ኢትዮጵያ ቡና ወደ ኢትዮጵያ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ተሸጋግሯል

በኢትዮጵያ ዋንጫ ዛሬ በተደረገው ብቸኛ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማን ከኢትዮጵያ ቡና ያገናኘው ጨዋታ እስከ መለያ ምት ድረስ አቅንቶ በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከወትሮው ተቀዛቅዞ በታየው የሁለቱ ክለቦች የደጋፊዎች ድባብ እና በከፍተኛ የቡድኖቹ ፉክክር በታጀበው ጨዋታ አርባምንጭ በስብስቡ በርካታ ለውጦችን ይዞ ሲገባ ኢትዮጵያ ቡና ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስችል ሁኔታ ዋና ስብስቡን ተጠቅሟል።

ጨዋታው ገና ከመጀመሩ ነበር ኢትዮጵያ ቡናዎች የአርባምንጭ ከተማን የግብ ክልል መድፈር የጀመሩት። በሁለተኛው ደቂቃ አንድነት አዳነ በባፕቲስቴ ፋዬ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ቅጣት ምት ሳምሶን ጥላሁን መቶ አንተነህ መሳ አድኖበታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ አርባምንጭ ከተማዎች ጎላቸውን ላለማስደፈር ሲጠነቀቁ ቆይተው 6ኛ ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ወደ ቡና የግብ ክልል በመድረስ ታገል አበበ ለማሻማት ያሻገረው ኳስ ወደ ግብ ሄዳ በኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂ ሃሪሰን የተያዘበት ሙከራ የባለሜዳዎቹ የመጀመርያ ሙከራ ሆኗል። ጨዋታው በጥሩ እንቅስቃሴ ቀጥሎ ኢትዮጵያ ቡናዎች በተደጋጋሚ ወደ ግብ ሲደርሱ ታይተዋል። 11ኛ ደቂቃ ላይ ታሪኩ ኮራቶ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ ሳኑሚ አገባ ተብሎ ሲጠበቅ ኳሷን ከግቡ አናት ላይ የላካት ኳስም ተጠቃሽ ነበረች። ኢትዮጵያ ቡናዎች የአርባምንጭ ከተማዎችን አለመረጋጋት ተመልክተው በተደጋጋሚ የተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል ሲፈትሹ ቆይተው በ16ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂው አንተነህ መሳና አንድነት አዳነ በፈጠሩት አለመናበብ ተጠቅሞ ባፕቲስቴ ፋዬ በፊት ለፊት እግሩ መትቶ ቡናን ቀዳሚ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል።

ከጎሉ በኋላ ባለው የጨዋታ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ቡናዎች ቀስ በቀስ ሲቀዛቀዙ በአንፃሩ አርባምንጭ ከተማዎች የቡናን የግብ ክልል ፈትሸዋል። 33ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል ከታሪኩ ኮራቶ የተሻገረውን ኳስ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ከጋሞ ጨንቻ አርባምንጭን የተቀላቀለው ፍቃዱ መኮንን የግል ችሎታውን ተጠቅሞ በአርባምንጭ ከተማ የመጀመሪያውን ጎል በማስቆጠር ቡድኑን አቻ አድርጓል።

አርባምንጭ ከተማዎች ከጎሉ በኋላም ጫና ለመፍጠር በማሰብ በመስመር ላይ ያደላ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የመጀመርያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊትም በዘካርያስ ፍቅሬ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ አድርገው የግቡን ቋሚ ታካ ወጥታለች። ሳኑሚ በአንድ ሁለት ቅብብል ኳሷን ይዞ ወደ ሳጥን ሲገባ አንድነት ተንሸራትቶ ያወጣበትና የመሐል ዳኛው ሳኑሚ የማጭበርበር ሙከራ አድርጓል በሚል የማስጠንቀቂያ ካርድ የመዘዙበት ክስተት በመጀመርያው አጋማሽ የሚጠቀስ ነው።

የተቀዘቀዘ እንቅስቃሴ በታየበት በሁለተኛው አጋማሽ የግብ ሙከራዎች የታዩት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ነበር። አርባምንጮች በመልሶ ማጥቃት ያልተሳካ የግብ እድል የመፍጠር ሙከራ ሲያደርጉ ኢትዮጵያ ቡናዎችም አልፎ አልፎ በሳሙኤል ሳኑሚ እና በሚኪያስ መኮንን ከመስመር የሚሻገሩ ኳሶች እምብዛም የተሳኩ አልነበሩም። የመጨረሻዎቹ 7 ደቂቃዎች ግን ኢትዮጵያ ቡናን ወደ አሸናፊነት ለማሸጋገር የተቃረቡ ሙከራዎች ተደርገዋል። 84ኛ ደቂቃ ላይ መስዑድ ከረጅም ርቀት አክርሮ መቶ በግቡ አናት የወጣበት ፣ 88ኛ ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ሳኑሚ ቡቻውን ይዞ ገብቶ በአንተነህ መሳ ተጨርፎበት እንደገና ፋኖ በተመቻቸ ቦታ ላይ ሆኖ ኳሷን ተቆጣጥሮ ወደ ግቡ ሲመታ አንድነት በግሩም ሁኔታ በግምባሩ ገጭቶ ያወጣው እንዲሁም ሚኪያስ አሁንም ብቻውን ወደ ግብ ክልሉ በመሄድ ግብ ጠባቂውን ሲሸውድ ከእግሩ አምልጦት ኤሊያስ ኳሷን አግኝቶ ሲሞክር ለጥቂት የወጣበት ሙከራዎች የሚያስቆጩ ነበሩ።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 1ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቆ ወደ መለያ ምት አቅንቷል። መለያ ምቱንም ኢትዮጵያ ቡናዎች 4-3 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜው መሸጋገር ችለዋል።

የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ዲድዬ ጎሜስ

” ከስድስት አመት በኋላ ዋንጫ ለማንሳት ነው የምንጫወተው። በውጤቱ በጣም ደስተኛ ሆኛለሁ። ሙሉ ትኩረት ያደረግነው ግን ከሀዋሳ ጋር ለምናደርገው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ነው። ተጫዋቾቼ በጥሩ ስሜት ላይ መሆናቸው አስደስቶኛል”

*የአርባምንጭ ከተማ አሰልጣኞች አስተያየት አልሰጡም