ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ይበልጥ ያስጠጋውን ጣፋጭ ሶስት ነጥብ አሳክቷል

በ25ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ  ዛሬ ሶዶ ላይ ኢትዮጵያ ቡና ወላይታ ድቻን 1 – 0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ሊጉ ቻምፒዮንነት ፉክክር ሲቀላቀል በአንፃሩ ባለሜዳዎቹ ድቻዎች ወደ ስጋት ወረዳ ተጠግተዋል፡፡

በዕለቱ ጨዋታ የሶዶ ስታዲየም የሰሞኑ ዝናብ ያጨቀየው በመሆኑ ኳስ ለማንሸራሸር ምቹ አለመሆኑ እየታወቀ በተመደቡት ኮምሽነሮች እና ዳኞች ሜዳው ለጨዋታው ብቁ ነው መባሉ አብዛኛውን የእግር ኳስ ቤተሰብ አስገረመ ነበር።

በኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር የጀመረው ጨዋታ ሁለቱም ተጋጣሚዎች ከጨዋታው የሚገኘው ነጥብ አስፈላጊነትን በመገንዘብ በሚገኙ አጋጣሚዎች በማጥቃት ላይ ያመዘነ አጨዋወትን ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ባለሜዳዎቹ ድቻዎች ባሳለፍነው ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ነጥብ ከተጋሩበት ስብስብ ውስጥ የሶስት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን ጉዳት ላይ በሚገኘው ጃኮ አራፋት ፣ ዮናታን ከበደ እና ተስፋ ኤልያስ ምትክ ደግም በቀለ ፣ ተመስገን ዱባ እና እሸቱ መናን ተክተዋል። ኢትዮጲያ ቡና በአንፃሩ የአንድ ተጨዋች ለውጥ ያደረገ ሲሆን ኤልያስ ማሞን ወደ ተጠባባቂ ወንበር በመመለስ በምትኩ አጥቂው ባፕቲሰቴ ፋዬን ወደ መጀመሪያ አስላለፍ አምጥቷል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ቡናዎች የሜዳው መጨቅየት ሳያግዳቸው ከባለሜዳዎቹ በተሻለ መልኩ ወደተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ጥሩ 45 ደቂቃ ያሳለፉ ሲሆን ፤ ድቻዎች ግን የጠራ የጨዋታ ስትራቴጂ ሳይኖራቸው በእንቅስቃሴም ተዳክመው ታይተዋል፡፡ በዚሁ ጊዜ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች ፈጣን እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን ድቻዎች በበዛብህ መለዮ እና እዮብ አለማየው ኳስን መሃል ለመሃል አንዲሁም ወደ ሁለቱ ክንፎች ለማድርስ ጥረት ቢያደርጉም ያልተሳኩ ቅብብሎቻቸው ወደ ቡና የግብ ክልል መጠጋት እንዲቸግራቸው አድርገዋል። በነዚህ ደቂቃዎች ውስጥ ግን ቡናዎች የተሻለ ወደ ጎል በመድረስ ዕድሎችን ሲፈጥሩ ተስተውለዋል። በተለይም በ10ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት የተገኘውን ቅጣት ምት አቡበከር ነስሩ ሞክሮ ወደ ላይ የወጣበት እና በ15ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳኑሚ በግራ መስመር ጥሩ አርጎ የሞከረው ኳስ በቀላሉ በኢማኑኤል ፌቮ ቢያዝበትም አጋጣሚዎቹ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።


በኳስ ቁጥጥር ተበልጠው የነበሩት ድቻዎች በመጀመርያ ሙከራቸው 32ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር እዮብ አለማየሁ ወደ ጎል የላካት ኳስ በግቡ አናት ስትሄድ ከአምስት ደቂቃዎች በኃላ ደግሞ በግራ በኩል የተገኘውን ቅጣት ምት ያሬድ በጥሩ ሁኔታ ቢያሻማም ማንም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በመቀጠልም 39ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልሰመድ አሊ ከርቀት አክርሮ የሞከረውን ኳስ ሀሪሰን ከተፋው በኃላ በፍጥነት በመነሳት በእግሩ ወደ ወጪ ያወጣት ሁኔታ ከድቻ የጠሩ የጎል አጋጣሚዎች መሀከል የሚጠቀስ ነበር። በዚህ ክፍለ ጊዜ ቡናዎች በሁለቱም ክንፎች በሳሙኤል ሳኑሚ እና ሚኪያስ መኮንን አማካኝነት ለግዙፉ አጥቂ በተደጋጋሚ ኳሶችን ሲጥሉ የቆዩ ሲሆን ጨዋታውን ያሸነፉበት ብቸኛ ጎልም በተመሳሳይ አኳኃን የተገኘ ነበር። ሳሙኤል ሳኑሚ በ41ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ወደ ግብ የላካትን ኳስ ኢማኑኤል ፌቮ ሲጨርፋት ከጀርባ የነበረው ሚኪያስ መኮንን በፍጥነት ወደ ድቻ ግብ ክልል አዙሮ ለአቡበከር ነስሩ አመቻችቶ ሰጥቶት አቡበከር በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ ልኳት የኢማኑኤል ፌቮ የማዳን ጥረት ሳይሳካ ኳሷ ከመረብ ጋር ተገናኝታለች፡፡ ከጎሏ መቆጠር በሁዋላ የደጋፊ ጫና ውስጥ የገቡ የሚመስሉት ድቻዎች ለተቆጠረባቸው ጎል ምንም አይነት አፀፋ ሳይሰጡ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ድቻዎች ግብ ለማግኘት እና ነጥብ ለመጋራት ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ ተጋጣሚያቸው ላይ ጫና ለመፍጠር በማሰብ ከአራቱ ተካላከዮች መሀከል ያሬድ ዳዊትን ወደፊት ተጠግቶ እንዲጫወት በማደረግ ወደ 3-4-3 የሚቀርብ አሰላለፍ መጥተዋል። በተቃራኒው በመጀመርያ አጋማሽ የነበራቸው የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ያጡት ቡናማዎቹ ብቸኛዋን ጎል ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው በመጫወት እና አልፎ አልፎ በመስመር ከሚጣሉ ኳሶች መነሻነት የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከሩበት አጋማሽ ነበር፡፡

