ፕሪምየር ሊግ | የ27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ – ክፍል 1

ከነገ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውሎ መካከል በአዲስ አበባ ስታድየም የሚስተናገዱት ሁለት ጨዋታዎች የዛሬው ቅድመ ዳሰሳ የክፍል አንድ ትኩረቶቻችን ሆነዋል።


ወልዲያ ከ ጅማ አባ ጅፋር

ወልዲያ በ19ኛው ሳምንት ፋሲል ከተማን ባስተናገደበት ጨዋታ በተፈጠረው ችግር ከተጣለበት ቅጣት የመጨረሻ በሆነው የገለልተኛ  ሜዳ ጨዋታ ከመሪው አባ ጅፋር ጋር ይገናኛል። በሊጉ ግርጌ የሚገኘው ወልዲያ በቀጣዩ አመት ወደ ከፍተኛ ሊግ ላለመውረድ ካሁኑ የሌሎችንም ውጤት መጠበቅ ሊኖርበት ይችላል። በዚህ ሳምንት ነጥብ ካላገኘ እንዲሁም ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አርባምንጭ ከተማ ድል ከቀናቸው ከሊጉ ጋር የሚለያይ በመሆኑ ነገ ከሌሎቹ ቀድሞ በሚጫወትበት በዚህ መርሀ ግብር በማሸነፍ ዕድሉን ማራዘም ግዴታው ሆኗል። ጅማ አባ ጅፋርም በመሪነት ለመቀጠል ሙሉ ነጥብ አስፈላጊው ነው። ይህ ካልሆነ ተከታዮቹ  የሚያስመዘግቡት ውጤት እስከ አምስተኝነት ሊያውረደው ይችላል። በመሆኑም ሽንፈት ከሚያስከፍላቸው ዋጋ አንፃር በነገው ግንኙነታቸው ሁለቱም ተጋጣሚዎች ከባድ ፍልሚያ የሚያደርጉበት የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ይጠበቃል።

ከሠለሞን ገ/መድህን ጉዳት እና ከብሩክ ቃልቦሬ ቅጣት ሌላ የወልዲያን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ያልተሳካ ሲሆን በጅማ አባጅፋር በኩል ጉዳት ላይ የሚገኘው ኄኖክ ኢሳያስ ውጪ ሙሉ ቡድኑ ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑን ሰምተናል።

ሁለቱም ቡድኖች በ26ኛው ሳምንት ለጨዋታ አስቸጋሪ በሆነው የአዲስ አበባ ስታድየም ተጫውተው አሁን መገናኘታቸው ራሳቸውን ከሁኔታው ጋር ለማላመድ ዕድል የሚሰጣቸው ይሆናል። ከመከላከያ ጋር በነበረው ጨዋታ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ሜዳው ጭቃማ ቢሆንም የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ባገኙባቸው ደቂቃዎች በተሻለ ትዕግስት ተጫውተው ግብ ያስቆጠሩት አባ ጅፋሮች ነገም ይሁን እንዳሻውን ወደ አጥቂው መስመር በማስጠጋት እና ተመስገን ገ/ኪዳንን ወደ ኃላ በመሳብ እንዲሁም የዮናስ ገረመው እና አሮን አሞሀ የቀኝ እና ግራ ድጋን በመጠቀም  የኄኖክ አዱኛን ጠንካራ የቀኝ መስመር የማጥቃት ሀይል ጨምረው በቅብብሎች በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ በመቆየት ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚሞክሩ ይጠበቃል።

