የሉሲዎቹ የተጨዋቾች ተገቢነት ክስ…

 በ2018 በጋና አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ የሴቶች ዋንጫ የመጨረሻ ማጣሪያ ወደ አልጀርስ አቅንተው 3-1 የተሸነፉት ሉሲዎቹ ከአልጀርሱ ጨዋታ አስቀድሞ የተጨዋች ተገቢነት ክስ ማስያዛቸው ይታወሳል።

የክሱ ሂደት አሁን ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ሉሲዎቹ  የተገቢነት ክስ ያቀረቡባቸው ተጨዋቾች ግብ ጠባቂዋ ካሂና ታኬኒንታ እና ተከላካይዋ ኢሶማ ኦውደም ናቸው ።  ከ2010 ጀምሮ ለተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በተለያዩ አለምአቀፍ ውድድሮች ላይ ተጫውተው በማሳለፍ እንደቆዩ እና ከ2016 ጀምሮ ደግሞ ለአልጄሪያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን እየተጫወቱ መገኘታቸው የክሱ መናሻ ሆኖ ቀርቧል። የእግርኳሱ የበላይ አካል ፊፋ ‘ለሁለት ብሔራዊ ቡድኖች መጫወት አይቻልም’ ብሎ ባስቀመጠው ደንብ መሰረት ተጨዋቾቹ ተገቢ አይደሉም በሚል ነበር የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ክሱን ያስያዘው። ካፍም ክሱን ተቀብሎ ለማጣራት ይረዳው ዘንድ መሞላት የሚገባው ዝርዝር ቅፅ ለፌዴሬሽኑ ልኳል ።

በዚህም መሰረት ከነገው ጨዋታ አስቀድሞ የክስ ማስያዣ 2000 ዶላር ፣ ማስረጃዎች እና ቅፁ ላይ የሚሞሉ ሌሎች ዝርዝር ሀሳቦች ከተሟሉ በኋላ በመጨረሻም በአንበሏ ረሂማ ዘርጋው ተፈርሞ እንደሚላክ ሰምተናል። ካፍም ክሱን ተቀብሎ ከመረመረ በኋላ በቅርቡ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል ።