አዲሱ ፌዴሬሽን የመጀመሪያውን ስብሰባ ዛሬ ጠዋት ላይ አከናውኗል

አቶ ኢሳይያስ ጂራ በፕሬዝዳንትነት ከተመረጡ በኋላ ከስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ጋር የመጀመሪያውን ስብሰባ ማከናወን ችለዋል።

በዛሬው ስብሰባ ሁለት ነጥቦች ላይ ውይይት ተደርጓል። የመጀመሪያው ውይይት የዚህ ዓመት ቀሪዎቹ ውድድሮች በምን መልኩ ይጠናቀቅ በሚል የነበረ ሲሆን ውድድሩ በጥንቃቄ መካሄድ አንዳለበት ካሳሰቡ በኋላ የሊጉ ኮሚቴ ኃላፊ ከሆኑት አቶ አበበ ገላጋይ ጋር በመሆን ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን እና አቶ ቻን ጋትኮት በጋራ እንዲሰሩ ተመድበዋል። የውድድሩ አካሄድ ግልፅነት እንዲኖረው አሳስበው የትኛውም ቡድን ማሸነፍ ያለበት በእግር ኳሳዊ መንገድ መሆን እንዳለበት በመግለፅ ሁሉም በስራው ተጠያቂ እንደሚሆን ገለፀዋል። ቀሪ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በተለይም ክብደት እና ጥንቃቄ የሚስፈልጋቸው የቻምፒዮንነት እና ላለመውረድ የሚደረጉ ጨዋታዋች እና ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት የሚደረጉ ወሳኝ ጨዋታዎች በሙሉ በካሜራ እንደሚቀረፁ መግለፃቸውን ሰምተናል።

በሁለተኛው የውይይት አጀንዳ የነበረው በአሁኑ ሰዓት አሰልጣኝ የሌለውና በነጥብ ውድድር ጊዜ ብቻ ብቅ የሚለው የኢትዮጽያ ብሔራዊ ቡድን ጉዳይ ነው። በዚህ ውይይት ብሔራዊ ቡድኑ በቋሚነት መኖር እንዳለበት እና ከስራ አስፈፃሚው መዋቀር ውስጥ መውጣት እንዳለበት የተገለፀ ሲሆን ዝርዝር መዋቅሩ እንዴት መሆን እንዳለበት የጥናት ስራን የመስራት ኃላፊነት ለአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው መሰጠቱ ታውቋል። ጥናቱ በቀጣዮቹ 15 ቀናት ተጠንቶ ይቀርባልም ተብሏል።