ሪፖርት |  ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል

በ27ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቅዳሜ ድሬዳዋ ስታዲየም ላይ ላለመውረድ ትግል ላይ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን ያገናኘው ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል።

ድሬዳዋ ከተማ በ26ኛው ሳምንት በሲዳማ ቡና ከተሸነፈው ስብስቡ ውስጥ ሳውሬል ኦልሪሽ እና ዘላለም ኢሳያስን በማሳረፍ በሱራፌል ዳንኤል እና አትራም ኳዋሜ ተክተው ጨዋታውን ሲጀምሩ ሀዋሳ ከተማን ሜዳው ላይ አስተናግዶ ያሸነፈው ኢትዮ ኤልክትሪክ በበኩሉ አወት ገ/ሚካኤል እና ጥላሁን ወልዴን በግርማ በቀለ እና ጫላ ድሪባ በመተካት ወደ ሜዳ ገብቷል።

በጨዋታው ባለሜዳዎቹ ድሬዳዋ ከተማዎች ኳስ በመቆጣጠር ወደ ጎል ለመድረስ ሙከራ ሲያደርጉ እንግዶቹ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው ጥብቅ መከላከልን ምርጫቸው አድርገው ነበር። በ5ኛው ደቂቃ ዘነበ ከበደ ከመስመር ያሻማውን አትረም ኳዋሜ ሞክሮ ወደ ወጪ ባወጣበት ኳስ የመጀመሪያ የጎል ሙከራቸውን ያደረጉት ድሬዳዋዎች በርካታ የግብ አጋጣሚ ቢፈጥሩም ጠንካራው የኤሌክትሪክ መከላከልን ሰብረው ጎል ለማስቆጠር ተቸግረዋል። በ17ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳንኤል ያሻማውን ኳስ ወስኑ ማዜ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት፣ በ20ኛው ደቂቃ ሱራፌል ከአትራም የተቀበለውን ኳስ አክርሮ መትቶ የግቡ ብረት የመለሰበት፣ በ36ኛው ደቂቃ ዮሴፍ ዳሙዬ ከመስመር ያሻገራትን ኳስ ወሰኑ ማዜ ለጎል የቀረበች ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው ሱሌይማና አቡ በቀለሉ የያዘበት በተከታታይ በባለሜዳው በኩል የተደረጉ ሙከራዎች ናቸው።

ከመከላከል ባሻገር በመልሶ ማጥቃት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሙከራ ያደረጉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በመጀመርያው አጋማሽ የሚጠቀስ ሙከራ ማድረግ የቻሉት አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን አልሀሰን ከሉሻ ኳስ ይዞ ወደ ፊት በመሄድ ለኃይሌ እሸቱ ያቀበለውን አጥቂው ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት አጋጣሚ የመጀመሪያ ሙከራቸው ነበር። በድሬዳዋ በኩል በ42ኛው ደቂቃ አህመድ ረሺድ ከመስመር በጥሩ ሁኔታ ያሻማውን ኳስ አጥቂው ሀብታሙ ወልዴ በጭንቅላት ገጭቶ  ግብ ጠባቂው በቀላሉ የያዘበት እና በ45ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ወልዴ ያመከነው ኳስ ለእረፍት ከመውጣታቸው በፊት የታዩ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

ከመጀመርያው አጋማሽ ጋር ተመሳሳይ መልክን ይዞ በቀጠለው የሁለተኛው አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ድሬዳዋዎች ጥቂት የማይባሉ የግብ እድሎች ቢፈጥሩም ኢላማቸውን ያልጠበቁ እና የግብ ጠባቂው ሱሌይማና አቡ ሲሳይ በመሆናቸው ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። 50ኛው ደቂቃ ላይ ዘነበ ከበደ ከመስመር ገፍቶ ያመጣውን ኳስ ራሱ አክርሮ መትቶ በተከላካዩ አዲስ ነጋሽ ተጨርፋ ለጥቂት ወደ ውጪ ስትወጣ 53ኛው ደቂቃ መሀል ሜዳ አካባቢ የተሰጠውን የቅጣት ምት አህመድ ረሽድ አሻምቶ በረከት ሳሙኤል ቢሞክርም ለጥቂት ኢላማዋን ሳትጠብቅ ቀርታለች።

