ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ በሜዳው መቐለን በማሸነፍ ከወራጅነት ስጋት የመራቅ ጥረቱን አሳምሯል

በ25ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ከተካሄዱ ጨዋታዎች መካከል በወራጅነት ስጋት ውስጥ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ በቻምፕዮንነት ፉክክር ውስጥ የሚገኘው መቐለ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። 

ድሬዳዋ ከተማ በ24ኛው ሳምንት ወደ ጎንደር ተጉዞ አቻ ከተለያየው ስብስብ መካከል በጉዳት ያልነበረው ሐብታሙ ወልዴን በሳውሬል ኦልሪሽ ምትክ በመጠቀም ወደ ሜዳ ሲገቡ በመቐለ ከተማ በኩል ሀዋሳ ከተማን ሜዳው ላይ ካሸነፈው ቡድን የ3 ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ለብሄራዊ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታ ወደ ሀገሩ አቅንቶ የነበረው ግብ ጠባቂው  ፊሊፕ ኦቮኖን በሶፈንያስ ስይፉ፣ አቼምፓንግ አሞስን በዳንኤል አድሓኖም እንዲሁም ከቅጣት የተመለሰው አመለ ሚልኪያስ በያሬድ ከበደ ምትክ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ተካተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

በፌዴራል ዳኛ ወልዴ ንዳው መሪነት በድንገት ከዚህ አለም በሞት ለተለዩት አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ለማሰብ በመቐለ ከተማ ደጋፊዎች የተጋጀው ባነርን ይዘው በሜዳው በመዞር በተጀመረው ጨዋታ አንደኛ አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ድሬድዋ ከተማዎች ተጭነው መንቀሳቀስ ችለዋል። አትራም ኩዋሜ በ5ኛው ደቂቃ ከወስኑ ማዜ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ የመታትና ኢላማዋን ያልጠበቀችው ሙከራ በድሬ በኩል የመጀመርያ አጋጣሚ ስትሆን በ10ኛው ከርቀት የተገኘውን ቅጣት ምት ጋቶች ፓኖም በቀጥታ አክርሮ በመምታት ሞክሮ የድሬ ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋ በቀላሉ ያዳነበት ኳስ በመቐለ በኩል ቀዳሚው አጋጣሚ ነበር።

በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያሳይ የነበረው ሱራፌል ዳንኤል ከመስመር በጥሩ ሁኔታ  ያሻገረለትን ኳስ አትራም በቀጥታ ወደ ጎል ቢሞክርም ወደ ውጭ ሲወጣ በ17ኛው ደቂቃ  ጋቶች ፓኖም ያሻገረውን ኳስ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በጥሩ ሁኔታ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ከእነዚህ ሙከራዎች በኋላ በሁለቱም ቡድን ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን አልፎ አልፎ ከሚደረጉ ሙከራዎች ውጪ እምብዛም የሚጠቀስ የግብ አጋጣሚ ሲፈጠር አልተስተዋለም። በአንፃራዊነት ወደ ጎል በመቅረብ የተሻሉ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በ23 ድቂቃ ከዮሴፍ ዳሙዬ የተሻገረለትን ኳስ ሀብታሙ ወልዴ የሞከረው እና በ28 ደቂቃ ሱራፌል ዳንኤል ከግራ መስመር ወሰኑ ያሻገረለትን ኳስ ሞክሮ የመቐለው ግብ ጠባቂ ኦቮኖ በቀላሉ የተቆጣጠረበት የሚጠቀሱ የግብ አጋጣሚዎች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ ድሬዎች ጨዋታውን አሸንፈው ለመውጣት የነበራቸው ተነሳሽነት የሚጠቀስ ሲሆን መቐለዎች በአንፃሩ የተቀዛቀዘ እና በመከላከል ላይ ያመዘነ እንቅስቃሴ አድርገዋል። በ47ኛው አትራም ኩዋሜ አክርሮ ወደ ግብ ሞክሮ ወደ ውጪ በወጣበት ሙከራ የመጀመርያ አጋጣሚ መፍጠር የቻሉት ድሬዎች አንፃራዊ ብልጫ ቢኖራቸውም ግብ እስኪያስቆጥሩ ድረስ የጠራ የግብ ሙከራ ማድረግ ግን አልቻሉም።