ወልዲያዎች እየታየባቸው ያለው የኃላ ክፍል ድክመት በጥንቃቄ እንዲጫወቱ የሚያስገድዳቸው ቢሆንም ግብ ማስቆጠር ደግሞ በዛው መጠን አስፈላጊያቸው ነው። ቡድኑ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ሁሉ ፍጥነት ባለው ጥቃት የመጀመሪያዎቹን ደቂቃዎች እንደሚያሳልፍም ይገመታል። ፊት ላይ ለሚሰለፉት አንዷለም ንጉሴ እና ኤዶም ኮድዞ የሚላኩ ቀጥተኛ ኳሶች ደግሞ ዋነኛ የጥቃት መነሻ እንደሚሆኑ ይታሰባል። ከዚህ ውጪ ወደ ውስጥ አጥብበው የሚጫወቱት የመስመር አማካዮቹም ከሌሎች አማካዮች እገዛ የሚያገኘው አሚኑ ነስሩን በመጋፈጥ በራሳቸው የግብ ዕድሎችን መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ ውጪ ግን ቡድኑ በተለይ ደካማ የሆነው የቆሙ ኳሶችን የሚከላከልበት መንገድ ለኦኪኪ አፎላቢ ብቃት ሊያጋልጠው የሚችልበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ መናገር ይቻላል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ጅማ ላይ የተደረገው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታ በአባ ጅፋር የ1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

– ወልዲያ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች በሙሉ ሽንፈት የገጠመው ሲሆን ሲዳማ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ካስቆጠራቸው ግቦች ውጪም ተጨማሪ ግቦችን ማግኘት አልቻለም።

– በሁለተኛው ዙር አንድ ሽንፈት ብቻ የገጠመው ጅማ አባ ጅፋር ከአራት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኃላ ነበር ሳምንት መከላከያን ማሸነፍ የቻለው።

ዳኛ

– ፌደራል ዳኛ ጌቱ ተፈራ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የመምራት ሀላፊነት ተሰጥቶታል።


ደደቢት ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የደደቢት በሁለተኛው ዙር በውጤት መንሸራተት የጨዋታውን ክብደት ዝቅ ያደረገው ቢሆንም ጥሩ ፉክክር እንደሚስተናገድበት ተስፋ ይጣልበታል። ከዓዲግራት በሽንፈት የተመለሰው ደደቢት ዳግም ወደ ዋንጫ ፉክክሩ የመመለስ ህልሙ ያበቃለት ይመስላል። ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች ውጤት ከተመለከትንም ደደቢት የስመዘገበው ውጤት የሚሻለው ከወልዲያ ብቻ ነው። በዚህ መለኪያ ከሁሉም ክለቦች በላይ ውጤት የሰበሰበው ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁን ሁለተኛ ደረጃ ላይ ቢቀመጥም አለማሸነፍ ግን ደረጃውን የሚያሸራትተው ይሆናል። ከሁለት አቻ ውጤቶች በኃላ ሳምንት ወደ ድል የተመለሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአንድ በላይ ግብ ማስቆጠር የቻለውም ከአራት ሳምንታት ቆይታ በኃላ ነበር። ጨዋታው አንድ ቀሪ ጨዋታ ያለው ደደቢት ከመጋቢት መጨረሻ በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ድል ለመመለስ ቅዱስ ጊዮርጊስም በዋንጫ ተፎካካሪነቱ ለመቀጠል የሚገናኙበት ይሆናል።

የደደቢቶቹ ኩዌኪ አንዶህ እና አስራት መገርሳ እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊሱ አዳነ ግርማ በቅጣት ከዚህ ጨዋታ ውጪ ሆነዋል። በጉዳት በኩል ደግሞ ከደደቢት የተሰማ ዜና የሌለ ሲሆን ሳላሀዲን ሰይድ ፣ አማራ ማሌ እና ሪቻርድ አፒያ ከቅዱስ ጊዮርስጊ አሁንም የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ይገኛሉ።

