የካፍ ኢንስትራክተር አብርሃም ተ/ሃይማኖት ሁለተኛ መፅሀፍ ተመረቀ

“እግር ኳሳችን እና የኃሊት ርምጃው” የተሰኘው መፅሀፍ ትናንት በመቐለ ከተማ አክሱም ሆቴል የክልሉ የስፖርት ሃላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ የክብር እንግዶች በተገኙበት በተደረገ ስነ-ስርአት ተመርቋል። 

ባለፈው ሳምንት ሰኔ 2 በአዲስ አበባ ከተማ በይፋ የተመረቀው ይህ የኢንስትራክተር አብርሀም ተ/ሃይማኖት መፅሃፍ 6 ምዕራፎች እና 248 ገፆች ሲኖሩት በኢትዬጽያ እግር ኳስ ችግሮች እና መፍትሄ ሃሳቦች ላይ ያተኮረ እንደሆነ አሰልጣኙ ተናግረዋል። መፅሃፋ ምረቃ ወቅት ሰፊ የመክፈቻ ንግግር ያረጉት አሰልጣኙ እግር ኳስ የአካል ብቃት ብቻ ሳይሆን የአዕምሮም ስራ መሆኑን አብራርተው ይህን ለማገዝ በማሰብም መፅሃፉን እንደፃፉት ገልፀዋል። አግራሞትን በፈጠረው ተጨማሪ ሀሳባቸውም በአሰልጣኝነት ወይም በሌላ የእግር ኳስ ሙያ ላይ ብሆን ኖሮ መፅሃፋን ባስመረቅሁ ማግስት የመባረር እጣ ይደርሰኝ ነበር ብለዋል።

1981 ዓ.ም በምድር ባቡር የአሰልጣኝነት ስራቸው የጀመሩት ኢንስትራክተር አብርሃም ባለፋት ዓመታት ከክለብ አሰልጣኝነት ራሳቸውን ካገለሉ በኃላ በአዲስ አበባ እና መቐለ ከተማዎች በከፈቷቸው የህፃናት የእግር ኳስ ትምህርት ቤቶች 150 ታዳጊዎችን ይዘው እየሰሩ እንደሆነ ይታወቃል።