ወንድወሰን ገረመው ወላይታ ድቻን ይቅርታ ሲጠይቅ ክለቡም ይቅርታውን ተቀብሎታል

የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ወንድወን ገረመው በልምምድ ወቅት ከተጫዋቾች ጋር በተፈጠረ ያለ መግባባት በክለቡ የአንድ አመት እገዳ እና የገንዘብ ቅጣት ተጥሎበት እንደነበር ይታወሳል። 

በፕሪምየር ሊጉ እና በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ጨዋታዎች ለወላይታ ድቻ ውጤት ግንባር ቀደሙን ድርሻ የሚወስደው ወንድወሰን በክለቡ ከተላለፈበት ቅጣት በኃላ ይፋዊ ይቅርታ ደብዳቤ ለክለቡ ማስገባቱን ለሶከር ኢትዮጵያ በእንዲህ መልኩ ገልጿል፡፡

” የልምምድ ሜዳ ውስጥ ያለመግባባት ተፈጥሮ ነበር። ሜዳ ውስጥ የተፈጠረ ችግር ደግሞ ሜዳ ውስጥ መፈታት ነበረበት። ነገር ግን በጣም ተጋኖ እንዲሰፋ ተደርጓል። እኔ ጥፋተኛ ሆንኩም አልሆንኩም ግን ነገሮች ሁሉ ሰላም መሆን ስላለባቸው የሚመለከተውን ሁሉንም አካል ከቦርድ እስከ ተጫዋች ከአሰልጣኝ እስከ ደጋፊ ብሎም እስከ ማህበረሰብ ድረስ ከክለቡ ጋር የሚገናኙትን ሁሉ ይቅርታ ጠይቄያለሁ። በሁኔታው የመጀመሪያ ተጎጂ እኔ ብሆንም ሲቀጥል ደጋፊው ክለቡም ሁሉም በሂደት ተጎጂ ነው የሆኑት። ስለዚህ ለነበሩት ሁኔታዎች ይቅርታ ጠይቄ ይቅርታዬም ተቀባይነት አግኝቶ አሁን ላይ ሰላም ወርዷል። ዋናው እርቁ ነው ለሁላችንም የሚበጀው። ይህ ነገር መፈጠር የለበትም ፤ ግን የተፈጠረው እና የተወራው ነገር የሰማይ እና የምድር ያህል ነው። በየትኛውም ዓለም ችግሮች ይከሰታሉ። እንኳን ሰዎች እግርም ከእግር ይጋጫሉ። ነገሩን ያባባሰው ግን ችግሩም ትርኢት የተደረገበት መንገድ ነው። አስቀድሞ የተወሰነው ነገር ትክክል አይደለም። ያም ቢሆን ግን ሰላም ለማውረድ እና መግባባት እንዲኖር ሰላም መፍጠሩ ተገቢ ነው። ይህ ደግሞ ብልሀትም ነው ትልቅነትም ነው”

የወንድወሰን ይቅርታ ተቀባይነት ስለማግኘቱ ደግሞ የክለቡ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጌታሁን ጋረደው ይህን ብለዋል።

” ይቅርታውን ተቀብለነዋል። ያ ማለት ደግሞ በቀጣይ ቦርዱ ተሰብስቦ ቅጣቱን የሚያስቀንስለት ነው። ችግሩ እኛ አብረን ባለንበት ወቅት የተፈጠረ ስለነበር እንደ ማኔጅመንት በአንድ ላይ ሆነን አቤቱታም ካለ በሂደት ስለሆነ የሚፈፀመው ከይቅርታው በኃላ ምላሹን ሰጥተነዋል። እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ቅጣቱ ይቀንስለታል። የኮቺንግ ስታፉ ያወቀው ነገር የለም። እኛ እንደ አመራር ግን ተቀብለነዋል ፤ ከአሰልጣኞቹጋም አውርተናል። ጠቃሚ ተጫዋች ስለሆነ ለሌሎች ማስተማርም ስላለበት ተቀብለናል። ከተጫዋቾቹ ጋር በዚህ ረገድ በማውራት ይቅርታውንም ተቀብለነዋል፡፡ “