ፕሪምየር ሊግ | የ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ – ክፍል 1

ሁሉም ክለቦች እኩል 23 ጨዋታዎችን ያደረጉበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በ7 የ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ይቀጥላል። በክፍል አንድ ቅድመ ዳሰሳችንም ሶስቱ የሊጉ መሪዎች የሚያደርጓቸው  ጨዋታዎች ላይ ትኩረት አድርገናል።

መከላከያ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በፕሪምየር ሊጉ ከሚገኙ ጠንካራ ፉክክር ከሚስተናገድባቸው ጨዋታዎች መሀከል የሚመደበው የመከላከያ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በ11፡30 የሚደረግ ይሆናል። ከውጤት መንሸራተት በኃላ ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ራሱን በሊጉ ለማደላደል ተቃርቦ የነበረው መከላከያ ድሬዳዋ ላይ ሽንፈት ከገጠመው በኃላ የሰበሰበው 28 ነጥብ እምብዛም አስተማማኝ አይመስልም። በመሆኑም የዛሬውን ጨምሮ በቀጣይ በሚጠብቁት ጠንካራ ጨዋታዎች በፍጥነት ወደ አሸናፊነት መመለስ ይጠበቅበታል። ባሳለፍነው ረቡዕ ወልዋሎን በአሜ መሀመድ ብቸኛ ጎል የረታው ቅዱስ ጊዮርጊስም እንደተጋጣሚው ሁሉ ሶስት ነጥቡን አጥብቆ ይፈልገዋል። ውጤቱን አስተካክሎ ከመሪው ጋር በነጥብ ዕኩል የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዳለፉት አመታት አጨራረሱን ለማሳመር እና በሻምፒዮንነቱ ለመቀጠል በብዛት ሲፈትነው የሚታየው መከላከያን ማሸነፍ ለቀጣዮቹ ሳምንታት ፈተናዎች ትልቅ ዋጋ ይኖረዋል። 

ከሁለቱ ቡድኖች ቴዎድሮስ በቀለ እና ሳላዲን ሰይድ የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል። ከዚህ በተጨማሪ የመከላከያው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ እና ተከላካዩ አወል አብደላ እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ የፊት አጥቂዎች ሪቻርድ አፒያ ፣ አሜ መሀመድ እና አማራ ማሌ በጉዳት ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ተጨዋቾች ናቸው። 

ከቡድኖቹ ሰሞንኛ የሜዳ ላይ ባህሪ ስንነሳ የዚህ ጨዋታ የአማካይ መስመር ፍልሚያ ትኩረት ይስባል። በዋነኝነት የዳይመንድ ቅርፅ ያለው የአማካይ መስመር የሚጠቀመው መከላከያ እንደተጋጣሚው የመሀል ሜዳ ጥንካሬ አምስት አማካዬችን የሚያሰልፍባቸው ወቅቶች አሉ። ቅዱስ ጊዮርጊስም ባሳለፍናቸው ሳምንታት ቀድሞ በመስመር አጥቂነት የምናውቃቸው ተጨዋቾቹን ወደ ኃላ በመሳብ ለ4-2-3-1 የቀረበ አሰላለፍን ሲከተል ተመልክተነዋል። ይህ የሚሆን ከሆነ ከመከላከያ ዳዊት እስጢፋኖስ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ አብዱልከሪም ኒኪማ ከፊታቸው ከሚገኙ ሁለት ነጣቂ አማካዮች ጋር የሚገናኙባቸው አጋጣሚዎች ወሳኝ ሲሆኑ በነዚህ ጊዚያት ከጎናቸው ከሚኖሩ የመስመር አማካዮች ጋር የሚኖራቸው የቅብብል ስኬት እጅግ ወሳኝ ይሆናል። በዚህ ሂደት ውስጥ ቡድኖቹ ወደ ማጥቃት በሚሸጋገሩባቸው ጊዜያት የመስመር ተከላካዮቻቸው የማጥቃት ተሳትፎ ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ መሀል ሜዳ ላይ የቁጥር ብልጫን የሚያስገኝ እና የሜዳውን የጎን ስፋት ለመጠቀም የሚያስችል እንዲሆን ይጠበቃል። በመከላከያ በኩል ወትሮውንም ቢሆን አጥብበው በመጫወት የሚታወቁት የመስመር አማካዮች ከበስተኃላቸው ላሉት ተከላካዮች በቂ በቶ እንደሚተው የሚታሰብ ሲሆን ከአሰልጣኝ ስዩም መምጣት በኃላ የማጥቃት ተሳትፏቸው የጨመረው የመስመር ተከላካዮችም እስከሶስተኛው የሜዳ ክፍል ድረስ የመሄድ ድፍረት እንደሚኖራቸው ይገመታል። በተመሳሳይ መልኩ ጥሩ መሻሻል እያሳዩ እና ለቅብብሎች አማራጭ ከመሆን ባለፈ ሙከራዎችን ማድረግ የጀመሩት (አብዱልከሪም በመቐለ ላይ ግብ ማስቆጠሩ ሳይረሳ) የቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር ተከላካዮችም ተሻጋሪ ኳሶችን በመጣል እና ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ቀጥተኛ ሙከራዎችን በማድረግ የቡድኑን የማጥቃት ሀይል የሚያግዙ ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ በርካታ ዋንጫ በማንሳት ቀዳሚ የሆኑት ሁለቱ ክለቦች በሊጉ 25 ጊዜ ተገናኝተው መከላከያ ሁለት ጊዜ ብቻ ሲያሸንፍ 12 አቻ ተለያይተው 11 ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስ አሸንፏል። መከላከያ 13 ጎሎች ሲያስቆጥር ቅዱስ ጊዮርጊስ 28 አስቆጥሯል።

