ከፍተኛ ሊግ | ባህርዳር ከተማ በግስጋሴው ሲቀጥል ተከታዩ ሽረ እንዳስላሴም አሸንፏል

በ21ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ ጨዋታዎች ተከናውነዋል። ባህርዳር ከተማ በግስጋሴው ሲቀጥል ሽረ እንዳስላሴ በርቀት መከተሉን ቀጥሏል።

ባህርዳር ከተማ 2-0 ነቀምት ከተማ

(በሚካኤል ለገሰ)

የምድብ ሀ መሪ ባህርዳር ከተማ ነቀምት ከተማን አስተናግዶ 2-0 አሸንፏል። በባህርዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም ከወትሮው በተለየ በርካታ ተመልካች በታደመት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን ተጋባዦቹ በተቃራኒው በሚያገኟቸው የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች እና ታይቶ የሚጠፋ አንድ ሁለት ቅብብሎች ታይተዋል። በስታዲየም የተገኙት የባህርዳር ከተማ ደጋዎዎች ዛሬ ከወትሮው በተለየ የተለያዩ ሞዛይኮችን ሲሰሩ የተስተዋለ ሲሆን በተለምዶ ሚስማር ተራ እየተባለ በሚጠራው የደጋፊዎች መቀመጫ በኩል የታየው የድጋፍ አሰጣጥ በከፍተኛ ሊግ ውድድሮች ያልተስተዋለ አይነት ነበር።

በመጀመሪያው አጋማሽ ተጭነው የተጫወቱት ባለሜዳዎቹ ጎል ለማስቆጠር ብዙም ደቂቃ አልጠበቁም። ደረጄ መንግስቴ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ የነቀምት ተከላካዮች ኳሷን በአግባቡ ሳያወጧት በመቅረታቸው ወሰኑ ዓሊ አግኝቷት ኳስ እና መረብን አገናኝቶ ባህርዳርን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከጎሏ መቆጠር በኃላ የተደናገጡ የሚመስሉት ነቀምቶች ተረጋግተው መጫወት ያቃታቸው ሲመስል በተቃራኒው ባህርዳር ከተማዎች ምንም እንኳን በበርካታ ሙከራዎች ባይታጀብም ኳስን በመቆጣጠር ለመጫወት ሞክረዋል። በ36ኛው ደቂቃ ፍቃዱ ወርቁ በግል ጥረቱ ከቀኝ መስመር ኳሷን እየገፋ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ገብቶ ተረጋግቶ በመምታት ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ የመጀመርያው አጋማሽ በባህርዳር 2-0 መሪነት ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ በመጠኑም ቢሆን ተጠናክረው የመጡት ነቀምት ከተማዎች ሁለት ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን በታሪኩ ጎጀሌ አማካኝነት በ60ኛው እና 74ኛው ደቂቃ አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። መሪነታቸው ድፍረት እና ሞራል የሰጣቸው የሚመስሉት ባህርዳር ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ጫናቸውን ቀንሰው የተጫወቱ ሲሆን በሚያገኙዋቸው የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች እና በመስመር ከሚሻገሩ ኳሶች ውጪ እምብዛም ጎል ለማግባት ሲጥሩ አልተስተዋለም።

በ70ኛው ደቂቃ ዳንኤል ኃይሉ ያለቀለት ኳስ ለሙሉቀን ታሪኩ ሰቶት የግቡ ቋሚ የመለሰበት አጋጣሚ በባለሜዳዎቹ በኩል የሚነሳ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሲሆን መሪነታቸውንም ወደ ሶስት ከፍ የምታደርግ አጋጣሚ ነበረች።

የመድን ሜዳ ውሎ

(በአምሀ ተስፋዬ)

ኢትዮጽያ መድን ከአክሱም ከተማ 4:00 ላይ ጨዋታቸውን አከናውነው መድን ከረጅም ሳምንታት በኋላ መድን ወደ ድል የተመለሰበትን የ1-0 ድል አስመዝግቧል። በ8ኛው ደቂቃ በግምት 18ሜትር ላይ አክርሮ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው ምናለ በቀለ ያዳንበት እንዲሁም በ18ኛው ደቂቃ ቢንያም ጌታቸው በአክሱም በኩል ለግብ የቀረበለ ሙከራ ያደረጉ ናቸው። በእንቅስቃሴ ተበልጠው የነበሩት መድኖች ከ20ኛው ደቂቃ በኋላ የተሸለ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉ ሲሆን በግራ መስመር አብዱልከሪም ወርቁ በግራ በኩል ሁለት ተከላካዮችን አልፎ ለታምሩ ባልቻ ያሻገረው ኳስ በቀላሉ ባክኗል። በ30ኛው ደቂቃ ሀብታሙ መንገሻ አግኝቶ ያበከናት የግብ እድልም ተጠቃሽ ነው።

ከዕረፍት መልስ መድኖች ተጭነው መጫወት ሲችሉ በ50ኛው ደቂቃ ታምሩ ባልቻ በቀኝ መስመር እየገፋ የሄደውን ኳስ አክርሮ ቢመታውም የግቡ የግራ አግዳሚ መልሶበታል። በ68ኛው ደቂቃ ታምሩ ባልቻ ያሻማውን ኳስ ከሁለት ተከላካዮች በማፍትለክ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሀብታሙ መንገሻ ብቸኛው ግብ ለመድን አስቆጥሯል። ከግቡ መቆጠር በኋላ አክሱሞች የመሐል ሜዳ ላይ በቁጥር በመብዛት የመድንን ተከላካይ ክፍል ሰብሩ ለመግባት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። በተለየም ስለሺ ዘሪሁን ሲያደርጋቸው የነበረው ጥረት የሚደነቅ ነበር።

መድን ሜዳ በ8:00 ላይ የጀመረው የሽረ እንዳስላሴ እና የወሎ ኮምበልቻ ጨዋታ ብርቱ ፉክክር አስተናግዶ በሽረ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በምድቡ ያለውን ቆይታ ለማረጋገጥ የማሸነፍ አላማ ይዘው የገቡት  ወሎ ኮምቦልቻዎች እና በምድቡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያለውን ሽረን ማግኘቱ ጨዋታውን ተጠባቂ እንዲሆን አስችሎታል። በሁለቱም በኩል ፈጣን እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ 3ኛው ደቂቃ ላይ የሽረው ጅላሉ ሻፊ የመጀመሪያውን ሙከራ ማድረግ ችሏል። በ19ኛው ደቂቃ ላይ ከኋላ ወደፊት የተጣለው ኳስ ልደቱ ለማ የግል ብቃቱን እና ፍጥነቱን በመጠቀም ወደ ግብነት በመለወጥ ሽረ እንደስላሴን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ኮምቦልቻዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ከመስመር ላይ የሚሻሙ ኳሶችን ለመጠቀም ጥረት አድርገዋል። በ25ኛው ደቂቃ ሙሉቀን ወልዴ የሞከረውን ግብ ጠባቂው ሙሴ ያደነበት እንዲሁም ሰለሞን በ30ኛው ደቂቃ ያደረገው  ሙከራም ተጠቃሽ ነበር። በጨዋታው በ31ኛው ደቂቃ ላይ  ከዳኛ እይታ ውጭ ልደቱን ለማን አንገቱን ስር የመታው ሲሆን አጥቂው ልደቱ ራሱን በመሳቱ በእለቱ የነበሩት የጠብታ አምቡላንስ ሰራተኞች እርዳታ በመስጠት በየጨዋታው ላይ ያላቸውን አስፈላጊነት አሳይተው አልፈዋል።

ከእረፍት መልስ ወሎዎች ሙሉ በሙሉ ተጭነው  የተጫወቱት ቢሆንም የአቻነት ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በተለይም ሄኖክ ጥላሁን እና ሳላሂድን ሙሰማ ያደረጉት ሙከራ በኮምቦልቻ በኩል ሲጠቀስ ልደቱ ለማ ያደረገው ሙከራ በሽረ በኩል የሚጠቀስ ነው።

ኢኮስኮ 2-1 አአ ከተማ

(አብርሀም ገ/ማርያም)

አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በ8:00 ኢኮስኮን ከአዲስ አበባ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በኢኮስኮ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በተደጋጋሚ ጨዋታዎች መደራረብ የተጎዳው የአዲስ አበባ ስታድየም ለቅብብል አስቸጋሪ የነበረ ሲሆን ሙሉው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተቀዛቀዘ እንዲሆን አድርጎታል።  ኢኮስኮዎች ቀዳሚ መሆን የቻሉት ገና በ8ኛው ደቂቃ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት በአበበ ታደሰ አማካኝነት በአግባቡ በመጠቀም ነበር። ብዙም ሳይቆይ ይበልጣል ሽባባው በኢኮስኮ የግብ ክልል የመጨረሻ አጥቂው ላይ በሰራው ጥፋት የፍፁም ቅጣት ምት ለአዲስ አበባ ከተማ ሲሰጥ ይበልጣል ባልተጠበቀ ውሳኔ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ውሳኔውን የተቃወሙት ኢኮስኮች ባስመዘገቡት ክስ ጨዋታው ቀጥሎ የፍፁም ቅጣት ምቱን ፍቃዱ ዓለሙ ወደ ግብነት ለውጦ አአ ከተማን አቻ አድርጓል። ቀሪውን 75 ደቂቃ በጎዶሎ ተጫዋቾች ለመጫወት የተገደዱት ኢኮስኮዎች ጎሉ ከተቆጠረባቸው በኋላ በፍጥነት ወደ መሪነት ለመመለስ ከ3 ደቂቃ ጊዜ አልፈጀባቸውም። በ21ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ወደ ሳጥን ይዘው የገቡትን ኳስ አባይህ ፌኖ በጠንካራ ምት በግሩም ሁኔታ ማስቆጠር ችሏል።

ከኢኮስኮ የመሪነት ጎል በኋላ ባሉት ረጅም ደቂቃዎች አዲስ አበባ ከተማዎች ብልጫ መውሰድ ቢችሉም ወደ ማጥቃት ወረዳው ሲደርሱ ውጤታማ የመሆን ችግር ታይቶባቸዋል። ፍቃዱ ዓለሙ በ45ኛው ደቂቃ መሬት ለመሬት መትቶ ለጥቂት የወጣበት እና በ70ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ ሆኖ ሳይደርስበት የቀረው አጋጣሚዎች ሲጠቀሱ ተቀይሮ የገባው ገናናው ረጋሳ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በግምባሩ ገጭቶ በተከላካዩ ዳግም ከመስመር የወጣው ኳስ አአ ከተማን አቻ ሊያደርግ የሚችል አስቆጪ አጋጣሚ ነበር።

ሌሎች ጨዋታዋች …

ፌዴራል ፖሊስን ያስተናገደው ሰበታ ከተማ 3-2 በማሸነፍ ወደመሪዎቹ የተጠጋበትን ውጤት አስመዝግቧል። በ2ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ መሀሪ እንዲሁም በ6ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ ሽብሩ ባስቆጠሯቸው ግቦች ሰበታዎች 2-0 መምራት ቢችሉም በ9ኛው ደቂቃ ሊቁ አልታየ እና በ38ኛው ደቂቃ ሙከሪም አለቱ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ፌዴራሎች አቻ እረፍት ወጥተዋል። ከዕረፍት መልስ ሰበታ ከተማዎች በጌዲዮን ታደሰ አማካኝነት የማሸነፊያውን ግብ በማስቆጠር ጨዋታውን 3-2 አጠናቆዋል። ሱሉልታ ከተማ በሜዳው በደሴ ከተማ 2-1 ተሸንፏል። እንዳለ ዘውገ ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ቢችልም ደሴ ከተማዎች ከእረፍት በፊት ብርሀኑ ተፈራ እና ከእረፍት መልስ ሐብታሙ ገብሬ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 2-1 አሸንፈው ወጥተዋል። የካ ክፍለ ከተማ ቡራዩን አስተናግዶ በሐብታሙ ፍቃዱ ጎል 1-0 ሲያሸንፍ ትላንት በተደረገ ብቸኛ መርሐ ግብር አውስኮድ ለገጣፎን 2-1 አሸንፏል።

ምድብ ለ

በፀጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ጨዋታዎች ወደገሌላ ጊዜ በተሸጋገሩበት ምድብ ለ ዛሬ ሶስት ጨዋታዎች ተደርገዋል። ስልጤ ወራቤ ወደ ድሬዳዋ ተጉዞ ናሽናል ሴሜንትን 3-1 ሲያሸንፍ ቤንች ማጂ ቡና በሜዳው መቂ ከተማን በተመሳሳይ 3-1 ረቷል። ሻሸመኔ ከተማ ከ ቡታጅራ ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በዚህ ምድብ ነገ ሀላባ ከተማ በሜዳው ካፋ ቡናን ሲያስተናግድ ጅማ አባቡና ከደቡብ ፖሊስ፣ ድሬዳዋ ፖሊስ ከ ነገሌ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና ከ ዲላ ከተማ እንዲሁም ወልቂጤ ከተማ ከ ሀምበሪቾ ወደ ሌላ ጊዜ የተሸጋገሩ ጨዋታዎች ናቸው።