በዚህ ክፍለ ጊዜ ድቻዎች በረጃጅም ኳሶች ወደ ቡና የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ያደረጉ ሲሆን በተለይም ከመጀመርያው አጋማሽ ይልቅ ጥሩ የነበረው በዛብህ መለዮ በግራ መስመር ለያሬድ ዳዊት የሚያሻግራቸው እና ያሬድ በረጅሙ ወደ ውስጥ የሚጥላቸው አንዲሁም እሸቱ መና አልፎ አልፎ ከተመስገን ዱባ ጋር በመጣመር ወደ ግብ የሚልካቸው ረጃጅም ኳሶች አደገኛ ሆነው ቢታዩም ድንቅ የነበሩት የቡና የመሃል ተከላካዮች ቶማስ ስምረቱ እና ክሪዚስቶም ንታምቢ በቀላሉ ከግብ ክልላቸው ሲያርቁባቸው ታይተዋል።


ድቻዎች በዚህ የጨዋታ ሂደት ውስጥ የሚፈጥሯዋቸውን ክፍተቶች በመጠቀም በከፍተኛ ተነሳሽነት ሲጫወቱ የነበሩት ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች እያሱ ታምሩ እና ኃይሌ ገ/ትንሳይ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ወደ ድቻ የግብ ክልል ኳስ ለማድረስ ሲጥሩ ተስተውለዋል፡፡ ባለሜዳዎቹ እንደነበራቸው የበላይነት በ49ኛው ደቂቃ በዛብህ መለዮ ከርቀት ከሞከረው አና በ73ኛው ደቂቃ  እዮብ አለማየው አግኝቶት ወደ ግብ ለመምታት ሲጥር ካመለጣችው አጋጣሚ በቀር ምንም አይነት የጠራ የጎል ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ይህንን ጫና በይበልጥ ለማስቀጠል 53ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ ብርሃኑን በተመስገን ዱባ እንዲሁም 80ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳን በዳግም በቀለ ቀይረው ቢያስገቡም የታስብውን ውጤት ማግኘት አልቻሉም። በአንጻሩ ቡናዎች ደቂቃ በገፋ ቁጥር ውጤት ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ የግቧን ባለቤት አቡበከር ነስሩን በተከላካዩ ወንድይፍራው ጌታሁን ፣ ኃይሌ ገ/ትንሳይን በአስራት ቱንጆ አንዲሁም ሚኪያስ መኮንንን በአክሊሉ ዋለልኝ ቀይረው በማስግባት የዲቻን ጫና ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል። እልህ አስጨራሽ በሆነ ምልኩም ወሳኙን ሶሰት ነጥብ ይዘው መመለስ ችለዋል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ዲድዬ ጎሜስ – ኢትዮጵያ ቡና

የዋንጫው ፉክክር ላይ ለመቆየት ይህ ሶስት ነጥብ በጣም ወሳኛችን ነበር። ለዚህም ጠንክረን ነበር የሰራነው ፤ ለተጨዋቾቼ  ‘እኛ ቡናዎች ነን የኢትዮጲያ ቡና ተጨዋች ተስፋ መቁረጥ የለበትም’ ብዬ ነግሬያቸው ነበር። እናም ጨዋታው ላይ ያላቸውን ሲሰጡ ነበር ፤ በጣም ደስተኛ ነበርኩኝ። የዛሬው ቡድኔ በጣም በጥብቅ የመከላከል ባህሪ ነበረው። ይሄ ደሞ ሆን ተብሎ የተነደፈ ስልት ነበር። አንዲህ አይነት አጨዋወት መልመድ እና ለወደፊትም መጠቀም ያለብን ነገር ነው። በተለይ ጎል አግብትን ስንመራ ውጤት ለማስጠበቅ የተነደፈ ስልት ነበር፡፡

አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃ – ወላይታ ድቻ

ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር። ያው ቡና በጣም ጠንካራ እንደመሆኑ መጠን እኛም ተጋድሎ አድርገናል። ቀላል የሚባል አይደልም እንደሚታዩት ከጭቃው ጋር ተገናኝቶ አስቸገሪ አድርጎብናል።  ዕድለኞችም አልነበርንም። ብዙ አጋጣሚዎችን ፈጥረናል ፤ የአጨራረስ ድክመት አለብን። መቅረፍ ያልቻልነው ነገር ነው። ባጠቃላይ ጥሩ ነን ፤ እንቀስቃሴው አያስከፋም፡፡ በቀጣይ መስራት ያለብንን ነገር አስተካክልን ጎል የማግባት ችግራችንን መቅረፍ አለብን።