ሙሉ ለሙሉ በመከላከል የተጠመዱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ በዚህ ክፍለ ጊዜ ወደ ድሬዳዋ የግብ ክልል በመልሶ ማጥቃት ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። በ56ኛው ደቂቃ አዲስ ነጋሽ ከ አልሀሰን ካሉሻ የተቀበለውን ኳስ አክርሮ መትቶ ወደ ውጪ የወጣ እንዲሁም በግራ መስመር ኃይሌ እሸቱ ከአልሀሰን ጋር በመቀባበል በቀጥታ ወደ ጎል መትቶ የተመለሰበት ኳስ ጥሩ የሚባሉ የጎል ሙከራዎች ነበሩ። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ወሳኝ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት ጫና በፈጠሩት ድሬዎች በኩል ዘነበ ከበደ በግምት ከ35 ሜትር የተገኘውን ቅጣት ምት በቀጥታ መትቶ ለጥቂት የወጣበት፣ በ84ኛው ደቂቃ ያሬድ  ታደስ ከመስመር ያሻማውን ኳስ ዳኛቸው በቀለ በጭንቅላት ገጭቶ ኢላማውን ስቶ የወጣበት እንዲሁም ዳኛቸው በቀለ በአንድ ሁለት ቅብብል እግሩ የገባችውን ኳስ ሞክሮ ሱሌይማን አቡ በቀላሉ የተቆጣጠራት ሙከራዎች የሚጠቀሱ ነበሩ።

ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማ 30 ነጥብ ካላቸው ወላይታ ድቻ እና ወልዋሎ በመቀላቀል 12ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ29 ነጥቦች በነበረበት 14ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል። የድሬዳዋ ወደ 30 ነጥብ ከፍ ማለትን ተከትሎም ወልዲያ በሂሳብ ስሌት መውረዱን አረጋግጧል።

የአሰልጣኞች አስተያየት
ስምዖን ዓባይ – ድሬዳዋ ከተማ
አጠቃላይ እንቅስቃሴያችን ጥሩ አልነበረም። ከመቼው ጊዜ ያነሰ እንቅስቃሴ ነው ያደረግነው ፤ ለኛ ቡድን አይገባንም። በግልም በቡድንም ቲሙ ዛሬ ጥሩ አልነበረም። ስለዚህ  ያንን አምኖ መቀበል ነው። እግር ኳስ የሚታይ ነገር ነው። እኛም ያየነውን ህዝቡም አይቶታል። በእያንዳንዱ ተጨዋች ላይ ያየነው ፐርፎርማንስ በቂና አስተማማኝ አልነበረም። ከዚህ በፊት በሜዳችን በተከታታይ ያደረግነውን ዛሬ ማድረግ አልቻሉም ፤ ቡድኑ በአጠቃላይ ደካማ ነበር። ቀጣዩን ጨዋታ እንዲህ ነው ብዬ አልገምትም። ነገርግን ቡድናችን ዛሬ እንዳየነው ነገ እንደዚህ ይሆናል ብዬ አልገምትም። ከመስራት ወደ ኋላ አንልም ያሉትን ስህተቶች አርመን እስከ መጨረሻ ድረስ ትግል እናደርጋለን።
ቦጋለ ዘውዴ  (ም/ አሰልጣኝ) – ኤሌክትሪክ
የዛሬው ጨዋታ ጥሩ ነው። ሁለታችንም ወራጅ ቀጠና ስጋት ውስጥ እንደመገኘታችን ማሸነፍ ነበር የፈለግነው። ሆኖም ግን ከሜዳ ውጪ አቻ መውጣቱ ጥሩ ነው። በሜዳቸው የማይሸነፉ በመሆናቸው ይህንን ታርጌት አድርገን ነው የመጣነው። ማሸነፍ ካልቻልን አቻ ይዘን ወጥተን ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት የሚያንደረድረንን ነጥብ ማግኘት ነበር ተሳክቶልናል።

መከላከልን የመረጥነው አየር ፀባዩ ከባድ በመሆኑና ቡድኑ በሜዳው ተጭኖ ስለሚጫወት በመከላከል በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት መርጠናል። ቀጣይ ጨዋታ አንድ ብቻ ነው ከሜዳችን ውጪ ያለን ዛሬ ብንሸነፍ ኖር ከባድ ነበር ስለዚህ በዛሬው ውጤት ደስተኛ ነኝ።