ፕሪምየር ሊግ | የ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ – ክፍል 3

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ ከሚጠበቁ ስምንት ጨዋታዎች መሀከል ሁለቱ አዲስ አበባ ላይ ይደረጋሉ። የሰዐት ማሻሻያ ተደርጎባቸው 9፡00 እና 11፡30 ላይ የሚከናወኑትን ሁለቱ ጨዋታዎችም በክፍል ሶስት ቅድመ ጨዋታችን ዳሰናቸዋል። 

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ

ይህ ጨዋታ በሁለቱ የሰንጠረዡ ክፍሎች ላይ ባሉት ፉክክሮች ውስጥ ወሳኝ ከሆኑ ጨዋታዎች መሀከል አንዱ ነው። ከመቐለ አንድ ነጥብ ይዞ የተመለሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተስተካካይ ጨዋታዎቹ ውጤቶች ደረጃውን ወደ 2 ከፍ አድርጎ መሪውን በሁለት ነጥቦች ልዩነት መከተል የጀመረ ሲሆን በአባ ጅፋር ውጤት ላይ ቢመሰረትም ነገ ወደ ሊጉ መሪነት የመምጣት ዕድል ይኖረዋል። የመቐለውን ቀሪ 45 ደቂቃዎች አርብ እንደሚጫወት የሚጠበቀው ወልዋል ዓ.ዩም የነጥብ መቀራረብ ከሚታይበት የወራጅ ቀጠና ፈቀቅ ለማለት ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይፈልጋል። ማሸነፍ ካለው ዋጋ አንፃርም ጥሩ ፉክክር የሚደረግበት የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ከቡድኖቹ ይጠበቃል። 

የቅዱስ ጊዮርጊሱ አዲስ አጥቂ ሪቻርድ አፒያ በኢትዮ ኤሌክትሪኩ ጨዋታ ከገጠመው ጉዳት ሙሉ ለሙሉ ያላገገመ ሲሆን አማራ ማሌ ግን ከጉዳት እንደሚመለስ ይጠበቃል። ምንም ጉዳት የሌለበት ወልዋሎ ዓ.ዩ በመከላከያው ጨዋታ በነበረው ክስተት ቅጣት ተላልፎባቸው ከነበሩት ስድስት ተጨዋቾቹ መሀከል ቅጣቱ የተነልላቸው ዋለልኝ ገብሬ ፣ በረከት ተሰማ ፣ ማናዬ ፋንቱ ፣ አፈወርቅ ኃይሉ እና ዓለምነህ ግርማ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆነዋል።

ተመሳሳይ አሰላለፍ እና የቡድን መዋቅር ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለማግኘት እና በመስመር አጥቂዎቻቸው ተጠቅመው ተጋጣሚያቸውን ለማስጨነቅ እንደሚጥሩ ይገመታል። በጨዋታው ናትናኤል ዘለቀን መጠቀም የጀመረው የቅስዱ ጊዮርጊስ የአማካይ ክፍል ከዋለልኝ ገብሬ እና አፈወርቅ ኃይሉ ጥምትረ ጋር ይገናኛል። ከመስመር አጥቂዎቻቸው የሚያገኟቸውን የመቀባባያ አማራጬች ተጠቅመው እና የቁጥር ብልጫን አሳክተው የመሀል ሜዳ የበላይነቱን ለማገኘትም የሚያደርጉት ፉክክር ተጠባቂ ይሆናል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በራሳቸው ሜዳ የሚጀምሯውቸን ኳሶች ለማስጣል ወደፊት ተጠግቶ ከሚጠብቃቸው የወልዋሎ የፊት እና የአማካይ ክፍል ጫና ነፃ ለመሆን የሚጠቀሟቸው ቀጥተኛ ኳሶች እንዲሁም ከመስመር አጥቂዎቹ የሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች አማራጭ የግብ ዕድሎችን መፍጠሪያ መንገዶች ሊሆኑ ይችላሉ። በወልዋሎዎች በኩል ደግሞ የፕሪንስ ሰቨሪንሆ ፣ ሪቻርድ ኦዶንጎ እና አብዱራህማን ፉሴይኒ የፊት ጥምረት ከተከላካዮች ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን በመጠቀም እንዲሁም ከፕሪንስ እና ፉሰይኒ ለአማካይ ክፍሉ ከሚሰጠው እገዛ መነሻነት የግብ ዕድሎችን ለማግኘት እንደሚንቀሳቀሱ ይታሰባል። 

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ዓዲግራት ላይ የተደረገው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊጉ ግንኙነታቸው ያለግብ የተጠናቀቀ ነበር።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮ አዲስ አበባ ላይ 8 ጊዜ የክልል ቡድኖችን ያስተናገደ ሲሆን አራቴ ሲያሸንፍ አንድም ጊዜ ሽንፈት አልገጠመውም።

– ወልዋሎ ዓ.ዩ ፎርፌ የተሰጠበት የመከላከያን ጨዋታ ሳይጨምር አዲስ አበባ ላይ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንዱን ሲያሸንፍ ሁለቴ ደግሞ ተሸንፏል።

