ፕሪምየር ሊግ | የ27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ – ክፍል 2

በጎንደር እና ድሬዳዋ የሚደረጉትን ሁለት የሊጉ 27ኛ ሳምንት የነገ ጨዋታዎች በክፍል ሁለት ዳሰሳችን ተመልክተናቸዋል።

ፋሲል ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

እንደ ሲዳማ ቡና የፎርፌ ውጤት ባይሆን ኖሮ ሁለቱ ክለቦች በእኩል 35 ነጥብ ነበር የሚገናኙት። ይህ ሆኖ ቢሆን ደግሞ ሁለቱም የተረጋጋ ቦታ ላይ እንደተቀመጡ መናገር ይቻል ነበር። አሁንም ቢሆን ፋሲል ከተማ ከዋንጫ ፉክክሩ ቢርቅም ስጋት ግን የለበትም። ሲዳማ ቡናም ነጥቡ ወደ 29 ዝቅ ካለ በኃላ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ማሸነፉ ከወራጅ ቀጠናው ያለውን ልዩነት መልሶ ለማስፋት አስችሎታል። ነገር ግን አሁንም ሙሉ ለሙሉ ከስጋት ነፃ አልሆነም። ጥሩ የሜዳ ውጪ ሪከርድ የሌለው ሲዳማ ጎንደር ላይ ውጤት ማግኘት ከቻለ ስጋቱን መቅረፍ የሚችል ይሆናል። ከ20ኛው ሳምንት በኃላ አሁንም ወደ አሸናፊነት መመለስ ያልቻለው ፋሲል ከተማ ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ውጤት ማግኘት በያዘው የ6ኛነት ደረጃ ላይ እንዲቆይ ያደርገዋል።

ፋሲል ከተማ አምሳሉ ጥላሀንን ከጉዳት መልስ የሚያገኝ ሲሆን አይናለም ኃይለ ግን አሁንም አላገገመም። በሲዳማ በኩል የተሰማ የጉድትም ሆነ የቅጣት ዜና ግን የለም።

ፋሲል ከተማ በአጨዋወት ደረጃ በፊት የሚታወቅበት መስመሮች ላይ ትኩረት ያደረገ ፈጣን ሽግግር አሁን አሁን እየታየ አይገኝም። ይልቁንም የአማካይ ክፍል ተሳላፊዎቹን ቁጥር በማብዛት በኳስ ቁጥጥር ላይ መሰረት ማድረግን የመረጠ ይመስላል። ሆኖም የመስመር ተከላካይዮቹ የማጥቃት ድርሻ ማነስ በቀላሉ ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ለመድረስ እንዲቸገር ሲያደርገው ይታያል። ከሙከራዎቹም አብዛኞቹ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች የግል ጥረት የሚገኙት ይበዛሉ። በነገውም ጨዋታ በጨዋታ አቀጣጣይነት የሚሰለፈው ኤፍሬም አለሙ እንዲሁም የራምኬል ሎክ እና መሀመድ ናስር እንቅስቃሴዎች ለቡድኑ ዋነኛ የግብ አጋጣሚ መፍጠሪያ መሳሪያዎች እንደሚሆኑ ይገመታል። 

ከአጥቂ መስመር ተሰላፊዎቹ በዋነኛነት ከአዲስ ግደይ በተጨማሪ ከአማካይ ክፍል ተሰላፊዎቹም ጭምር ግቦችን እያገኘ የሚገኘው ሲዳማ ቡና ከመስመር አጥቂዎቹ ብቻ ይመነጭ የነበረውን ጥቃት ወደ መሀል ያስተላለፈው ይመስላል። ባለፉት ስድስት ጨዋታዎችም ቡድኑ አምስት ግቦችን ከመሀል ክፍል ተሳላፊዎቹ አግኝቷል። በነገው ጨዋታ ከታታውሪ ኄኖክ ገምቴሳ እና ይስሀቅ መኩሪያ እንዲሁም ከእነርሱ ፊት ከሚኖረው ኤፍሬም አለሙ ጋር የሚፋለሙት የሲዳማ የአማካይ ክፍል ተጨዋቾች በተለይም ዮሴፍ ዮሀንስ ልዩነት ፈጣሪ ሊሆን የሚችልበት ዕድል አለ። እዚህ ላይ የሀብታሙ ገዛሀኝ እና አዲስ ግደይ የቀኝ እና ግራ ጥቃት ከጠንካሮቹ የፋሲል የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚገናኙባቸው ቅፅበቶችም መረሳት የለባቸውም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– እስካሁን ባለው የሶስት ጊዜ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው በሙሉ ሲዳማ ቡና አሸናፊ መሆን ችሏል። በነዚህ ጨዋታዎች ሲዳማ ሰባት ግቦችን ሲያስቆጥር ፋሲል ከተማ ብቸኛዋን ግብ አምና በሁለተኛው ዙር 3-1 ሲሸነፍ በናትናኤኣ ጋንቹላ አማካይነት አግኝቷል።

– ፋሲል ከተማ ጎንደር ላይ ካደረጋቸው የመጨረሻ ሶስት ጨዋታዎች ውስጥ  ሁለቱን ያለግብ በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ በመጨረሻ ደግሞ በመከላከያ 1-0 ተረቷል።       

– ሲዳማ ቡና በዘንድሮው አመት ከይርጋለም ውጪ ሶስት ነጥብ ያሳካው ወልዲያ እና ድሬዳዋን በገለልተኛ ሜዳ በገጠመባቸው ሳምንታት ብቻ ነበር።

