ሩሲያ 2018 | ሴኔጋል (የቴራንጋ አናብስት)

በሩሲያ አስተናጋጅነት በቀጠለው የዓለም ዋንጫ አሁንም አፍሪካን የወከሉት ቡድኖች ድል ርቋቸዋል። ዛሬ ከፖላንድ ጋር በምታደርገው ጨዋታ ጉዞዋን የምትጀምረው ሴኔጋልን የዓለም ዋንጫ ጉዞ ተስፋ እና ስጋት እንዲህ አቅርበናል።

ሴኔጋል ከ16 ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫው ተመልሳለች። በካንሰር ህመም ምክንያት አሁን በህይወት በሌሉት ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ብሩኖ ሜትሶ እየተመሩ የቴራንጋ አናብስቱ በመጀመሪያ ተሳትፏቸው እስከሩብ ፍፃሜ የዘለቀ ድንቅ ጉዞን አድርገዋል። ያን ግዜ የብሄራዊ ቡድኑ አምበል የነበረው አሊዩ ሲሴ አሁን ደግሞ በአሰልጣኝነት ቡድኑን እየመራ ወደ ዓለም ዋንጫው መልሷል።

ተስፋ

ሴኔጋል በልምድ እና ተስጥኦ የታጨቀ የቡድን ስብስብ ባለቤት ነች። በፊት መስመር ላይ ያሉት ተጨዋቾች ያላቸው ፍጥነት እና ክህሎት ቡድኑ ረጅም ጉዞ እንዲጓዝ ሊያግዘው ይችላል። ሙሳ ሶው፣ ኬታ ባልዴ እና ሳዲዮ ማኔን ያካተተው ይህ ስብስብ ለየትኛውም ቡድን ፈተና እንደሚሆን የታወቀ ነው። በተለየ በእንግሊዝ መልካም ግዜያትን ያሳለፈው ማኔ ይህንን ብቃቱን በዓለም ዋንጫው መድገም ከቻለ ለሴኔጋል ጥሩ ነው። ኮያቴ እና ጋይ ለተከላካዮች ሽፋን በመስጠት የአማካይ ክፍሉን ማጠናከራቸው ለሴኔጋል ጉዞ ማማር ቁልፍ ሚናን ሊጫወቱ ይችላሉ። የተከላካይ ክፍሉ በተለይም የመሃል ተከላካዮቹ መልካም የሚባል የውድድር ዘመንን ማሳለፈቸው እንዲሁም በጣሊያኑ ታክቲሻን ማውሪዚዮ ሳሪ ስር በናፓሊ የሰለጠነው ካሊዱ ኩሊባሊ በታክቲክ አረዳድ መብሰሉ ለቴራንጋ አናብስት ተስፋ እንዲሰንቁ ያስችላቸዋል። የተደለደሉበት ምድብን ስንመለከትም ወደ ጥሎ ማለፉ ሊያሳልፋቸው የሚችሉበት ውጤት ሊያስመዘግቡ ይችላሉ። ልምድ ወሳኝ ቢሆንም የ2002 ገድል ተጨዋቾቹን ለሌላ ትልቅ ውጤት ሊያነሳሳቸው ይችላል። የ2002 ስብስብ ሩብ ፍፃሜ ድረስ ሲጓዝ በመጀመሪያ ተሳትፎው እንደነበር የሚታወስ ነው።


የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት – 2 (2002 እና 2018)

የሚጠቀስ ውጤት – ሩብ ፍፃሜ (2002)


ስጋት

አሊዩ ሲሴ ለቡድኑ የሚሆን የጨዋታ ስልት ለማግኘት የቻለ አይመስልም። በተደጋጋሚ የቅርፅ ለውጦችን ለማምጣት መሞከሩ መልካም ቢሆንም ፍሬ አለማፍራቱ ግን አሉታዊ ጎን አለው። ይህ የሲሴን በትልቅ ውድድር ላይ የመምራት ብቃቱን ጥያቄ ምልክት ውስጥ ያስገባል። በተለያዩ ግዜያትም በታክቲካዊ ብስለቱ ላይ ጥያቄ ቢነሳም ሲሴ ከ2015 ወዲህ መሻሻሎችን ማሳየቱን ፈፅሞ መካድ አይቻልም። ቡድኑ ፈጣሪ አማካይ ይጎለዋል። ቡድኑ ባለፉት ጥቂት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ግብ ለማስቆጠር ተቸግሯል። ቀለል ያለች ተጋጣሚ ነች ተብላ በብዙዎች የምትገመተው ሉክሰምበርግ ላይ እንኳን ሴኔጋሎች ግብ አላስቆጠሩም። ይህ ወቅታዊ ደካማ አቋም በዓለም ዋንጫው መደገም የለበትም።

*ሴኔጋል ፖላንድን በመግጠም የዓለም ዋንጫ ጉዞዋን ትጀምራለች።

ሙሉ ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

አብዱላሂ ዲያሎ (ሬን/ፈረንሳይ)፣ አልፍሬድ ጎሜዝ (ስፓል/ጣሊያን)፣ ካዲም ንዳዬ (ሆሮያ አትሌቲክ/ጊኒ)

ተከላካዮች

ካሊዱ ኩሊባሊ (ናፓሊ/ጣሊያን)፣ ላሚን ጋሳማ (አላንያስፓር/ቱርክ)፣ ሳሊዩ ሲስ (ቫለንሲየንስ/ፈረንሳይ)፣ ካራ ምቦዲ (አንደርሌክት/ቤልጂየም)፣ የሱፍ ሳባሊ (ቦርዶ/ፈረንሳይ)፣ዠየ ሳሊፍ ሳኔ (ሻልክ 04/ጀርመን)፣ ሙሳ ዋጉ (ዩፒን/ቤልጂየም)

አማካዮች

ቼኮ ኮያቴ (ዌስትሃም ዩናይትድ/እንግሊዝ)፣ ኢድሪሳ ጋይ (ኤቨርተን/እንግሊዝ)፣ አልፍሬድ ንድዬ (ወልቨርሃምፕተን ዎንድረርስ/እንግሊዝ)፣ ባዱ ንዳዬ(ስቶክ ሲቲ/እንግሊዝ)፣ ቼክ ንዶዬ (በርሚንገሃም ሲቲ/እንግሊዝ)፣ እስማኤላ ሳር (ሬን/ፈረንሳይ)

አጥቂዎች

ኬይታ ባልዴ ዲያዎ (ሞናኮ/ፈረንሳይ)፣ ማሜ ቢራም ዲዩፍ (ስቶክ ሲቲ/እንግሊዝ)፣ ሙሳ ኮናቴ (ኤሚየን/ፈረንሳይ)፣ ሳዲዮ ማኔ (ሊቨርፑል/እንግሊዝ)፣ ምባዬ ንያንግ (ቶሪኖ/ጣሊያን)፣ ዲያፍራ ሳኮ (ሬን/ፈረንሳይ)፣ ሙሳ ሶ (ቦራስፖር/ቱርክ)