ጋና 2018 | ሉሲዎቹ በመጀመርያው ጨዋታ በአልጄርያ ሽንፈት አስተናግደዋል

በጋና አስተናጋጅነት በ2018 ለሚካሄደው የቶታል አፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻው የማጣርያ ዙር ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከአልጄርያ ጋር ያደረገውን የመጀመርያ ጨዋታ 3-1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።

በአልጀርሱ ስታደ 5 ጁላይ ስታድየም በጣት የሚቆጠሩ ተመልካቾች ፊት በተደረገው ጨዋታ በኢትዮጵያ በኩል ከወር በፊት በመጀመርያው ዙር ማጣርያ ሊብያን አአ ስታድየም ላይ 7-0 ከረታው ስብስብ መካከል በቀኝ ተከላካይ ስፍራ ላይ አለምነሽ ገረመው ብዙዓየሁ ታደሰን ተክታ ስትሰለፍ በጉዳት ወደ ስፍራው ባላቀናችው መስከረም ካንኮ ምትክ ታሪኳ ደቢሶ የመሰለፍ እድል አግኝታለች።

ሉሲዎቹ የተሻለ አጀማመር ባደረጉበት የመጀመርያው አጋማሽ ጎል እስከሚያስቆጥሩ ድረስ በተጋጣሚ ሜዳ ላይ በማመዘን አንፃራዊ ብልጫን ማስመዝገብ ችለው ነበር። በ6ኛው ደቂቃ መሠሉ ከግራ መስመር የተገኘውን ቅጣት ምት በቀጥታ በመምታት ሞክራ በተከላካይ የተመለሰባት ኳስ የመጀመርያ አጋጣሚ ሲሆን ከአንድ ደቂቃ በኋላ ከማዕዘን የተሻማው ኳስ በተከላካዮች ሲመለስ ሎዛ አበራ አግኝታ ብትመታም በግቡ አናት ወደ ውጪ ወጥቶባታል። 
በ15ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ሕይወት ደንጊሶ በረጅሙ ያሻማችውን የቅጣት ምት ከተከላካዮች ተነጥላ በነፃ አቋቋም ላይ የነበረችው ረሒማ ዘርጋ በግንባሯ በመግጨት ኢትዮጵያን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች። 

ሆኖም የኢትዮጵያ መሪነት የቆየው ለ3 ደቂቃዎች ብቻ ነበር። በ18ኛው ደቂቃ መሪየም ቤንላዛር ከቀኝ መስመር ያሻገረችውን ኳስ መዲና ራምዳኒ ከመሠሉ እና ግብ ጠባቂዋ ንግስት ቀድማ በግንባሯ በመግጨት ባለሜዳዎቹን አቻ አድርጋለች። ከዚህ ጎል መቆጠር በኋላ የሉሲዎቹ የተከላካይ መስመር ድክመት ይበልጥ ጎልቶ ወጥቷል። የቅብብል ስህተቶችን የሚሰራ እና በቀላሉ የሚታለፍ ከመሆኑም ባሻገር ከአማካዮች በቂ ሽፋን ማግኘት አለመቻሉ ይበልጥ ተጋላጭ አድርጎታል። በዚህም የተከላካይ መስመር ተጫዋቾቹ የሚያገኟቸውን ኳሶች በረጅሙ ሲያወጡ ተስተውሏል።

በ31ኛው ደቂቃ ከኳስ ጋር ተከላካዮችን ስታስጨንቅ ያመሸችው ነኢማ ቦውሄኒ ከቤተልሔም ቀድማ ያገኘቸውን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ መትታ ኢላማውን በመሳት ወደ ውጪ ሲወጣ በ32ኛው ደቂቃ ከአማካዮች የቅብብል ስህተት የተገኘውን ኳስ ነኢማ ቦውሄኒ ከመሪየም ቤንላዛር ጋር ተቀባብላ ወደ ሳጥን ይዛ በመግባት ግብ ጠባቂዋን አልፋ ያሻገረችውን አሲያ ሲዶም ወደ ግብነት ለውጣ አልጄሪያን ወደ መሪነት አሸጋግራለች።

በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አልጄርያዎች የግብ ልዪነቱን የሚያሰፉባቸው አጋጣሚዎች መፍጠር ችለዋል። በተለይም በ34ኛው ደቂቃ በረጅሙ ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ ማስቆጠር ቢችሉም ረዳት ዳኛዋ ከጨዋታ ውጪ በሚል የሻረችው እንዲሁም በጨዋታው እጅግ ድንቅ የነበረችው ነኢማ ቦሄኒ በ42ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ግቡ በማጥበብ አመቻችታ የመታችውና መሠሉ አበራ በግሩም ሁኔታ ተደርባ ያወጣችው ኳስ የሚጠቀሱ አጋጣሚዎች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ ሉሲዎቹ የበለጠ ተዳክመው ሲቀርቡ አንድም ሙከራ በዚህ ክፍለ ጊዜ ማድረግ ካለመቻላቸው በተጨማሪ የአጥቂ መስመሩ ከአማካይ ክፍሉ ተነጥሎ አምሽቷል። እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ በራሱ ላይ አደጋ ሲጋብዝ በተደጋጋሚ የታየው የተከላካይ መስመሩም በተደጋጋሚ በሚሰራው ጥፋት በሚሰጡ ቅጣት ምቶች ሲፈተን ተስተውሏል። 

በ49ኛው ደቂቃ ነኢማ ቦሄኒ ከግራ መስመር ያሻገረችውን ኳስ መሪየም ቤንላዛር በቀጥታ መትታ ንግስት መዓዛ ስታድንባት በ56ኛው ደቂቃ ደግሞ ቤንላዛር ያሻማችውን ቅጣት ምት ቦሄኒ በግንባሯ ገጭታ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶባታል። በ67ኛው ደቂቃ በድጋሚ ቤንላዛር ከግራ መስመር ያሻማችውን የቅጣት ምት ንግስት መዓዛ ብትመልሰውም አጠገቧ የነበረችው ፋቲማ ሴኮውኔ ተደርባ ወደ ግብነት በመለወጥ የአልጄርያን መሪነት ወደ ሶስት ከፍ አድርጋለች። 

ከጎሉ መቆጠር በኋላ በቀሩት ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ከሚቆራረጡ ቅብብሎች በቀር ግልፅ የግብ እድል ያልተፈጠረ ሲሆን አልጄርያዎች ከቆሙ ኳሶች እንዲሁም በቦሄኒ እና ቤንላዛር የግል ጥረት የኢትዮጵያን የተከላካይ መስመር ፈትነዋል። በኢትዮጵያ በኩል ተቀይራ የገባችው ሴናፍ ዋኩማ በግል ጥረቷ ኳስ ወደ አጥቂ መስመሩ ይዛ ለመጠጋት ብትሞክርም የመጨረሻዎቹ ኳሶች ከጨዋታ ውጪ ሲሆኑ ተስተውሏል።

ጨዋታው በዚህ መልኩ 3-1 በሆነ ውጤት ሲጠናቀቅ የመልሱ ጨዋታ በመጪው እሁድ በአዲስ አበባ ስታድየም የሚከናወን ይሆናል። በድምር ውጤት የሚያሸንፈው ብሔራዊ ቡድንም የጋና አፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ትኬት የሚቆርጥ ይሆናል።