ ኳሶችን አግኝተው ብሩክ ብርሀኑ እና ምስጋናው መኮንን አምክነዋቸዋል። የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ግን በግምት ከ30 ሜትር የተገኘውን ቅጣት ምት ሙሉቀን ተስፋዬ አክርሮ መትቶ ወደ ግብነት በመለወጥ የመጀመርያው አጋማሽ በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 መሪነት ተገባዷል።

ጥፋቶች የበዙበት እና ጥቂት የግብ እድሎች በታዩበት በሁለተኛው አጋማሽ በ60ኛው ደቂቃ ከሉክ ፓውሊን የተሻማውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲተፋው ጊዮርጊሶች ቢያስቆጥሩም በአወዛጋቢ ሁኔታ የተሻረው እና በ76ኛው ደቂቃ አቤል አምበሴ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ያወጣበት የቅጣት ምት በሁለተኛው አጋማሽ የሚጠቀሱ ብቸኛ ሙከራዎች የነበሩ ሲሆን ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ዳግም አርዓያ ፣ በደደቢት በኩል አንተነህ ከተማ መልካም እንቅስቃሴ ያደረጉ ተጫዋቾች ናቸው። (በአብርሀም ገብረማርያም)

10:00 ላይ ቀጥሎ በተካሄደው ጨዋታ ወላይታ ድቻ አዲስ አበባ ከተማን 3-1 አሸንፏል። በአዲስ አበባ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ እና መሀል ሜዳ ላይ በሚቆራረጡ ቅብብሎች ታጅቦ በጀመረው ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች የግብ ሙከራዎችን በማድረግ ቀዳሚ ነበሩ። በ3ኛው ደቂቃ የአጥቂ አማካዩ ምስክር መለሰ ከእያሱ ለገሰ መሀል ሜዳ ላይ የቀማውን ኳስ ይዞ በመሄድ ከሳጥኑ ጠርዝ አቅራቢያ ሞክሮ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። ከ4 ደቂቃዎች በኃላም ምስክር ከዛው ቦታ ላይ ሌላ ሙከራ አድርጎ ውጤቱም ተመሳሳይ ሆኗል። ቅብብሎቻቸው የተጋጣሚያቸውን የአማካይ ክፍል አልፈው ሙከራ ለመሆን ጊዜ የወሰደባቸው አዲስ አበባዎች በሴድዋን ናስር እና አላዛር ሽመልስ አማካይነት ከርቀት ያደረጓቸው ሙከራዎች በግቡ አናት የወጡ ነበሩ። ሆኖም 26ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ሞክሮት የተመለሰውን የፊት አጥቂው አሸናፊ ጉታ ከሳጥን ውስጥ በድጋሜ ሞክሮ ለጥቂት የወጣበት አጋጣሚ ቡድኑን ቀዳሚ ለማድረግ የተቃረበ ነበር። የተጋጣሚያቸው እንቅስቃሴ ከመሀል ሜዳ እንዳያልፍ በማድረግ በፍጥነት ወደ ግብ ይደርሱ የነበሩት ድቻዎች 32 እና 33ኛው ደቂቃዎች ላይ ያደረጓቸው ሙከራዎች ኢላማቸውን የጠበቁ ነበሩ። ሆኖም የመስመር አማካዩ በረከት ወንድሙ ድንቅ ሆኖ ከዋለው ምስክር መለሰ በግሩም ሁኔታ ደርሶት ከሳጥን ውስጥ የሞከረውም ሆነ ሙሉቀን ተስፋዬ ከርቀት ያደረገው ሙከራ ለአዲስ አበባው ግብ ጠባቂ ናትናኤል ተፈራ እምብዛም ፈታኝ አልሆኑም። ነገር ግን ምስክር 42ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ አክርሮ የመታው ግሩም ኳስ ወላይታ ድቻን ከእረፍት በፊት ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከእረፍት በኃላ የነበረው የጨዋታ ሂደት ከመጀመሪያው በፍጥነትም ሆነ የሜዳ ላይ ክፍተትን በመጠቀሙ ረገድ የተሻለ ነበር። ከዚህ ባለፈም ሶስት ግቦች የተቆጠሩበትም ጭምር ሆኖ አልፏል። አጋማሹ ምንም እንኳን በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ያለቀለት የግብ ሙከራ ባይታይበትም 55ኛው ደቂቃ ላይ ግን በድቻው የመስመር አማካይ ሳምሶን ደጀኔ አማካይነት ግብ ተቆጥሮበታል። በፊት አጥቂው ታምራት ስላስ አማካይነት በግራ መስመር የተጀመረው ጥቃት በድንቅ ቅብብሎች ሰምሮ ነበር በሳምሶን አማካይነት ግብ የሆነው። ነገር ግን አዲስ አበባዎች ከአንድ ደቂቃ በኃላ ከአሸናፊ ጉታ ሙከራ የተመለሰችን ኳስ በብሩክ ስሞ አማካይነት አስቆጥረው በፍጥነት ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል። በቀጣይም ይበልጥ ወደፊት ገፍተው እና ተጋጣሚያቸውን ተጭነው በመጫወት የአቻነቷን ግብ ቢፈልጉም የድቻን የመከላከል አደረጃጀት ማለፍ ከብዷቸው ታይቷል። ይልቁንም ወላይታ ድቻዎች 73ኛው ደቂቃ ላይ በፈጠሩት የመልሶ ማጥቃት ዕድል ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘው ታምራት ስላስ በጥሩ አጨራረስ ባስቆጠራት ኳስ መሪነታቸውን ማስፋት ችለዋል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም አዲስ አበባዎች ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም 88ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው  አብዱልሳትር መኪ ከሙባረክ ጅላሉ የተሻገረለትን ኳስ ከቅርብ ርቀት ሲሞክር ሁለተኛ ግብ ለማግኘት ቢቃረቡም ያሰቡትን ሳያሳኩ ጨዋታው በወላይታ ድቻ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። (በዮናታን ሙሉጌታ)

በዚህ ምድብ ይርጋለም ላይ በሲዳማ ቡና እና በመሪው ሀዋሳ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።