ሪፖርት | አዳማ እና አርባምንጭ ነጥብ ተጋርተዋል

አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ በ27ኛው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር የተገናኙት አዳማ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ 1-1 በሆነው ውጤት ተለያይተዋል።

ቡድኖቹ በ26ኛው ሳምንት ካደረጓቸው ጨዋታዎች መጠነኛ ለውጥ አድርገዋል። አዲስ አበባ ላይ በኢትዮጵያ ቡና 1-0 የተሸነፈው አዳማ ከተማ በዚሁ ጨዋታ በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ የወጡትን ጃኮ ፔንዜ እና በረከት ደስታን በጃፋር ደሊል እና ቡልቻ ሹራ ከመተካቱ በቀር ተጨማሪ ለውጥ አላደረገም። በሜዳው ወላይታ ድቻን አስተናግዶ ያለግብ የተለያየው አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ ሶስቱም የቡድን ክፍሎቹ ላይ አንድ አንድ ለውጦች አድርጓል። በዚህም መሰረት ከኃላ አንድነት አዳነን በወንደሰን ሚልኪያስ ፣ አማካይ ክፍል ላይ ምንተስኖት አበራን በአለልኝ አዘነ ከፊት ደግሞ ብርሀኑ አዳሙን በበረከት ደስታ ተክቷል።

ከጨዋታው መጀመር አንስቶ አዳማ ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ማግኘት ችለዋል። ሆኖም ቡድኑ መሀል ለመሀል ለመሰንዘር የሚሞክራቸው ጥቃቶች በአርባምንጩ የአለለኝ አዘነ እና ወንደሰን ሚልኪያስ የተከላካይ አማካይ ቦታ ጥምረት ፍሪያማ ለመሆን አልቻለም። በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎችም አብዛኛው የጨዋታ እንቅስቃሴ በአርባምንጭ አጋማሽ ላይ ያመዘነ ቢሆንም የግብ ሙከራ አልታየበትም። ዳዋ ሁቴሳ 10ኛው ደቂቃ ላይ በግምት ከ20 ሜትር አካባቢ የተሰጠውን ቅጣት ምት በአስደናቂ ሁኔታ መቶ ፂዮን መርዕድ በቅልጥፍና ያወጣበት ኳስ የመጀመሪያ ሙከራ ሆኗል። በቀጣይም አዳማዎች ቀስ በቀስ የጥቃት አቅጣጫቸውን ወደ ቀኝ መስመር የሚያደላ ካደረጉት በኃላ የተሻሉ የግብ አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል። ዳዋ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ አንዳርጋቸው ይልሀቅ ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ ሲወጣበት በ14ኛው ደቂቃ ደግሞ ከክፍት ጨዋታ አንዳርጋቸው ያሻገረውን ሌላ ኳስ በድጋሜ በግንባሩ ቢገጭም ሙከራው በግቡ ቋሚ ተመልሶበታል። 

በአዳማ የኳስ ቁጥጥር ምክንያት በራሳቸው ሜዳ ላይ ለመቆየት የተገደዱት  አርባምንጮች  ሙከራ ለማድረግ 25 ደቂቃዎች ፈጅቶባቸዋል። በዚሁ ደቂቃ በረከት አዲሱ በደረቱ ያበረደለትን ኳስ አለልኝ አዘነ ከሳጥን ውጪ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጓል። ሆኖም ወደ እንዳለ ከበደ አድልቶ ብቸኛውን አጥቂ በረከት አዲሱን መዳረሻ ያደረገው የቡድኑ መልሶ ማጥቃት እምብዛም አመርቂ አልነበረም። ወደ መሀል ሜዳ የተጠጋው የአዳማ ተከላካይ መስመርን አልፎ ለመግባት የሚያስችሉ ክፍተቶች ቢታዩም የአዞዎቹ ጥቃት በቀላሉ በአዳማ ተከላካዮች ሲከሽፍ ይታይ ነበር። በአለልኝ እና ወንደሰን ጥሩ ሽፋን ያገኝ የነበረው የቡድኑ የኃላ ክፍል ግን ለአዳማ አማካዮች ክፍተት ባለመስጠት በጥንቃቄ ሲንቀሳቀስ ቆይቶ 28ኛው ደቂቃ ላይ የሰራው ያለመናበብ ስህተት ዋጋ አስከፍሎታል። በዚህ አጋጣሚ ከሱራፌል ለዳዋ የተሻገረው ኳስ በአዞዎቹ ተከላካዮች ሳይርቅ ቀርቶ ዳዋ በማንም ላልተያዘው ቡልቻ ሹራ አመቻችቶለት ወጣቱ አጥቂ በጥሩ አጨራረስ አዳማን ቀዳሚ አድርጓል።

ከግቡ መቆጠር በኃላ በቀደመው መንገድ ገፍተው መጫወት የተሳናቸው አዳማዎች ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር የበላይነቱን ለአርባምንጭ በመልቀቅ በርከት ያሉ መከራዎች እንዲደረጉባቸው በር ከፍተዋል። ከእረፍት በፊት የነበሩትን የመጨረሻ 10 ደቂቃዎች ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን ቀርበው የማጥቃት ዕድል ያገኙት አዞዎቹ በ34 እና 43ኛው ደቂቃ በፀጋዬ አበራ እና አማኑኤል ጎበና ከሳጥን ውጪ ጠንከር ያሉ ሙከራዎችን አድርገዋል። ጫናቸውን አጠናክረው በመቀጠል 45ኛው ደቂቃ ላይ የማዕዘን ምት ያገኙ ሲሆን የማዕዘን ምቱ በእንዳለ ከበደ ተሻምቶ ተመስገን ካስትሮ በግንባሩ ግብ ሊያስቆጥር ቢቃረብም ሱሊማን መሀመድ ኳሷን ከመስመር ላይ አውጥቶበታል። ሆኖም ከሰከንዶች በኃላ አርባምንጮች በቀኝ መስመር በፀጋዬ አበራ  ከከፈቱት ፈጣን ጥቃት በረከት አዲሱ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ወደ ውጪ ከመውጣቱ በፊት እንዳለ ከበደ አግኝቶ የአቻነቷን ግብ አስቆጥሮ ቡድኖቹ እረፍት ወጥተዋል።