ዳኛ

– ይህን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

ደደቢት ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በደረጃ ሰንጠረዡ የተራራቀ ቦታ ላይ ቢቀመጡም ላለመውረድ ጥረት ውስጥ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሊግ መሪነቱ ወደ አምስተኛነት ከተንሸራተተው ደደቢት አንፃር የተሸለ ውቅታዊ ውጤት አለው። በመጀመሪያው ዙር ስድስት ተከታታይ ድሎችን አሳክቶ የነበረው ደደቢት አሁን ደሞ ሶስት ሽንፈቶች በመደዳ ገጥመውታል። ዳግም የዋንጫ ፉክክሩን ለመቀላቀል እና አራተኛ ሽንፈት ላለማስተናገድም ኢትዮ ኤሌክትሪክን ይገጥማል። ጅማ አባ ጅፋር እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ከመሳሰሉ የሰንጠረዡ አናት ቡድኖች ጋር ገጥሞ የተሸነፈው ኤሌክትሪክ አሁን ደግሞ ሶስተኛ ፈተና ይገጥመዋል። ሆኖም በሁለትኛው ዙር ሁለት ጨዋታዎችን ማሸነፉ ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ማግኘትን ለማለም ተስፋ ይሰጠዋል።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል ምንም የጉዳት ዜና ባልተሰማበት በዚህ ጨዋታ የማይሳተፈው የአምስት የቢጫ ካርድ ቅጣት ያለበት የደደቢቱ የመስመር አጥቂ ሽመክት ጉግሳ ብቻ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የደደቢቱ አሰጣጥኝ ንጉሴ ስደታ የተጣለባውቸን የ6 ወር ቅጣት ጨርሰው ቡድናቸውን እንደሚመሩ ይጠበቃል። 

ደደቢት ከምንም በላይ አሰልጣኙን ማግኘቱ በእጅጉ ተጠቃሚ እንደሚያደርገው ይጠበቃል። ቡድኑ በመጀመሪያው ዙር ሲያሳየን የነበረውን አስፍተው የሚጫወቱ የመስመር አጥቂዎች ፣ ለአማካይ ክፍሉ እየቀረበ የተጋጣሚን የመሀል ተከላካዮች አቋቋም የሚያዛባ አጥቂ እና በተመጠነ ርቀት ሁለቱን ሽግግሮች የሚያሳልጡ የሶስቱ አማካዮቹን ውጤታማ ጥምረት ለመድገም የአሰልጣኙ በሜዳ ላይ መኖር ፋይዳው የጎላ ይሆናል። ቡድኑ በቀደመ ውህደቱ ላይ በዚህ ፍጥነት ያገኛል ተብሎ ባይጠበቅም ካለፉት ጨዋታዎች የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴን እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች የማጥቃት ፍላጎት ያላቸው የመስመር ተከላካዮችን ከመጠቀም እና በጉልበት የሚጫወት የመሀል ክፍልን ከመገንባት አንፃር መሻሻሎችን ያሳየው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዕድገቱን ማስቀጠል ከቻለ ለደደቢት ከባድ ተጋጣሚ የመሆን አቅም አለው። በእጅጉ የተጠናከረው የቡድኑ የግራ ወገን የማጥቃት ኃይል እና የካሉሻ አልሀሰን በተሻለ የጨዋታ ነፃነት ላይ የተመሰረተ የማጥቃት ተሳትፎ ግቦችን ለማግኘት ሊያግዘው ይችላል። ሆኖም ቡድኑ አሁንም በሙሉ ልብ ወደ ፊት ገፍቶ መጫወት ላይ እና በተጋጣሚ ላይ ብልጫ በሚወስድባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ሙከራዎችን ማድረግ ላይ ያለበትን ድክመት በነገው ጨዋታ መቅረፍ ይገባዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– እስካሁን 17 ጊዜ ተገናኝተው ደደቢት 11 በማሸነፍ ከፍተኛ የበላይነት ሲኖረው 3 ጊዜ አቻ ተለያይተው ኤሌክትሪክ በ3 ጨዋታዎች አሸንፏል። ደደቢት 34 ፣ ኤሌክትሪክ 14 ጎል አስቆጥረዋል።

– ካለፉት 10 ግንኙነቶች መካከል ኤሌክትሪክ አንድ ጊዜ ብቻ ነው ማሸነፍ የቻለው። (በ2008 የውድድር ዓመት 2-0)

– ደደቢት ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሳካት የቻለው አንድ ነጥብ ብቻ ሲሆን አስራት መገርሳ መቐለ ላይ ያስቆጠረው ግብም ብቸኛው የቡድኑ ጎል ነበር። 

– ከመዲናዋ ክለቦች ጋር ሲገናኝ ደካማ ሪከርድ ያለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመከላከያ ነጥብ ከተጋራበት እና ኢትዮጵያ ቡናን ካሸነፈበት ውጤት ውጪ ቀሪዎቹን 5 ጨዋታዎች በሽንፈት ደምድሟል።

ዳኛ

– ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃ/ስላሴ መሪነት የሚከናወን ይሆናል።