” አሁን ጥሩ ስሜት እየተሰማኝ ነው” ሚኪያስ መኮንን

የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ለማድረግ ወደ ካይሮ አቅንቶ የግብፅ አቻውን 3 – 1 በረታበት ጊዜ ሦስተኛውን ጎል በአስደናቂ የግል ብቃት ጎል ካስቆጠረ ጀምሮ የብዙ የስፖርት ቤተሰብ ትኩረት ውስጥ የገባው ሚኪያስ መኮንን ወደ ኢትዮዽያ ቡና ዋናው ቡድን ካደገ በኋላ በዘንድሮ ዓመት በሚሰጠው እድል ደስተኛ እንዳልነበር ጥር 24 ቀን 2010 ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሮ ነበር ። 

“ይህ አመት ለእኔ ጥሩ አይደለም እድገቴን የጎተተ እና ያዘገየብኝ ወቅት ነው። ፈጣን የነበረው እድገቴ መሄድ በሚገባው መጠን ማደግ አልቻለም ፤ ዘግይቷል። ለእድገቴ መዘግየት ደግሞ ችግሩ በእኔ ነው ብዬ አላስብም። የምገኘው በትልቅ ቡድን በመሆኑ የበዛ የመሰለፍ እድል ላላገኝ እንደምችል አምናለው። ሆኖም ግን እኛ ምንም የመሰለፍ እድል ሳይሰጠን ከውጭ እና ከሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ይመጣሉ። እነሱ እስኪታዩ ድረስ የእኛ እድገት ይቀጭጫል። ወደፊት ግን እድሉን እንደማገኝ አምናለው ” ሲል ሁኔታውን ገልፆ የነበረው ሚኪያስ ያለፉት ሳምንታትን በመጀመርያ ተሰላፊነት እየተጫወተ ለቡድኑም ወሳኝ ግልጋሎት እያበረከተ ይገኛል።

ሚኪያስ ስለወቅታዊ አቋሙ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አሁን ከባለፉት ሳምንታት ጀምሮ ተከታታይ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ በመጀመርያ 11 ውስጥ በመካተት አቅም እንዳለህ በማሳየት የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋች መሆን ችለሀል። ከወራት በፊት የነበረውን ስሜት እንዴት ታስታውሰዋለህ ? 

” (እየሳቀ) እውነት ነው ያው በወቅቱ ብዙ ደስ የማያሰኝ ነገሮች ነበሩ። አሁን ግን ብዙ ለውጥ አለ። እንደምታውቀው ያኔ የመጫወት እድል አላገኘሁም፤ 18 ውስጥ ብቻ ነው የምገባው። አሁን ደግሞ ነገሮች ተቀይረው ቡድናችን ውጤት እያመጣ እኔም በቡድኑ ውስጥ የመሰለፍ እድል አግኝቼ ጥሩ እየተንቀሳቀስኩ አሁን ያለው ነገር መልካም ነው።

የመጫወት እድል ያገኘሁት ለምንድነው ብለህ ታስባለህ?

የመጀመርያው አሰልጣኙ ዲዲዬ ጎሜስ ነው ብዬ የማስበው። ለአንድ ተጨዋች እድገት አሰልጣኝ ትልቅ ድርሻ አለው። መጀመርያም ወደ 18 ውስጥ ያስገባኝ እርሱ ነው። በሂደት ደግሞ አቅሜን አውቆ እምነት ጥሎብኝ እያጫወተኝ ይገኛል ።  በመቀጠል የቡድን ጓደኞቼ ሁሌም ከጎኔ ናቸው። እያበረታቱ ፣ እየመከሩ እዚህ እንድደርስ ረድተውኛል ።

አሁን በየጨዋታዎቹ አቅምህን እያሳየህ ነው ምን አይነት ስሜት ይሰማሀል?

አሁን ትልቅ ተስፋ ይታየኛል፤ ነገ ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደምችል አስባለው። መጫወት በቻልኩ ቁጥር ራሴን እያሳደግኩ እሄዳለው። የመጫወት እድል ሳላገኝ ተቀምጬ ሌሎች ተጨዋቾች ይመጣሉ እነርሱ እስኪታዩ ብዙ የመጫወት እድል ያልፈናል። በዚህ ደግሞ አቋምህ ሊወርድ ይችላል ፣ ተስፋ የመቁረጥ ነገር ይመጣል፣ በአሰልጣኞች የመፈለግህ ዕድል ይጠባል። አሁን ያ ሁሉ ነገር አልፎ መጫወት ስትችል እና በእዚህ በርካታ ደጋፊ ባለው ትልቅ ክለብ ውስጥ ገብቶ መጫወት በራሱ በራስ መተማመንህን ይጨምረዋል። አሁን ጥሩ ስሜት ነው እየተሰማኝ ያለው በጣም ደስተኛ ነኝ።

ቀጣይ ምን ታስባለህ…

አሁን በኢትዮዽያ ቡና ደስተኛ ነኝ፤ በእዚህ ዕድሜዬም በዚህ ክለብ መጫወት በራሱ ትልቅ ነገር ነው ። አሁን የዋንጫ ፉክክር ውስጥ ገብተናል፤ የማንንም ጨዋታ ውጤት ሳንጠብቅ ቀሪ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ዋንጫውን ማንሳት አንድ እና አንድ እቅዳችን ነው ። ከዚህ በተረፈ ጠንክሬ በመስራት አቅሜን ማሳደግና ለዋናው የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን መጫወት ትልቁ ህልሜ ነው።