ከእረፍት ሲመለሱ አርባምንጮች ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ጨዋታውን ቢጀምሩም ቀስ በቀስ ግን ወደ መጀመሪያው ጥንቃቄያቸው መመለሳቸው አልቀረም። የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ሲያገኙ በግራ እና ቀኝ አማካይነት በተሰለፉት እንዳለ እና ፀጋዬ ጥቃት ቢሰነዝሩም በቶሎ የመከላከል ቅርፃቸውን ሲይዙ ይታይ ነበር። በመሆኑም ቡድኑ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ የግብ ሙከራ ለማድረግ ረጅም ደቂቃዎችን እንዲጠብቅ ሆኗል። ሙከራዋም 73ኛው ደቂቃ ላይ አለልኝ አዘነ በግራ መስመር ሰብሮ በመግባት ያደረጋት ስትሆን ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥታለች። ነገር ግን አዞዎቹ አሁንም የመስመር ተከላካዮችን ወደ ኃላ እንዲቀሩ በማድረግ እና ለአዳማ ባለተሰጥኦ ተጨዋቾች ክፍተት በማይሰጥ ፈጣን የመከላከል ሽግግር በፍፁም ቅጣት ምት ክልሉ ዙሪያ ጠንካራ አጥር በመገንባቱ ተሳክቶላቸው ታይቷል።

አዳማዎች በሁለተኛውም አጋማሽ የተጋጣሚያቸውን የመከላከል አደረጃጀት ምርጫቸው በሆኑት አጫጭር ቅብብሎች ማስከፈት አልተቻላቸውም። ቡልቻ ሹራ በ51 እና 61ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጋቸው ሙከራዎችም ከረጅም ርቀት የተደረጉ እና ለፂዮን መርዕድ ችግር ያልፈጠሩ ነበሩ። ቡድኑ በተሻለ ሁኔታ ለጎል መቅረብ የቻለው 56ኛው ደቂቃ ላይ ሱሊማን መሀመድ ሁለተኛው ቋሚ ላይ በጣለው የቅጣት ምት በከንዓን ማርክነህ እና ዳዋ ሁቴሳ ሙከራ ሲሆን 67ኛው ደቂቃ ላይ ኢስማኤል ሳንጋር ከአዲስ ህንፃ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ከሳጥን ውስጥ የሞከረው ኢላማውን የጠበቀ ኳስም ተጠቃሽ ነው። ቡድኑ መሀል ለመሀል የሚያደርገውን ጥቃት ኤፍሬም ዘካርያስ እና ሲሳይ ቶሊን ቀይሮ በማስገባት ለማጠናከር ያደረገው ጥረትም ያን ያህል ውጤታማ አልሆነም። ይልቁንም የተሻለ አስፈሪነት ይላበስ የነበረው ከሱሊማን መሀመድ እና ሱራፌል ዳኛቸው ተሻጋሪ ኳሶች የነበረ ቢሆንም እነዚህም ጥረቶች በአርባምንጭ ተከላካዮች መሀል ነፃነት ላላገኘው ዳዋ ሁቴሳ የመጨረሻ የግብ ዕድል የሚፈጥሩ አልነበሩም።

የጨዋታው የመጨረሻ 10 ደቂቃዎች እና ጭማሪዎቹ 6 ደቂቃዎች በውጥረት የተሞሉ ነበሩ። የአዳማዎች ተሻጋሪ ኳሶች የበረከቱበት አርባ ምንጮችም በመልሶ ማጥቃት ክፍተቶችን ሲያገኙ የነበሩባቸው እነዚህ ጊዜያት ሁለት ከባድ ሙከራዎችንም አስተናግደዋል። 84ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ካስትሮ ከተካልኝ ደጀኔ የማዕዘን ምት በግንባሩ ግብ ለማስቆጠር ሲቃረብ ከ4 ደቂቃዎች በኃላ ደግሞ ሙጂብ ቃሲም በተመሳሳይ ከማዕዘን ምት በተሻማ እና በተጨራረፈ ኳስ ያለቀለት ዕድል አግኝቶ አምክኗል። 

ከዚህ ውጪ ግን ትኩረት ይስብ የነበረው ተደጋጋሚ የነበረው የተጨዋቾች ጉዳት ሲሆን ፌደራል ዳኛ ተካልኝ ደጀኔ የቅጣት ምት ውሳኔዎች የማጥቃት ሂደታችንን በማቋረጣቸው በአድቫንቴጅ ሊታለፉልን ይገባ ነበር እንዲሁም ቅጣት ምቶቹን በፍጥነት መጀመር አልተፈቀደልንም በሚሉ ከሁለቱም ቡድኖች ይነሱ የነበሩ ተቃውሞዎች ተበራክተው  ጨዋታው ሌላ ግብ ሳያስተናገድ ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል።

በተመዘገበው ውጤት አዳማ ከተማ ሳምንቱን በድል ያሳለፉትን አባ ጅፋር ፣ ጊዮርጊስ እና መቐለን መቅረብ የሚችልበትን ዕድል ሲያበላሽ  አርባምንጭ ከተማ ነጥቡን 28 አድርሶ በነበረበት የ15ኛ ደረጃ ላይ እንዲቆይ ሆኗል።