ሪፖርት | ጅማ አባጅፋር በሜዳው ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቷል 

ጅማ ላይ የሊጉ መሪ ጅማ አባ ጅፋር እና ላለመውረድ እየታገለ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማን ያገናኘው የ23ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ጅማ አባጅፋር በ22ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን ከገጠመው ስብስቡ ውስጥ መላኩ ወልዴን በአሮን አሞሀ ቀይሮ በ4-4-2 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ሲገባ በአርባምንጭ በኩል ቅዱስ ጊዩርጊስን ካሸነፈው ስብስብ ውስጥ ምንተስኖት አበራን በወንድወሰን ሚልኪያስ በመቀየር በ4-3-2-1 አሰላለፍ ወደሜዳ ገብቷል። ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ፋኖ ስፖርት ያዘጋጀው የወሩ ኮከቦች ሽልማት ለአዳማ ሲሶኮ እና ለአሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ተበርክቷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ የመጀመርያዎቹ 5 ደቂቃዎች በፈጣን እቅስቃሴና ቶሎ ቶሎ ወደግብ በመድረስ ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ የነበሩ ሲሆን ጅማዎች በኦኪኪ አፎላቢ እንዲሁም አርባምጮች በእንዳለ ከበደ አማካኝኘነት ወደ ግብ ቢደርሱም ኳስና መረብን ማገናኘት አልተቻለም። በ11ኛው ደቂቃ የማዕዘን ምት በሚሻሙበት ወቀች አዳማ ሲሶኮ እና አንድነት አዳነ ተጋጭተው አንድነት በጉዳት ተቀይሮ ሲወጣ ወደ ሆስፒታል ሄዶ የህክምና እርዳታ ተደርጎለትም ተመልሷል። ከ10ኛው ደቂቃ በኋላ ጅማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱ ቢሆንም ለአጥቂዎች የሚሻገሩ ኳሶች የተሳኩ አልነበሩም። የጅማ አባጅፋር የአማካይ እና የመስመር ተጫዋቾች የአርባምንጮችን የተደራጀ መከላከል አስከፍተው እድሎችን መፍጠር ሲሳናቸው ከመስተዋሉ ባሻገር በአርባምንጮች በተደጋጋሚ ሰዓት ለማባከንና የአባጅፋሮችን ተነሳሽነት ለማቀዝቀዝ የሚያደርጉት ጥረት የተሳካላቸው ቢሆንም የጨዋታው ውበት ያበላሸ እና ታዳሚውን ሲያስቆጣ የተስተዋለ ክስተት ነበር።

በዚህ መልኩ ያለ ጎል ሙከራዎች በዘለቀው ጨዋታ በ34ኛው ደቂቃ ዮናስ ገረመው ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ ጽዮን መርዕድ እንደምንም ካወጣበት ሙከራ ውጭ የመጀመሪያው አጋማሽ ይህ ነው የሚባል የጎላ ሙከራ ሳይደረግ ለእረፍት ወጥተዋል።

ከእረፍት መልስ ጅማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ቢወስዱም አርባምጮች ይበልጥ ወደ ኃላ በመሳብ በህብረት በመከላከል እና ከእረፍት በፊት እንደነበረው ሁሉ ጨዋታውን ለማቀዝቀዝ በተደጋጋሚ በመውደቅ እና በውሳኔዎች ላይ ዳኛ በመክበብ ላይ ተጠምደው ውለዋል። በተለይ ተመስገን ካስትሮ ከዳኛው ጋር የሚገባው ሰጣገባ በሜዳ የተገኙትን የስፖርት ቤተሰቦች ያሳዘነ ክስተት ሲሆን ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ጨዋታውን የመሩበት እና ሁኔታዎችን የተቆጣጠሩበት መንገድ የሚደነቅ ነበር።

ጨዋታው እስከ 88ኛው ደቂቃ ድረስ በመሐል ሜዳ ላይ ያመዘነ እና ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ሳንመለከትበት ወደ መገባደጃው ሲደርስ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ የመሀል ዳኛው ለጅማ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል። ከውሳኔው በኋላም በአስገራሚ ሁኔታ የአርባምንጭ ተጨዋቾች ሜዳውን ለቀው ለመውጣት ቢሞክሩም ተጠባባቂ ላይ ካሉ ከራሳቸው የቡድን አባላት ጋር ባለመግባባት እንደገና ወደሜዳ በመመለሳቸው ከ10 ደቂቃዎች በኋላ የተቋረጠው ጨዋታ በተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት ተጀምሯል። ሆኖም ኦኪኪ አፎላቢ የመታውን የፍፁም ቅጣት ምት ጽዮን መርዕድ አምክኖት አርባምንጭን ከሽንፈት ታድጎታል።

በዚህ ሳምንት ያለ ጎል የተጠናቀቀ ብቸኛ ጨዋታ ከሆነው ከዚህ ፍልሚያ በኋላ ጅማ አባ ጅፋር የሊግ መሪነቱን ባይለቅም ከተከታዮቹ ያለው ርቀት ጠቧል። አርባምንጭ ከተማ ደግሞ በኤሌክትሪክ ማሸነፍ ምክንያት ወደ ወራጅ ቀጠናው ተመልሶ ገብቷል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

ማትዮስ ለማ – አርባምንጭ ከተማ

ባገኘነው ነጥብ በጣም ደስተኛ ነኝ። ተጋጣሚያችን የሊጉ መሪ እንደመሆኑ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሞክረናል። መከላከላችንም ውጤታማ  ነበር። ሰዓት ማባከኑ ወራጅ ቀጠና ውስጥ እንደመገኘታችን ልጆቹ ውጤቱን ለማስጠበቅ ጉጉት አድሮባቸው ያደረጉት ነው። ፍፁም ቅጣት ምቱ ተገቢ ባይሆንም ጨዋታውን አቋርጠው ለመወጣት መሞከራቸው ተገቢ አይደለም። ተቆጥቼ መልሻቸው ውጤት አስመዝግበን ወጥተናል።

* አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ አስተያየት አልሰጡም።