በ69ኛው ደቂቃ ዘላለም ኢሳይያስን ቀይሮ የገባው ዘነበ ከበደ በቀኝ ከኩል ያሻገረውን ኳስ አትራም ኩዋሜ በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ወደ ጎል ሲልካት የመቐለው ግብ ጠባቂ ኳሷን ሲተፋት በቅርበት የነበረው ያሬድ ታደሰ ወደ ግብ መትቶ በድጋሚ በተከላካዮች ተደርቦ ሲመለስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ሱራፌል ዳንኤል አክርሮ በመምታት ወደ ጎልነት ቀይሮ ድሬዳዋ ከተማን መሪ አድርጓል።

ከጎል መቆጠር በኋላ ድሬዳዋ ከነማዎች ይበልጥ ተጭነው መጫወት ሲችሉ በተለይ በ71ኛው ደቂቃ ያሬድ ታደሰ በግል ጥረቱ ከመሀል ይዞ የሄደው ኳስ ጥሩ የጎል አጋጣሚ ቢፈጥርለትም የመታው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። በመቐለ ከተማ በኩልም በ85ኛው ደቂቃ አመለ ሚልኪያስን ቀይሮ የገባው መድኃኔ ታደሰ ከመሀል ሜዳ በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ ሞክሮ የድሬዳዋ ግብ ብጠባቂ ሳምሶን አስፋ በቀላሉ የተቆጣጠረው ኳስ የሚጠቀሱ የጎል ሙከራዎች ነበሩ።

ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ የምስራቁ ክለብ ነጥቡን 29 በማድረስ ከመውረድ ስጋት ራሱን የማላቀቅ ጥረቱን ሲገፋበት መቐለ ከተማ ተከታዩኑ ነጥብ መጋራታቸውን ተከትሎ መሪነቱን የሚያሰፋበትን አጋጣሚ መጠቀም ሳይችል አንደኛ ደረጃን ለጅማ አስረክቧል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ስምኦን ዓባይ – ድሬዳዋ ከተማ

ጨዋታውን እንደተመለከታቹት ከሞላ ጎደል ስኬታማ ነን ብዬ አስባለው። ተጋጣሚያችን መቐለ ከተማ ሊጉን የሚመራ ቡድን ነው፤ በታክቲክ ረገድም ጠንካራ ነው። ስለዚህ እንዲህ አይነት ቡድን ጥንቃቄ አድርገህ ነው መግጠም ያለብህ። ሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ውጪ እኛ በምንፈልገው መንገድ ጨዋታውን ማካሄድ ችለናል። ሳቢ ጨዋታ ላንጫወት እንችላለን፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ የምንጫወታቸው ጨዋታዎች ለኛ ሪስክ አላቸው። ስለዚህ ያንን ከባድ ሪስክ መወሰድ አንፈልግም። ከእንደዚህ አይነት ከባድ ቡድን ጋር ስትጫወት ተጠንቅቀህ ነው መጫወት ያለብህ። ዛሬ ቡድናችን እንደ በፊቱ አልነበረም በመሆኑም በልጆቹ ብቃትና ጥረት ታክቲካችንን ተግብረን ወጥተናል ብዬ አስባለው።

አስልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ – መቐለ ከተማ

በመጀመሪያ ደጋፊውን ላመሰግን እወዳለሁ። ኳስ አፍቃሪ ህዝብ ነው። በድጋፍ ደረጃ ለሁለታችንም እኩል ነበር ማለት እችላለው። ሜዳ ላይ የታዩ አንዳንድ የዳኝነት ውሳኔዎችለደጋፊ እንተዋለን። ከዚህ ውጪ ድሬዳዋ ከኛ ቡድን በጨዋታ ፍላጎት የተሻለ ነበር። 50/50 ኳስን በማሸነፍ፣ የአየር ላይ ኳስን በማሸነፍ እንዲሁም እንደማስበው የሜዳ ጨዋታ ወሳኝ መሆኑ እናም የበለጠ ውጤቱን የሚፈልጉት መሆኑን አሳይተዋል። በልጠውናል፤ ያ በመሆኑም አግብተው አሸንፈውናል። እንኳን ደስ አለችሁ ልላቸው እወዳለው። አመሰግናለው!