ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመከላከያ አቻ ተለያይቶ የሊጉ መሪ የሚሆንበትን እድል አምክኗል

የ24ኛው ሳምንት የሊጉ የመጀመሪያ ቀን ውሎ የመጨረሻ በነበረው የአዲስ አበባ ስታድየሙ ጨዋታ መከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተገናኝተው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል። 

ሁለቱ ተጋጣሚዎች በ23ኛው ሳምንት ባደረጓቸው ጨዋታዎች ከተጠቀሙበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በድምሩ የአምስት ተጨዋቾች ቅያሪ አድርገዋል። ወደ ድሬደዋ አቅንቶ 1-0 ተሸንፎ የተመለሰው መከላከያ በዐወል አብደላ እና አማኑኤል ተሾመ ምትክ ምንተስኖት ከበደ እና በኃይሉ ግርማን ወደ ሜዳ ሲያስገባ ምንይሉ ወንድሙም በማራኪ ወርቁ ተተክቷል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ወልዋሎ ዓ.ዩን ከረታበት ጨዋታ በአቡበከር ሳኒን እና ጉዳት በገጠመው አሜ መሀመድ ምትክ ለበሀይሉ አሰፋ እና አዳነ ግርማ የመሰለፍ ዕድል ሰጥቷል።

ጨዋታው ጎል ለማስተናገድ ሰከንዶች ብቻ ነበሩ ያስፈለጉት። ቴዎድሮስ ታፈሰ ከመሀል ሜዳ በረጅሙ የላከውን ድንቅ ኳስ ማራኪ ወርቁ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሳጥን ውስጥ በሚገባ ተቆጣጥሮ መከላከያን መሪ ሲያደርግ ጨዋታው ከጀመረ ግማሽ ደቂቃ እንኳን አልሆነም ነበር። ከግቡ መቆጠር በኃላ በቶሎ ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተደጋጋሚ ሙከራዎችን አድርገዋል። በተለይም ናትናኤል ዘለቀ ከመስመር የመጣለትን ኳስ በቀጥታ የሞከረበት እና የተመለሰውንም ኳስ አዳነ በድጋሜ ሞክሮ ሳይሳካለት የቀረበት አጋጣሚ ቡድኑ በጊዜ አቻ ለመሆን የተቃረበበት ነበር። ከራሱ የግብ ክልል እምብዛም የራቀ ከማይመስለው  የመከላካያ የኃላ መስመር ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ላይ አተኩረው ጫናቸውን  የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 

በሌሎች ሁለት አጋጣሚዎችም ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። 11ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ መልኩ ለኦዝቫልዶ ታቫሬዝ የተጣለውን ኳስ ለማዳን ግብ ጠባቂው ይድነቃቸው እና ሙሉቀን ደሳለኝ እርስ በእርስ ሲጋጩ ያገኘውን አጋጣሚ ታቫሬዝ መጠቀም ሳይችል ቀርቷል። ተደጋጋሚ የነበሩት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተሻጋሪ ኳሶችን በማምከኑ በኩል ጥሩ የነበሩት የመከላከያ የመሀል ተከላካዮች 16ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉአለም መስፍን ከመሀል ሜዳ ያሻማውን ኳስ ማመክን ሳይችሉ ቢቀሩም ኳሷን በድንቅ ሁኔታ በደረቱ ያበረደው አዳነ ግርማ ከቅርብ ርቀት የሞከረው ኳስ ኢላማውን ሳይጥጠብቅ ቀርቷል።

