ሪፖርት | አርባምንጭ እና ወላይታ ድቻ ነጥብ ተጋርተዋል

በ26ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማን ከወላይታ ድቻ ያገናኘው የዳንጉዛ ደርቢ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል፡፡

25ኛው ሳምንትን ሳይጫወቱ ያሳለፉት ባለሜዳዎቹ አርባምንጮች ከወልዲያው የ24ኛ ሳምንት ጨዋታ ስብስብ አለልኝ አዘነ እና ወንድወሰን ሚልኪያስን አሳርፈው አንድነት አዳነን እና ምንተስኖት አበራን ተክተው ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን እንግዳዎቹ ወላይታ ድቻዎች ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ስብስብ ኢማኑኤል ፌቮ፣ ተክሉ ታፈሰ፣ ያሬድ ዳዊት፣ ኃይማኖት ወርቁ፣ አብዱልሰመድ ዓሊ፣ ተመስገን ዱባ እና ዳግም በቀለን አሳርፈው በምትካቸው እርቅይሁን ተስፋዬ፣ ዮናታን ከበደ፣ ታድዮስ ወልዴ፣ ጃኮ አረፋት እና ወንድወሰን ገረመውን ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

ጨዋታው ገና ከረፋዱ በደመቀ የደጋፊዎች ድባብ ታጅቦ የዋለ ሲሆን የአርባምንጭ ከተማ የደጋፊዎች ማህበር ለወላይታ ድቻ የደጋፊዎች ማህበር ስጦታ ሲያበረክቱ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ተዘምሯል፡፡

በጣም የተቀዛቀዘ የነበረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የረባ እንቅስቃሴ ሳይታይበት ለረጅም ደቂቃ ዘልቋል፡፡ በተለይ የመጀመሪያዎቹ 15 እና 20 ደቂቃ በጣም አስልቺ መልክ የነበራቸው ነበሩ፡፡ 21ኛ ደቂቃ ላይ የጨዋታውን እንቅስቃሴ ልትቀይር የምትችል ሙከራ ከአማኑኤል ጎበና ወደ ፀጋዬ አበራ በጥሩ ቅብብል የተሻገረችውን ኳስ ፀጋዬ ወደ ግብ አክርሮ ቢመታም የድቻ ተከላካዮች ተደርበው ኳሷ ወደ ውጪ ወጥታለች፡፡ ይህች ኳስ በእጅ ተነክታለች በሚልም አርባምንጮች ቅሬታ አሰምተዋል፡፡

በጨዋታው አርባምንጮች የወላይታ ድቻን አደረጃጀት ለመስበር ቢሞክሩም ጥረታቸው በሙከራዎች የታጀበ አልነበረም። በአማኑኤል ጎበና እና ምንተስኖት አበራ የሚመራው የአማካይ መስመርም አመርቂ እንቅስቃሴ ማሳየት ተስኖታል። ወላይታ ዲቻዎች በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የአርባምንጭ ከተማን የግብ ክልል በጃኮ አረፋትና በበዛብህ መለዮ አማካኝነት ሲፈትሹ ቢታዩም እነሰደ አርባምንጭ ሁሉ የእንግዶቹም ጥረት በሙከራዎች የታጀበ አልነበረም። በመጀመርያው አጋማሽ መገባደጃ 42ኛ ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል ፀጋዬ አበራ እና ብርሃኑ አዳሙ ተቀባብለው ለአማኑኤል የደረሰውን ኳስ አማካዩ ወደ ግብ ቢመታም ኳሷ አቅጣጫዋን ቀይራ ወደ ውጪ ወታለች፡፡ በዚህ መልኩም ጥሩ የሚባል ሙከራ ሳይደረግበት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ሲጫወቱ የነበሩት አርባምንጭ ከተማዎች ከተከላካይ መስመር ጀምሮ መስርተው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ወላይታ ድቻዎች ጠንካራ የሆነ የመከላከል አደረጃጀት ይዘው ገብተዋል። በ49ኛው ደቂቃ ላይ ከአማኑኤል ጎበና የተቀበለውን ኳስ ምንተስኖት አበራ ከረጅሙ ወደ ጎል አክርሮ ቢመታም በግቡ አናት ላይ ሲወጣበት 51ኛው ደቂቃ ላይ በአጭር ቅብብል ፀጋዬ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ተመስገን ካስትሮ በግምባሩ ገጭቶ በግብ ቋሚ በኩል ወጥታለች። 56ኛው ደቂቃ ላይ አሁንም በአርባምንጭ ከተማ በኩል ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ተከላካዩ አሌክስ አማዙ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጭ ወጥቶበታል።

ከእረፍት በኋላ ለረጅም ደቂቃዎች ከማጥቃት ወረዳው ርቀው የቆዩት ወላይታ ድቻዎች እዮብ ዓለማየሁን ቀይረው ካስገቡ በኋላ መሻሻል በማሳየት ወደ አርባምንጭ ግብ ክልል በተደጋጋሚ ደርሰዋል፡፡ በተለይ 79ኛው ደቂቃ ላይ የአርባምንጭ ከተማ ተካላካይ እና ግብ ጠበቂው በፈጠሩት ስህተት እዮብ ለጎል የቀረበ ኳስ አግኝቶ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ግብ ጠባቂውን አታሎ በማለፍ ወደ ጎል ቢመታም አሌክስ አማዙ ደርሶ በግንባሩ በመግጨት አውጥቶበታል፡፡ ሆኖም እዮብ ዓለማየሁ አሌክስ አማዙና ወርቅይታደስ አበበ ላይ በሰራው ተከታታይ ጥፋት 84ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ የቀረውን ደቂቃ ግብ ለማስቆጠር አርባምንጭ ከተማዎች በረጅሙ ኳሶችን ወደ ማጥቃት ሳጥን በመጣል እድል ለመፍጠር ቢሞክሩም አንድ ነጥብን መሰረት ያደረገው ጠንካራው የወላይታ ድቻን የተከላካይ መስመር ሰብሮ ማስቆጠር ሳይችሉ ያለ ግብ ጨዋታው ተጠናቋል፡፡

የአስልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሃ – ወላይታ ድቻ

በጨዋታው ያሰብነው ተሳክቶልናል፡፡ በተደጋጋሚ ነጥብ መጣላች ይህንን ጨዋታ በጥንቃቄ እንድንጫወት ምክንያት ሆኖናል፡፡ እንደተመለከታችሁት አርባምንጮች በጣም ጥሩ ነበሩ። የኛን የመከላከል ሲስተም ሰብረው ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡ በዚህ አጨዋወታቸው እዚህ ደረጃ ላይ መሆን አልነበረባቸውም፡፡ ደጋፊዎች ያሳዩት መከባበር ደስ የሚል ነው። በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

* የአርባምንጭ ከተማ አሰልጣኞች አስተያየት ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆኑም።