ሪፖርት | መቐለ እና ፋሲል ያለግብ ተለያይተዋል

የ26ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታድየም  መቐለ ከተማ እና ፋሲል ከተማን አገናኝቶ 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ሁለቱ ቡድኖች በ25ኛው ሳምንት ከተጠቀሙበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ እያንዳዳቸው የሁለት ተጨዋቾች ለውጥ አድርገዋል። መቐለ ከተማ በድሬዳዋ ከተማ 1-0 ከተሸነፈበት ጨዋታ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ በዳንኤል አድሀኖም ምትክ ከቅጣት የተመለሰው አቼምፖንግ አሞስን ሲያሰልፍ አማካይ ክፍል ላይ ደግሞ ሀብታሙ ተከስተን በያሬድ ብርሀኑ ቀይሯል። ፋሲል ከተማም በተመሳሳይ ውጤት በመከላከያ ከተረታበት ቡድን ውስጥ  መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ጉዳት የገጠመው አምሳሉ ጥላሁንን በሰይድ ሁሴን እንዲሁም አማካይ ክፍል ላይ ሙሉቀን አቡሃይን በኄኖክ ገምቴሳ በመቀየር ወደ ሜዳ ገብቷል።

በርካታ ተመልካች በተከታተለው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ፉክክር የተስተናገደበት እና በርካታ ፍትጊያዎችን የተመለከትንበት ነበር። ይሁን እንጂ አብዛኛው ፍልሚያ ይደረግ የነበረው በመሀለኛው የሜዳ ክፍል ላይ ሆኖ እና የሜዳው ጥራት መውረዱን ተከትሎ በሁለቱም በኩል የተፈጠሩት የግብ ዕድሎች በቁጥርም ሆነ በጥራት ዝቅተኛ ነበሩ። በተሻለ ሁኔታ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የነበራቸው ፋሲሎች መቐለዎች የመከላከል ቅርፃቸውን በያዙባቸው አጋጣሚዎች ሰብረው መግባት ሲቸግራቸው ይታዩ ነበር። 3ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አለሙ ከሳጥን ጠርዝ ላይ ሞክሮት ኢላማውን ካልጠበቀው ኳስ በኃላ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ተስኗቸዋል። ቡድኑ በተሻለ ሁኔታ ወደ ግብ ከደረሰባቸው አጋጣሚዎች መሀከል 22ኛው ደቂቃ ላይ ራምኬል ሎክ በመልሶ ማጥቃት በአስደናቂ ሁኔታ በግራ በኩል ተጨዋቾችን አልፎ ወደ ሳጥን ይዞ የገባው ኳስ በዋነኝነት ተጠቃሽ ሲሆን ከዚህ በቀደመው አጋጣሚ ደግሞ ኤፍሬም አለሙ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የገባበት ሁኔታ ሌላው ነበር። ኤፍሬም ሳጥን ውስጥ ከገባ በኃላ የወደቀ ሲሆን ፌደራል ዳኛ ተካልኝ ለማ ጨዋታው እንዲቀጥል ያደረጉበት ውሳኔ በፋሲል ተጨዋቾች ዘንድ ተቃውሞ እንዲደርስባቸው አድርጓል። ከዚህ ውጪ ከሰይድ ሁሴን በቀጥታ ወደ ሳጥን ይጣሉ የነበሩ ኳሶችም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠሪያነት ሲውሉ ይታይ ነበር። 

በአመዛኙ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ሲሞክሩ የነበሩት መቐለዎች ዐመለ ሚልኪያስን በፊት አጥቂነት ማሰለፋቸው ያልተጠበቀ ነበር። አብዛኛው የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴም በግራ መስመር አማካይነት ብዙውን ደቂቃ ወዳሳለፈው አማኑኤል ገ/ሚካኤል የሚጣሉ ኳሶች ላይ የተመረኮዘ ነበር። ሆኖም ፋሲሎች በተለይም ሰይድ ሁሴን የአማኑኤልን እንቅስቃሴ ለመግታት ያደረገው ጥረት የተሳካ ነበር። የመቐለዎች ብዙዎቹ ሙከራዎችም ጋቶች ፓኖም ከርቀት ከሚመታቸው እና ኢላማቸውን ካልጠበቁ ኳሶች የመነጩ ነበሩ። ከነዚህ አጋጣሚዎች ውጪ በ8ኛው እና 42ኛው ደቂቃ የተመቱት የአማኑኤል እና ጋቶች ቅጣት ምቶች የተሻሉ ሙከራዎች ነበሩ። ለ42ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር የተመታው የጋቶች ቅጣት ምት ምክንያት የሆነው ያሬድ ብርሀኑ ከአማኑኤል ጋር ቦታ ከተቀያየረ በኃላ የፋሲልን የቀኝ መከላከል ክፍል በተሻለ ሁኔታ ፈትኗል። ሆኖም ቡድኑ በጨዋታ አቀጣጣይነት በተጠቀመበት ኑሁ ፉሰይኒ በኩል ይሰነዘሩ የነበሩ ጥቃቶች እምብዛም ስኬታማ አልነበሩም። 