ከጨዋታው መጀመር አንስቶ መጣል የጀመረው ከባድ ዝናብ እያባራ ቢሄድም የሜዳው መጨቅየት ግን ቀጣዮቹን ደቂቃዎች ለሁለቱም ተጋጣሚዎች ከባድ አድርጎት ነበሩ። በተጨዋቾች መሀል የሚደረጉ ቅብብሎች የታሰበላቸው ቦታ ሳይደርሱ እየቆሙ አንዳንዴ ደግሞ ነጥረው ያለቅጥ እየረዘሙ መሀል ሜዳ ላይ ሲቆራረጡ ይታይ ነበር። መሰል ክስተቶች የግብ ክልሎች ጋር ቢፈጠሩ አደጋቸው የጎላ ቢሆንም በአመዛኙ መሀል ሜዳ ላይ ይታዩ የነበረ በመሆኑ ተጨዋቾች መልሰው ነገሮችን ለማስተካከል ጊዜ ያገኙ ነበር። በፍጥነት መሪ መሆን ቢችሉም የመጀመሪያዎቹን 20 ደቂቃዎች በከባድ ጫና ውስጥ ያሳለፉት መከላከያዎች በመጠነኑ በተነቃቁባቸው ደቂቃዎች ጥሩ የሚባል የኳስ ቁጥጥር ድርሻን ቢያገኙም አጫጭር ቅብብሎቻቸው ከሜዳው ባህሪ ጋር አብረው ሊሄዱ አልቻሉም። ሆኖም 28ኛው ደቂቃ ላይ የዳዊት እና የማራኪ ቅብብል ለፍፁም ገ/ማርያም ነፁህ ዕድል ቢፈጥርለትም ኳስ ገፍቶ ሳጥን ውስጥ ከተገኘ በኃላ ከመሞከሩ በፊት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ከኃላ ደርሰው አስጥለውታል። 

በቀሪዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች የታዩት ሙከራዎች 32ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉአለም መስፍን ከበሀይሉ ቅጣት ምት የተነሳችን ኳስ በግንባሩ የሞከረበት እና 39ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ዘለቀ ከማዕዘን ምት የመጣለትን ኳስ በግንባሩ ሞክሮ በግቡ ቋሚ የተመለሰበት ይጠቀሳሉ። ከዚህ ውጪ የሜዳው ምቹ አለመሆን የተጨዋቾች የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች በእልህ እና በሽኩቻዎች የተሞሉ እንዲሆኑ ድርሻው ከፍ ያለ ነበር። በተደጋጋሚ ከኳስ ጋር ይታይ የነበረው ይህ ሂደት 45ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከኳስ ውጪ መደገሙ የኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ቀይ ካርድ እንዲመዘዝ ምክንያት ሆኗል። ከቀኝ መስመር ወደ መከላከያ ሳጥን ውስጥ በተጣለው ኳስ የተገናኙት አዲሱ ተስፋዬ እና አዳነ ግርማ ኳሱን ሳያገኙት በይድነቃቸው ቢያዝም በወደቁበት በመሰናዘራቸው ነበር ሁለቱም ተያይዘው በቀይ ካርድ እንዲወጡ የሆነው።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ቡድኖቹ የተፈጠረባቸውን የተጨዋች ጉድለት በምን መልኩ ይሸፍኑታል የሚለው ጥያቄ ተጠባቂ ነበር። መከላከያ ሳሙኤል ታዬን በመሰዋት በአማካይነት የምናውቀው ኦጉታ ኦዶክን አዲሱ ለጎደለበት የመሀል ተከላካይ ቦታ ቀይሮ አስገብቶታል። ቡድኑ በጉዳት ምክንያት በተጠባባቂ ወንበር ላይ የመሀል ተከላካይ አለመያዙ ለዚህ ውሳኔ ያበቃው ይመስላል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ግን የተጨዋች ቅያሪ ያልተደረገ ሲሆን አብዱልከሪም ኒኪማ የቡድኑን የግራ መስመር ጥቃት እየመራ እና በተለይ ከኳስ ውጪ በሚኖረው እንቅስቃሴ ወደ ኃላ እየተሳበ የአማካይ መስመሩን እንዲያግዝ ተደርጓል።

በእንቅስቃሴ እና በግብ ሙከራ ተቀዛቅዞ የታየው ሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ በመከላከያ አጋማሽ ላይ የተጠናቀቀ ነበር። አማካይ መስመር ላይ በዳዊት እስጢፋኖስ መሪነት ተረጋግተው ኳስ ለመያዝ ጥረት ሲያደርጉ ይታዩ የነበሩት መከላከያዎች ለብቸኛው አጥቂ ፍፁም ገብረማርያም የሚልኳቸው ኳሶች ስኬታማነት እምብዛም ነበር። በአንፃሩ እንደመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሁሉ ወደ ሳጥን በሚልኳቸው ረጃጅም ኳሶች ተጭነው መጫወት የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በርካታ የግብ ዕድሎችን ባይፈጥሩም ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተደጋጋሚ ያገኟቸው ከነበሩ የማዕዘን ምቶች መሀልም በአንደኛው ተሳክቶላቸው አቻ መሆን ችለዋል። 62ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምቱ የተነሳውን ኳስ በግንባሩ ወደ ግብነት የቀየረው ደግሞ ግዙፉ የመስመር አጥቂ ኦዝቫልዶ ታቫሬዝ ነበር። ከግቡ በኃላም በሀይሉ አሰፋ ከርቀት ያደረገው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ተጠቃሽ የነበረ ሌላ ሙከራ ነው።