– ጨዋታው ከፍተኛ ፉክክር እንደሚያስተናግድ ከሚያሳዩ እውነታዎች መካከል ካለፉት 12 ግንኙነቶች 9 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት መጠናቀቃቸው ነው።

– መከላከያ ከ3 ተከታታይ ድሎች በኋላ ባለፈው ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ ሲሸነፍ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለፉት 7 ጨዋታዎች አንድ ሽንፈት ብቻ አስተናግዷል።

ዳኛ

– የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የሚመራው ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ነው። 

ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ ጅማ አባ ጅፋር

የዚህ ጨዋታ ውጤት በሰንጠረዡ የላይኛውም ሆነ የታችኛው ክፍል ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ በሁለት የሊጉ አዲስ ቡድኖች መሀከል ከሚደረግ ጨዋታ በላይ እጅግ ከፍ ባለ ሁኔታ ዋጋ እንዲኖረው አድርጓል። ከመቐለ ጋር የቀረውን 45 ደቂቃ ያለግብ የጨረሰው ወልዋሎ ዓ.ዩ ላለመውረድ በሚያደርገው ትግል ውስጥ የአርቡ የሽረ ጨዋታ ተስፋውን ቢያለመልምለትም ከስጋት ነፃ ግን አላደረገውም። በዚህም የተነሳ በዛሬው ጨዋታ ከሊጉ መሪ ጋር የሚገናኝ ቢሆንም ከወረጅ ቀጠናው የሚያስወጣውን ውጤት ሊሸምት የሚችልበት ስለሆነ ከባድ ፍልሚያ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። አስገራሚ ግስጋሴው የተቀዛቀዘው ጅማ አባ ጅፋር ሁለት ነጥብ ብቻ ያሳካባቸው ያለፉት ሁለት ጨዋታዎች ከሊጉ መሪነት ባያወርዱትም ከዚህ ጨዋታ ውጤት አለማግኘት ግን ወደ ሶስተኝነት ዝቅ የማለት አደጋን አጋርጦበታል። በሊጉ መሪነት ለመዝለቅም ከዓዲግራት ሶስት ነጥቦችን ይዞ መመለስ ለአባጅፋር አማራጭ የሌለው አላማ ይሆናል።

ጅማ አባ ጅፋር ከቅጣትም ሆነ ከጉዳት ነፃ የሆነ ስብስቡን ይዞ ወደ ዓዲግራት ያቀና ሲሆን በወልዋሎ በኩልም ቅጣት ላይ ከሚገኙት በረከት አማረ እና አሳሪ አልመሀዲ በቀር በጉዳት ጨዋታው የሚያመልጠው ተጨዋች እንደማይኖር ተሰምቷል።

