ለአሰልጣኝ ሥዩም አባተ ህክምና የገቢ ማሰባሰቢያ ጨዋታ ተደርጓል

ለአሰልጣኝ ሥዩም አባተ ህክምና ገቢ የማሰባሰብ አላማ ይዞ የተዘጋጀው ጨዋታ ትላንት በአአ ስታድየም ተከናውኗል።

ዋናው መርሐ ግብር ከመጀመሩ አስቀድሞ ኑሯቸውን በዱባይ ያደረጉ የቀድሞ ተጫዋቾች ከቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ጋር ባደረጉት ጨዋታ የዱባይ ኮሚኒቲ 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

በመቀጠል ኢትዮጵያ ቡናን ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገናኘው ጨዋታ ሲካሄድ ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ የሻላ የጤና ቡድን ለሥዩም አባተ ህክምና የሚውል 20,000 ብር ለተቋቋመው ኮሜቴ ፀኃፊ አስራት ኃይሌ አበርክተዋል። በሞት ከተለየ አንድ አመት የደፈነውን የቀድሞ ታላቅ አጥቂ አሰግድ ተስፋዬን በህሊና ፀሎት በማሰብ በተጀመረው ጨዋታ የለጣው ዝናብ የጨዋታውን ፍሰት ሲጎዳው ከመታየቱም ባሻገር በርካታ ተመልካች ወደ ስታድየም ከመምጣት ሲያግደውም ተስተውሏል።

ኢትዮጽያ ቡና በ18ኛው ድቂቃ አስቻለው ግርማ ባስቆጠራት ግብ ቀዳሚ በመሆን የመጀመርያው አጋማሽ ሲጠናቀቅ በ71ኛው ደቂቃ ኃይሌ እሸቱ ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ግብ አስቆጥሮ አቻ መሆን ችለዋል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜም በአቻ ውጤት በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርተው ኢትዮጵያ ቡና 5-4 አሸናፊ ሆኗል።

ከጨዋታው በኋላ ለዝግጅቱ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላደረጉት አካላት የምስክር ወረቀት በቀድሞ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ንጉሴ ገብሬ አማካይነት ሲበረከትላቸው በመቀጠል ለዱባይ ኮሚኒቲ እንዲሁም ለኢትዮጽያ ቡና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቷል።

ስለገቢ ማሰባሰቢያ ውድድሩ የኮሚቴው ፀኃፊ አቶ አስናቀ ደምሴ የሚከተለውን ብለዋል
” ይህ ዝግጅት የታሰበው ሥዩም አባተን ለበለጠ ጤንነት ለማብቃት ነው። በአሁኑ ሰዓት የሥዩም ጤንነት ከበፊቱ የተሻለ ነው። ነገር ግን ለሚቀጥለው ህክምና አንድ ሚሊዮን ብር ተጠይቀናል። ይህን ለማሟላት እንዲ አይነቱን ፕሮግራም አዘጋጅተናል።

” እንደሚታየው የዛሬው ዝግጅት የታሰበውን ያህል ነበር ማለት አልችልም። ነገር ግን የአየር ሁኔታው ሊሆን ይችላል ሰውን ያስቀረው። ለታደመው የስፖርት ቤተሰብ ግን በጣም እናመስግናለን።

” በቀጣይ ከኢትዮጽያ ክለቦች ጋር በመቀራረብ እንሰራለን። ከዛም ለስፖርቱ ቅርብ ከሆኑት ባለሀብቶች ጋር በቅርበት እንሰራለን።

” ከጎናችን ለነበሩት ሁሉ እናመስግናለን። የሥዩምን ህይወት ወደተሻለ እርምጃ ለማሻገር አሁንም የስፖርቱ ቤተሰብ ከጎናችን እንዲሁን ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።”