ሁለተኛው አጋማሽ እንደጀመረ መቐለዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ሁኔታ ተጭነው ተጫውተዋል። ይሁን እንጂ የሰይድ ሁሴን እና ፍፁም ከበደ የሁለቱ መስመሮች የመከላከል ብቃት ለፋሲሎች መከታ ሆኗቸዋል። እንደመጀመሪያው ሁሉ በዚህኛውም አጋማሽ ሙከራ በማድረግ የቀደመውም የፋሲሉ ኤፍሬም አለሙ ነበር። ሆኖም ከሁለት ተከላካዮች ጋር ታግሎ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የገባበት ይህ አጋጣሚ ለኢቮኖ ቀላል ነበር። 64ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ኄኖክ ገምቴሳ ከመሀል ሜዳ ያሻማውን ቅጣት ምት መሀመድ ናስር በግንባሩ ለመግጨት ተቃርቦ ነበር። በቁጥር በርክተው በመልለ የግብ ክልል የመድረስ በርከት ያሉ አጋጣሚዎች የነበሯቸው ፋሲሎች በሜዳው እና በተሳሳቱ ውሳኔዎቻቸው ምክንያት ወደ ሙከራነት መቀየር የሚችሉ በተለይም ከቀኝ መስመር ሊነሱ ይችሉ የነበሩ በርካታ አጋጣሚዎችን አባክነዋል። አብዱርሀማን ሙባረክ እና ኤርሚያስ ኃይሉ የቡድኑን ማጥቃት ለማጠናከር ተቀይረው የገቡበት ቅያሪም እምብዛም ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል።

በመቐለ በኩል በ66ኛው ደቂቃ አማኑኤል ገ/ሚካኤል እንዲሁም በ89ኛው ደቂቃ መድሀኔ ታደሰ ከቅርብ ርቀት ያገኟቸው ንፁህ ዕድሎች ተጠቃሽ ነበሩ። በተለይ መድሃኔ በዛው ቅፅበት በተከታታይ ያደረጋቸው ሙከራዎች ግብ እንዳይሆኑ የሳማኬን ጥረት የፈለጉ ነበሩ። ነገር ግን የሁለቱም ሙከራዎች እንቅስቃሴ ከጨዋታ ውጪ ነበር በማለት የፋሲል ተጨዋቾች ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን ሁኔታው ተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበሩት የቡድኑ አባላትም ከአራተኛው ዳኛ ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት የሆነ ነበር።  አማኑኤልን ወደ ፊት አጥቂነት በመቀየር እያሱ ተስፋዬ ፣ መድሃኔ ታደሰ እና ያሬድ ከበደን ቀይረው ያስገቡት መቐለዎች የመስመር ጥቃቶቻቸው ስኬታማ ሳይሆኑ እና ያገኟቸውን የማዕዘን ምቶችንም ወደ ግብነት ሳይቀይሩ ጨዋታው ተጠናቋል። 

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህለ – መቐለ ከተማ

እንደማስበው ጨዋታው ለሁለታችንም ጥሩ የነበረ አይመስለኝም ከሜዳው አንፃር። ደጋፊዎችን ለማስደሰት የሚያስችል ጨዋታ መጫወት የሚያስችል ሜዳ አልነበረም። ጨዋታው ተመጣጣኝ ነበር ማለት እችላለው በሁለት አጋጣሚዎች የተሻሉ እድሎች አግኝተን ነበር። እነሱን መጠቀም አልቻልንም።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – ፋሲል ከተማ

ባለፈው ሳምንት በመሸነፋችን ይህን ጨዋታ ለማሸነፍ ነበር የመጣነው። በመሆኑም በሁለቱም አጋማሾች ጥሩ ለመንቀሳቀስ ሞክረናል። በመከላከያውም ጨዋታ ጥሩ ነበርን ዛሬም የተሻለ ጥረት አድርገናል። በቡድኔ ላይም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎችን እያየሁ ነው።