በመቀጠል ጨዋታውን ለመከላከያ ይበልጥ የሚያከብድበት ክስተት 70ኛው ደቂቃ ላይ ተፈጥሯል። በተደጋጋሚ ጉሽሚያዎች ላይ ሲሳተፍ የቆየው ዳዊት እስጢፋኖስ አስቻለው ታመነን በክርኑ በመማታት ሶስተኛው በቀይ ካርድ ከሜዳ የተወገደ ተጨዋች ሆኗል። በቀሩት 20 ደቂቃዎች ስምንት የሜዳ ላይ ተጨዋቾችን ይዘው ለመቀጠል የተገደዱት መከላከያዎች ከአራቱ ተከላካዮች በተጨማሪ የአብዱልከሪምን የቀኝ መስመር እንቅስቃሴ እንዲቆጣጠር ቴዎድሮስ ታፈሰን እንደ አምስተኛ የግራ መስመር ተከላካይ በመጠቀም እና የተጋጣሚያቸውን ተሻጋሪ ኳሶች በመከላከል ተጠምደው አሳልፈዋል። 

የአማኑኤል ተሾመ እና ሳሙኤል ሳሊሶ መግባት ቡድኑ አልፎ አልፎ የሚታዩ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን እንዲጠቀም ያለመ ቢመስልም መከላከያዎች ወደ ሮበርት ለመቅረብ ሌላ ዕድል ሳያገኙ ነበር ጨዋታው የተጠናቀቀው። አስቻለው ግርማ በግንባር እንዲሁም አብዱልከሪም ኒኪማ እና አብኩልከሪም መሀመድ ከርቀት ካደረጓቸው ሙከራዎች በቀር ሌላ የመጨረሻ ዕድል መፍጠር ያልቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶችም ሁለተኛ ግብ ማግኘት አልቻሉም። አቡበከር ሳኒ እና ምንተስኖት አዳነ ተቀይረው በመግባት ያደረጉት እንቅስቃሴም ለፈረሰኞቹ ግብ ማስገኘት ሳይችል ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል። በውጤቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊጉን መምራት የሚችልበትን አጋጣሚ ለመቐለ አሳልፎ ሲሰጥ መከላከያም በሊጉ ወገብ ላይ ሆኖም የመውረድ ስጋቱ እንዳይለቀው ሆኗል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ – መከላከያ
በጨዋታው የነበረው ትግል ጥሩ ነው። ካለንበት ቀጠና ለመውጣት እያንዳንዱ ጨውምታ ለኛ አስፈላጊ ነው። ነጥብ ለማግኘት ካለው ጉጉት አንፃር እና ጊዮርጊሶች ተጭነው የተጫወቱበት ደቂቃ እንደማመዘኑ የሚቻለንን ነገር አድርገናል። አጠቃላይ ፉክክሩ ጥሩ የሚባል ነው። ወደ ኃላ ማፈግፈጋችን አደጋ ነበረው። የኔም ፍላጎት አልነበረም። ቀድመን እንደማግባታችን ይበልጥ ተጭነን ብንጫወት ጫናው እነሱ ላይ ነበር ሚሆነው። ነገር ግን ድሬደዋ ላይ ነጥብ ጥለናል አሁንም ላለመጣል ውጤቱን ወደ ማስጠበቁ አመዝነናል። 

አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

1-0 እየተመታን የጀመርነው ጨዋታ ነው። ከዛ በኃላ ግን ሜዳ ውስጥ የነበረው አንድ ቡድን ብቻ ነው። በርካታ የግብ ዕድሎችን ፈጥረናል በቀላሉ ሶስት እና አራት ግቦችን ማስቆጠር እንችል ነበር። ሙሉ ለሙሉ ከመከላከያ የተሻልን ነበርን።  ሜዳው ምቹ ባይሆንም ተጨዋቾቼ የሚችሉትን አድርገዋል። በርካታ ሙከራዎችን ብናደርግም አንዳንዴ ዕድለኛ መሆንንም ይጠይቃል። ሮበርት በጨዋታው ላይ ምንም ሚና አልነበረውም። እግር ኳስ ነውና አንዳንዴ ያጋጥማል።