ወላይታ ድቻ በሜዳው የሚያደርጋቸው ቀሪ ጨዋታዎቹ ላይ የቦታ ለውጥ ያደርጋል

ወላይታ ድቻ በፕሪምየር ሊጉ ከሚያደርጋቸው ቀሪ አራት ጨዋታዎች መካከል ሁለቱ የሜዳው ጨዋታዎቹን የሚያደርግበትን ሜዳ ከሶዶ ወደ ቦዲቲ ለማዞር ወስኗል፡፡

በወቅታዊ የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ (27ኛ ሳምንት) እና ጅማ አባጅፋር (30ኛ ሳምንት) የሚያስተናግድበት እና ወደ ወራጅ ቀጠናው ከመግባት ስጋት ርቆ አመቱን ለማጠናቀቅ የሚያደርጋቸውን ወሳኝ የሜዳው ጨዋታዎች ለማድረግ የሶዶ ስታዲየም ምቹ ባለመሆኑ ወደ ቦዲቲ ስታዲየም ለማዘዋወር መወሰኑ ተገልጿል፡፡

የክለቡ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጌታሁን ጋረደው በጉዳዩ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ የሚከተለውን ብለዋል።

” የሶዶ መጫወቻ ሜዳው ጥሩ ባለመሆኑ ቅሬታዎች እየመጡ ነው። ሜዳው በዝናብ ምክንያት በመጨቅየቱና ጨዋታ ለማድረግ ብቁ ባለመሆኑ ምክንያት ነው ወደ ቦዲቲ ለመቀየር ከውሳኔ ላይ የደረስነው። የአንደኛ ሊጉ ቡድን ወላይታ ሶዶ ራሱ ወደ ቦዲቲ መጥቶ ነው ጨዋታውን ያደረገው። እኛም ይህን ማድረጋችን የግድ ነው። ስለዚህ ስራ አስኪያጁ በጉዳዩ ዙርያ ከፌድሬሽን ጋር ተነጋግሮ ውጤቱን እንዲገልፅልን አሳውቀነዋል። ”

ወላይታ ድቻ በ2006 ወደ ፕሪምየር ሊግ ካደገ በኋላ የሶዶ ስታድየም ለውድድር ብቁ ባለመሆኑ ምክንያት እስከ 2008 ድረስ በሀዋሳ እና ቦዲቲ የሜዳውን ጨዋታዎች ማድረጉ የሚታወስ ነው።

ፎቶ – ወላይታ ድቻ ከአንድ ሳምንት በፊት (25ኛ ሳምንት) ጨዋታ ያደረገበት የሶዶ ስታድየም