ዝናባማ በነበረው አመሻሽ የተገናኙበት የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ነገም ሊደገም የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል። ይህ ከሆነም ጨዋታው በቀላሉ ክፍተቶች የማይገኙበት እንዲሁም የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ምርጫ ከሆነው በኳስ ቁጥጥር ላይ ከተመሰረተው ጨዋታ ይልቅ ተሻጋሪ ኳሶች ጎልተው የሚታዩበት የመሆን ዕድል ይኖረዋል። በደደቢት በኩል አብዝተው ወደ ፊት የማይሄዱ የመስመር ተከላካዮች እና ኳሶችን በፍጥነት ፊት ላይ ለሚገኙ አጥቂዎች ከተጋጣሚ የተከላካይ መስመር ጀርባ ለመጣል የሚሞክሩ አማካዮችን የማየት ዕድላችንም ሰፊ ነው። ጉልበት በሚፈልገው የመሀል ሜዳ ፍልሚያ ላይም አስራት መገርሳ በሌለበት ከድር ኩሊባሊን በቦታው በመጠቀም እና የአንድ ለአንድ ፍልሚያዎች ላይ እንዲሳተፍ በማድረግ ቀሪዎቹ ሁለት አማካዮች ከመከላከል ሀላፊነታቸው ባለፈ ተፈላጊዎቹን ቀጥተኛ ኳሶች በተለይ ለመስመር አጥቂዎች የማድረስ ኃላፊነታቸው ሊጎላ ይችላል። ጌታነህ ከበደም በሚደርሱት ኳሶች ከቅዱስ ጊዮርጊስ የኃላ መስመር ተሰላፊዎች ጋር ከባድ ፍሊሚያ የሚጠብቀው ይሆናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅርብ ጨዋታዎች ፊት ላይ አንድ አጥቂ በማሰለፍ አምስት አማካዮችን ለመጠቀም ሲሞክር ይታያል። ከነዚህ መሀል ከሁለቱ መስመሮች የሚነሱት በሀይሉ አሰፋ እና ኦዝቫልዶ ታቫሬዝ ነገም ወደ መሀል በማጥበብ በደደቢት የመሀል እና የመስመር ተከላካዮች መሀል ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት እንዲሁም እየተነቃቁ የመጡት የመስመር ተከላካዮች ደግሞ ኮሪደሩን ተከትለው ወደ ውስጥ በሚጥሏቸው ኳሶች ተደጋጋሚ ጥቃት ለመሰንዘር እንደሚሞክሩ ይታሰባል። በመጠኑ ወደ ፊት ተጠግቶ ማጥቃቱን የሚያግዘው ናትናኤል ዘለቀም ከደደቢት የሶስትዮሽ ጥምረት ጋር የሚጋፈጠው አብዱልከሪም ኒኪማን በማገዝ የመጨረሻ ዕድሎችን ለመፍጠር ለቡድኑ ተጨማሪ ሀይል መሆኑ የሚቀር አይመስልም። የደደቢት የመስመር አጥቂዎች ፊት ላይ ተነጥለው የሚቀሩበት አጨዋወት ነገም የሚደገም ከሆነ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚኖራቸው ፍልሚያ ተጠባቂ የመሆኑን ያህል የሰማያዊዎቹ የኃላ ክፍል በሶስቱ የአማካይ መስመር ተጨዋቾቹ ዕገዛ ብቻ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚመጣውን ጫና በምን መልኩ ሊወጣው የችላል የሚለውም ጥያቄ አጓጊ ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 17 ጊዜ ተገናኝተዋል።  ቅዱስ ጊዮርጊስ በ11 ጊዜ ድል ቅድሚያውን ሲወስድ ደደቢት ሶስት ጊዜ አሸንፎ ቀሪዎቹ ሶስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው። ቅዱስ ጊዮርጊስ 28 እንዲሁም ደደቢት 17 ጊዜ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ችለዋል። 

– ደደቢት በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ድል ያስመዘገበው ቡድኑ ዋንጫ ባነሳበት የ2005 የውድድር ዘመን 3-1 ባሸነፈበት ወቅት ነው።

– ደደቢት ከ17ኛው ሳምንት በኃላ ባደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ብቻ ያሳካ ሲሆን በአምስቱ ደግሞ ግብ ሳያስቆጥር ቀርቷል።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ያስመዘገባቸው ሶስት ድሎች እና ሶስት የአቻ ውጤቶች ከሌሎቹ ክለቦች ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲተያይ ከፍተኛው ነው።

ዳኛ

– ጨዋታው በፌደራል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው መሪነት የሚካሄድ ይሆናል።