ጨዋታው ሙሉ ለሙሉ በኳስ ቁጥጥር ላይ ትኩረቱን የሚያደርግን ቡድን ከ በፈጣን ሽግግር ወደ ተጋጣሚው ሜዳ ለመድረስ የማይቸገር ቡድንን የሚያገናኝ ነው። ሜዳ ላይ ከሚኖሩት ፍልሚያዎች መሀከል በብዛት የወልዋሎ የኳስ ቁጥጥር የመጨረሻ ማረፊያ የሆኑት የመስመር አጥቂዎች አብዱርሀማን ፉሰይኒ እና ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ለማጥቃት ወደ ፊት ከመሄድ ከማይቦዝኑት የአባጅፋር የመስመር ተከላካዮች ኄኖክ ኢሳያስ እና ኄኖክ አዱኛ የሚገናኙባቸው ቅፅበቶች ተጠቃሽ ናቸው። በሽግግሮች ወቅት ማንኛቸው ወደ ፊት ገፍተው አደጋ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ እና በአንድ ለአንድ ግንኙነት ወቅት ማንኛቸው አሸናፊ እንደሚሆኑ መመልከት ወሳኝ ይሆናል። ከተጋጣሚው የመሀል ሜዳ ማርኪንግ ነፃ ለመሆን ከሁለቱ የመስመር አማካዮቹ ቢያንስ የአንዱን እገዛ ማግኘት የሚያስፈልገው የወልዋሎው የአፈወርቅ ኃይሉ እና ዋለልኝ ገብሬ የአማካይ ክፍል ጥምረት እንደሁል ጊዜው ሁሉ የቡድኑን የመሀል ሜዳ የበላይነት ለማስጠበቅ ከአሚኑ ነስሩ እና ይሁን እንዳሻው ጋር መፋለም ይኖርበታል። ይህን በአሸናፊነት መወጣት እና በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ራስን ነፃ በማድረግ የመጨረሻ የቅብብል አማራጮችን መፍጠር ከሁለቱ አማካዮች የሚጠበቅ ነው። በጅማ አባ ጅፋር በኩልም ወደ ራሱ ግብ ያፈገፈገ እና መከላከል ላይ ያመዘነ ቡድን የሚጠበቅ ባይሆንም መሀል ከሚያስጥላቸው ኳሶች ግን ወደ መሀል ሜዳ ከሚቀርበው የተጋጣሚው የተከላካይ መስመር ጀርባ ለመገኘት እንደሚጥር ይታሰባል። በዚህ ሂደት ውስጥም የተመስገን ገብረኪዳን ከመስመር የሚነሱ እንቅስቃሴዎች እጅግ ወሳኝ ሲሆኑ ከኦኪኪ ጋር የሚኖረው የቅብብል ፍጥነት እና ጥራት ለጅማ የግብ ሙከራዎች ዋነኛ መንገድ እንደሚሆን ይታሰባል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች ለመጀመርያ ጊዜ በሊጉ የተገናኙት ዘንድሮ ሲሆን ጅማ ላይ ባደረጉት ጨዋታ ጅማ አባጅፋር 3-0 አሸንፏል።

– ጅማ ካለፉት 6 የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ ሽንፈት ሲያስተናግድ ወልዋሎ የመቐለውን ድል ጨምሮ ካለፉት 5 የሜዳው ጨዋታዎች ሶስት አሸንፎ 2 አቻ ተለያይቷል።

ዳኛ

– ፌደራል ዳኛ ወልዴ ንዳው ለጨዋታው የተመደበ አርቢትር ነው። 

መቐለ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

በ23ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቻቸውን በተመሳሳይ የ2-0 ውጤት መርታት የቻሉት መቐለ እና ሀዋሳ ነገ ደግሞ እርስ በእርስ ይገናኛሉ። የጨዋታው ትርጉም ለመቐለዎች ከፍ ያለ ቢሆንም ለሀዋሳም ቢሆን እንደምንም በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ለመገኘት ለራሱ መንገድ የሚከፍትበት ነው። ሽረ ላይ ከወልዋሎ ጋር በቀሪ 45 ደቂቃዎች የተገናኙት መቐለዎች የሊጉን መሪነት የሚጨብጡበትን ዕድል አሳልፈው ሰጥተዋል። ነገር ግን ከበላያቸው ካሉት ሁለት ክለቦች ጋር ያላቸው የአንድ ነጥብ ልዩነት ሀዋሳን አሸንፎ ወደ ሊጉ መሪነት ለመምጣት ራሳቸውን ይበልጥ እንዲያነሳሱ እንደሚያደርጋቸው መናገር ይቻላል። መሀል ሰፋሪ የሚሆኑት ቡድኖች ገና በግልፅ ባልተለዩበት ፕሪምየር ሊጉ ሀዋሳ ከተማ በቀሪ ሳምንታት የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የሻምፒዮንነት ተስፋን የዘሉ እንዲሆኑ ከባዱን የመቐለን ፈተና በአሸናፊነት መወጣት ይኖርበታል። በመሆኑም ጨዋታው ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር ከሚደረግባቸው የ24ኛ ሳምንት መርሀ ግብሮች አንደኛው እንደሚሆን ይታሰባል። 

