” በግሌ ተጨማሪ ልምምዶች መስራቴ ወደ ቀድሞ አቋሜ እንድመለስ ረድቶኛል” አብዱልከሪም መሐመድ

ኢትዮጵያ ቡናን ለቆ በክረምቱ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያመራው አብዱልከሪም መሐመድ በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሳምንታት ከቡድኑ ጋር በፍጥነት ካለመላመዱ ጋር ተያይዞ ለቡድኑ ይሰጠው የነበረው አገልግሎት የተጠበቀውን ያህል አመርቂ አልነበረም። አብዱልከሪም ከጨዋታ ጨዋታ አቋሙን በማሻሻል በቡድኑ የዋንጫ ተፎካካሪነት ጉዞ ላይ ወሳኙን ሚና ከሚወጡ ተጫዋቾች ግንባር ቀደሙ ከመሆኑ ባሻገር ከኋላ መስመር በመነሳት ግሩም ጎሎች እያስቆጠረ ይገኛል።

አቡዱልከሪም እያሳየ ስለሚገኘው ወቅታዊ መልካም እንቅስቃሴ እና ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀሪ ጨዋታዎች ስለሚያደርገው የዋንጫ ተፎካካሪነት ጉዞ ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

ፆም እንዴት ነው?  ፆመኛ ሆኖ መጫወት ምን ይመስላል ?

ፈጣሪ ይመስገን ጥሩ ነው። በእኔ እምነት ከፆም ጋር ኳስ መጫወት ከባድ አይደለም። እርግጥ ፆመኛ ብሆንም ራስህን ለጨዋታ በሚገባ ጠብቀህ ማዘጋጀት ከቻልክ ፣ በቂ እረፍት ካደረክ ፣ በአፍጥር እና በሱር ሰዓት ምን አይነት ምግብ መመገብ እንዳለብህ ከመረጥክ ጨዋታ ላይ ይከብዳል ብዬ አላስብም።

በመጣህበት አመት መጀመርያ በተወሰኑ  ጨዋታዎች ላይ የተጠበቀውን ያህል ጥሩ አገልግሎት አልሰጠህም። ምንድን ነበር ምክንያቱ? 

የመጣሁበት ዓመት አንተ እንዳልከው ጥሩ አልነበርኩም። እኔ ብቻ ሳልሆን ሙሉ የቡድኑ አባላትም ጥሩ አልነበርንም። የአሰልጣኛችን አጨዋወት ቶሎ መላመድ ላይ ተቸግረን ነበር። አጠቃላይ አንደኛው ዙር ላይ ብዙ ተቸግረናል፤ ብዙም ነጥብ ጥለናል ብዬ የማስበው። እኔም የዛኑ ያህል ቸግሮኝ ነበር ።

አሁን በጥሩ አቋም ላይ ትገኛለህ በቡድኑ ውስጥ በመከላከሉም በማጥቃት ሽግግሩም ትልቁን ሚና እየተወጣህ ነው…

አዎ። ያለኝን አቅም አውጥቼ ብዙ ቡድኑን እየጠቀምኩ ነው ብዬ ባላስብም በምችለው አቅም ሁሉ ክለቡን እያገለገልኩ ነው ብዬ አስባለው። አሁን ላይ ጥሩ ነገር እያደረኩ ነው። ተጨማሪ ልምምዶችን እሰራለው፤ ያው አሁን ፆም በመሆኑ ድካም ለመቀነስ በአሁን ሰአት ባልሰራም በፊት ተጨማሪ ልምምዶችን በግሌ መስራቴ ወደ አቋሜ ለመመለስ አግዞኛል። ይህ ብቻ ሳይሆን ለእኔ ጥሩ መሆን የረዳኝ  ከእኔ አጠገብ አብረው የሚጫወቱ የቡድን አጋሮቼ ጥሩ መሆን እና ተግባብተን መጫወታችን አስተዋፆኦ አለው። በአጠቃላይ አሁን ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ ነው።

ግሩም ጎሎችን በወሳኝ ጨዋታዎች ላይ እያስቆጠርክ ነው…

ጎል ካስቆጠርኩ ረጅም ጊዜዬ ነው፤ ቡና እያለው ነበር ጎል ያስቆጠርኩት። በቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያ የመጀመርያ ጎሌን መቐለ ከተማ ላይ አስቆጥሬያለው። ባለፈው ሳምንትም ጅማ አባጅፋር ላይ እንዲሁ ተመሳሳይ ጎል አስቆጥሬያለው። የእኔ ጎል ማስቆጠር ብቻ ሳይሆን ቡድናችን እንደ ቡድን ጥሩ እየተደራጀ አሰልጣኙ የሚፈልገውን አጨዋወት ለመጫወት ጥረት እያደረግን ነው። አሁን ጥሩ ነገር ላይ እየመጣን ነው ።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ዘንድሮ የመጀመርያ ዋንጫዬን አነሳለሁ ብለህ ታስባለህ ? 

አዎ። በቀጣይ እያንዳንዱን ጨዋታ በትኩረት እየተጫወትን ሦስት ነጥብ ይዘን እየወጣን ከፈጣሪ ጋር የዋንጫው አሸናፊ እንሆናለን ብዬ አስባለው። እኔም በታሪክ የመጀመርያዬን የሊጉን ዋንጫ አነሳለው ብዬ አስባለው።