የአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ድንገተኛ አሟሟት መንስዔ በቅርቡ ይፋ ይደረጋል

አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ዜና እረፍታቸው ከተሰማ ዛሬ 15ኛ ቀን ሆኖታል። እስካሁንም የድንገተኛ ህልፈታቸው መንስኤ ምን እንደሆነ በይፋ የታወቀ ነገር የለም። 

እስካሁን ምክንያቱ አለመታወቁ ለምን እንደሆነ ጥያቄ በመያዝ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታን የአሟሟት ጉዳይ እየተከታተለ ከሚገኘው የደደቢት እግርኳስ ክለብ ባገኘነው ምላሽ መሰረት በአሁኑ ሰዓት የአሟሟቱን ሁኔታ ለማወቅ በሀገር ውስጥ የሚገኝ የመመርመርያ መሳርያ የሌለ በመሆኑ ናሙናው ወደ እንግሊዝ ሀገር እንደተላከ እና በቅርቡ የምርመራውን ውጤት ጎፋ የሚገኘው የፖሊስ መምሪያ እንዳሳወቀ ለህዝቡ ይፋ እንደሚያደርጉ ተነግሮናል።

የቀድሞ የምድር ጦር ተጫዋች እና በመከላከያ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ደደቢት እና ወልዲያ በአሰልጣኝነት የሰሩት አሰልጣኝ ንጉሴ በድጋሚ  ወደ ደደቢት ከ2010 ጀምሮ በመመለስ በመስራት ላይ እያሉ ነበር ግንቦት 28 በዕለተ ማክሰኞ ምሽት 04:00 ገደማ ከጓደኞቸቻው ጋር በነበሩበት ሰዓት በተሰማቸው የህመም ስሜት ወደ ሆስፒታል ካመሩ በኋላ ህይወታቸው ያለፈው ። ስርአተ ቀብራቸውም ወዳጅ ዘመድ በተገኘበት በትውልድ ስፍራቸው ማይጨው ግንቦት 29 ቀን መፈፀሙ ይታወሳል ።