የመቐለ ከተማው ዐመለ ሚልኪያስ በወልዋሎው ቀሪ 45 ደቂቃዎች በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ በመውጣቱ በቅጣት ይህ ጨዋታ የሚያልፈው ሲሆን ቢስማርክ ኦፖንግም ከጉዳቱ እንዳላገገመ ተሰምቷል። በሀዋሳ በኩል እስራኤል እሸቱ ጉዳት ላይ የነበሩት ዮሀንስ ሴጌቦ እና ዳንኤል ደርቤን ሲቀላቀል ጂብሪል አህመድ ደግሞ ከጉዳት ወደ ጨዋታ እንደሚመለስ ይጠበቃል።

ሀዋሳ ከተማ ከሚከተለው ወጥ የሆነ አጨዋወት እና ከሚፈልገው ምቹ ሜዳ አንፃር መቐለ ከተማም ሜዳው ላይ የሚያስተናግደው ጨዋታ መሆኑ ከግምት ውስጥ ሲገባ በሁለቱም ተጋጣሚዎች በኩል ማጥቃትን መሰረት ያደረገ እና በፍጥነቱም ከፍ ያለ ጨዋታን እንድንጠብቅ ያደርገናል። ግብ ከማስቆጠር ባለፈ በሁሉም የማጥቃት ሂደቶች ላይ አሻራውን በማሳረፍ ለተጋጣሚዎች እጅግ አስቸጋሪ የሚሆነው አማኑኤል ገብረ ሚካኤል ዛሬም ለሀዋሳ የተከላካይ ክፍል ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል። በቁጥር ጥቂት በሆኑ ተጨዋቾች ግን ደግሞ ፍጥነት በተሞላበት መንገድ የሚተገበረው የመቐለ የማጥቃት ሽግግር ከግብ ክልሉ የራቀ አማካይ የቦታ አያያዝ የሚኖረው የሀዋሳን የተከላካይ ክፍል ኢላማ ማድረጉ የማይቀር ነው። በተለይም በመከላከል ቀጠናቸው ኳስ ማስጣል የማይቸገሩት መቐለዎች የመስመር አማካዮቻቸው ከሚጠቁ የመስመር ተከላካዮች ጅርባ በመገኘት በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ለመገኘት እምብዛም አይቸግራቸውም። እንደሁል ጊዜውም በኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርተው በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ በሚደረጉ ቅብብሎች ክፍተቶችን ለማግኘት የሚሞክሩት ሀዋሳዎች በበኩላቸው የዐመለ ሚልኪያስ ጉዳት ተጠቃሚ ቢያደርጋቸውም በብዛት የማይንቀሳቀስ የአራት ተከላካዮች ጥምረትን ለማለፍ በእንቅስቃሴ የተሞላ የፊት መስመር አስፈላጊያቸው ይሆናል። ይህን ሂደት ለማገዝ የመስመር ተከላካዮቻቸው ሀላፊነትም የሚዘነጋ ባይሆንም የመቐለን ፈጣን የማጥቃት ሽግግርን ለመቋቋም ግን ከወትሮው ቀነስ ያለ ተሳፎፍ እንደሚኖራቸው ይገመታል። ከዚህ በተጨማሪ የታፈሰ ሰለሞን እና ሙሉአለም ረጋሳ ጥምረት ከሚካኤል ደስታ እና የዐመለን ቦታ ሊሸፍን ከሚችለው ጋቶች ፓኖም ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ ተጠባቂ ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በመጀመርያ ዙር በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ ላይ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል።

– መቐለ ከተማ ትግራይ ስታድየም ላይ በደደቢት ከመረታቱ በቀር ሽንፈት ያልገጠመው ሲሆን ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ከሜዳው ውጪ ድል ካስመዘገበ አንድ አመት አልፎታል።

ዳኛ

– ይህ ጨዋታ የሚካሄደው በፌደራል ዳኛ ሀብታሙ መንግስቴ መሪነት ነው።