የ28ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ተሸጋግረዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ28ኛ ሳምንት መደበኛ መርሐ ግብር በተስተካካይ ጨዋታዎች ተተክተዋል።

ከ23ኛው ሳምንት ጀምሮ ያለተስተካካይ ጨዋታዎች ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባሳለፍናቸው ሶስት ሳምንታት ከአቅም በላይ በሆኑ ችግሮች ምክንያት ሶስት ጨዋታዎችን በይደር ለማቆየት እንደተገደደ ይታወቃል። እነዚህም በ25ኛው ሳምንት በአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ህልፈት ምክንያት ያልተደረገው የደደቢት እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ እንዲሁም ባሳለፍነው ሳምንት ከፀጥታ ጋር በተያያዙ ችግሮች የተላለፉት የቦዲቲው የወላይታ ድቻ እና ወልዋሎ ዓ.ዩ እንዲሁም የሀዋሳ ከተማ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታዎች ናቸው።

ከሰዐታት በፊት ባስነበብነው ዜና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታዎቹ በቅድሚያ እንዲከናወኑ መጠየቁ የሚታወስ ሲሆን የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የሊግ ኮሚቴ ዛሬ ያደረገው ስብሰባም እነዚሁኑ መርሀ ግብሮች የተመለከተ ነበር። በስብሰባውም በክለቦች መሀከል ሊኖር የሚችለውን የውጤት መጠባበቅ ለማስቀረት በማሰብ የ28ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ከመካሄዳቸው አስቀድሞ ሦስቱ ጨዋታዎች እንድደረጉ ወስኗል። በዚህም መሰረት ሁሉም ጨዋታዎች በመጪው ሰኞ ሰኔ 18 በ09፡00 የሚደረጉ ሲሆን የ28ኛ ሳምንት መርሀ ግብር የሚከናወንበት ቀን ወደፊት የሚገለፅ ይሆናል።