አዲሱ የፌዴሬሽኑ አመራር ከፕሪምየር ሊግ ዳኞች ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ ይዟል

በአፋር ሰመራ ለቀጣዩ አራት አመታት እግርኳሱን በበላይነት ለመምራት የተመረጡት ፕሬዝደንቱን ጨምሮ አስር የስራ አስፈፃሚ አባላት ባሳለፍነው ማክሰኞ የመጀመርያ መደበኛ ስብሰባቸውን በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር እና የስራ ክፍፍል በማድረግ ስራቸውን መጀመራቸው ይታወቃል ።

የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ሊጠናቀቅ የአምስት ጨዋታ ዕድሜ በሚቀረው በአሁኑ ወቅት ለዋንጫ የሚደረገው ፉክክር እና ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ ማን የውድድሩ አሸናፊ እና ወራጅ ሊሆን እንደሚችል ቁርጡ አለየለትም። ከዚህ በኋላ የሚደረጉ ጨዋታዎች ሁሉ ከፍተኛ ቁጥጥር እና ክትትል የሚያስፈልገው መሆኑን ከግምት ያስገባው የፌዴሬሽኑ የተለያዩ ውሳኔዎችን የወሰነ ሲሆን በተለይ ከዚህ በኋላ ያሉት ጨዋታዎች በሙሉ ጨዋታዎቹ በሚደረጉበት ቦታ በፌዴሬሽኑ ሙሉ ወጪ የቪዲዮ ቀረፃ እንዲደረግ ውሳኔ አሳልፏል። ከዚህ በተጨማሪ የውድድሩ ወሳኝ አካላት የሆኑትን ዳኞች ቀሪ ጨዋታዎችን ከምንም ነገር በፀዳ መልኩ በትክክል ጨዋታዎችን መርተው መውጣት እንዳለባቸው አቅጣጫ ለመስጠት እና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር የፕሪምየር ሊግ ዳኛ ብቻ ለሆኑት ከ100 በላይ ዳኞችን የፊታችን ቅዳሜ ከጠዋቱ 03:00 ጀምሮ በቸርችል ሆቴል ለማነጋገር ቀጠሮ መያዙ ታውቋል።