ዳኛ

– ፌደራል ዳኛ ኢብራሂም አጋዥ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።


        ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ለረጅም ሳምንታት ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ ዋና ተዋንያን ሆነው የቆዩት ሁለቱ ክለቦች እርስ በእርስ መገናኘታቸው ጨዋታውን እጅግ ተጠባቂ አድርጎታል። ለአምስት ሳምንታት የዘለቀው ያለመሸነፍ ጉዞው በሲዳማ የተገታው ድሬዳዋ ከተማ ዳግም ወደ አሸናፊነት ተመልሶ በአንድ ነጥብ ከሚበልጠው ተጋጣሚዉ ጋር ያለውን ልዩነት ወደ አራት ከፍ ለማድረግ ይጫወታል። በወራጅ ቀጠናው ውስጥ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከድሬ በተለየ 25ኛውን ሳምንት በድል ነበር ያሳለፈው። ነገር ግን 28 ነጥብ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ወደ ምስራቅ ከሚያደርገው ጉዞ ሶስት ነጥብ ማግኘት እጅግ ጠቃሚው ይሆናል። በታችኛው የሰንጠረዡ ክፍል ባለው ተለዋዋጭ ፉክክር ላይ ልዩነት የሚፈጥረው ይህ ጨዋታ ከዚህ ሳምንት ጨዋታዎች ሁሉ ከፍተኛ ፍልሚያ የሚደረግበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

በድሬዳዋ ከተማ ብቸኛው ጉዳት ላይ ይገኝ የነበረው ተጨዋች ሚካኤል አካፉ እንዳገገመ የተሰማ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክም ኄኖክ ካሳሁንን በጉዳት ሲያጣ ተስፋዬ መላኩን ከጉዳት ዮሀንስ በዛብህን ከቅጣት መልስ የሚጠቀም ይሆናል።

በቅርብ ሳምንታት ቡድኖቹ ከተጠቀሙባቸው አሰላለፎች በመነሳት ነገ ሁለቱም 4-4-2ን ምርጫቸው ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይገመታል። ለማጥቃት በሚፈልግባቸው ጨዋታዎች ላይ ይህን አሰላለፍ የሚጠቀመው ድሬዳው ከተከላካይ አማካዩ ኢማኑኤል ላርያ ፊት ለሚያሰልፋቸው ሶስት አማካዮች የሚሰጠውን የማጥቃት ነፃነት ነገም እንደሚደግመው ይታሰባል። በዚህም በደካማው የኢትዮ ኤሌክትሪክ የኃላ መስመር ላይ ጫና እንደሚያሳድሩ ከሚጠበቁት ሁለቱ አጥቂዎች ጀርባ ወደ መሀል የጠበበ ቅርፅ ባላቸው አማካይምቹ ተጠቅሞ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚንቀሳቀስ ይጠበቃል።

ከኄኖክ ካሳሀን ጉዳት በኃላ ተጨዋቹ ከአዲስ ነጋሽ ጋር የፈጠረውን የአማካይ መስመር ጥምረት ያፈረሰው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ4-4-2 ሀዋሳ ከተማን ድል ማድረግ ችሏል። በተለይ በመከላከል የጨዋታ ሂደት ላይ ቡድኑ ለተከላካይ መስመሩ ጥሩ ሽፋን መስጠት የቻለ ሲሆን የአልሀሰን ካሉሻ የፈጠራ ሀላፊነት እንዳለ ሆኖ የመስመር ተከላካዮቹን በተይም በቀኝ በኩል የሚሰለፈው ዐወት ገ/ሚካኤልን ተሻጋሪ ኳሶች በማጥቃት ሂደቱ ላይ እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። እንደ ሀዋሳው ጨዋታ ሁሉ በነገው ጨዋታም ቡድኑ አሁንም በግራ መስመር አማካይነት ሲጠቀምበት የነበረው ዲዲዬ ለብሪን ሊያሳርፈው አልያም ፊት ላይ ከታፈሰ ተስፋዬ ወይም ኃይሌ እሸቱ ጋር ሊያጣምረው የሚችልበት ዕድል ይኖራል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች 13 ጊዜ ሲገናኙ ኤሌክትሪክ 6 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ድሬዳዋ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በ5 አጋጣሚዎች አቻ ተለያይተዋል። አሌክትሪክ 19፣ ድሬዳዋ 10 ግቦችን አስቆጥረዋል።

– ድሬዳዋ ላይ ባደረጓቸው 6 ጨዋታዎች ድሬዳዋ አንድ ጊዜ ብቻ ድል ሲያስመዘግብ ሶስት ጊዜ አቻ ተለያይተው ሁለት ጊዜ ኤሌክትሪክ አሸንፏል።

– ድሬዳዋ ለመጨረሻ ጊዜ በሜዳው ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች አራቱን አሸንፎ በአንዱ ነጥብ ተጋርቷል። በነዚህ ጊዜያት ግብ የተቆጠረበት ከሀዋሳ ጋር አቻ በተለያየበት ጨዋታ ብቻ ነበር።

– ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሁለተኛው ዙር ሶስት ጊዜ ከአዲስ አበባ የወጣ ሲሆን ከወልዋሎ ጋር ነጥብ ከመጋራቱ ውጪ ጅማ ላይ አራት እንዲሁም አዳማ ላይ ስድስት ግቦች ተቆጥረውበት ከባባድ ሽንፈቶችን አስተናግዷል።

ዳኛ

-ይህን ተጠባቂ ጨዋታ ለመዳኘት የተመረጠው ኢንተርናሽናል በላይ ታደሰ ነው።