በኢትዮጵያ ዋንጫ መከላከያ፣ ኤሌክትሪክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሩብ ፍፃሜ አልፈዋል

የኢትዮጵያ ዋንጫ በዛሬው እለት ሶስት የመጀመርያው ዙር ጨዋታዎችን በአዲስ አበባ ስታድየም አስተናግዶ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኤሌክትሪክ እና መከላከያ ወደ ሩብ ፍፃሜ የተሸጋገሩበትን ድል አስመዝግበዋል።

የዛሬ የአዲሰ አበባ ስታድየም ጨዋታዎችን በዚህ መልኩ ተመልክተናቸዋል

መከላከያ 3-2 ድሬዳዋ ከተማ

(በአምሀ ተስፋዬ)

04:00 ላይ የጀመረው ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር እና በርካታ ጎሎችን አስተናግዶ በመከላከያ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ ወደ ግብ የደረሱት ድሬዳዋዎች ነበሩ። 7ኛው ደቂቃ ላይ ዳኛቸው በቀለ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ በመግባት ወደግብ አክርሮ የመታት ኳስ የግቡን አግዳሚ ታካ የወጣችበት እንዲሁም በ15ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ሞክሮ ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ያደንበት ለዚህ ተጠቃሽ ነበሩ። መከላከያዎች በሁለቱ የፊት አጥቂዎቻቸው የድሬዎችን የተከላካይ መስመር በመለጠጥ በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ የተጣመሩት ዘሪሁን እና ያሬድን ለተደጋጋሚ ስህተት ሲያጋልጡ ተስተውሏል። በ19ኛው ደቂቃ አቅሌስያስ ግርማ በቀኝ መስመር እየገፋ ወደ ግቡ በሚያጠብበት ወቅት በሳጥን ውስጥ ጥፋት በመፈፀሙ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ፍፁም ገብረማርያም ወደግብነት ለውጦታል።

የመከላከያ መሪነት የዘለቀው ለ5 ደቂቃዎች ብቻ ነበር። በ24ኛው ደቂቃ ላይ ዳኛቸው በቀለ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ በተረጋጋ ሁኔታ አንድ ተጫዋች በማለፍ ድሬዳዋ ከተማን አቻ አድርጓል። ከአቻነት ጎሉ በኋላ የድሬዳዋ ከተማ የተከላካይ መስመር ለስህተት ይበልጥ የተጋለጠ ሆኖ ታይቷል። በ34ኛው ደቂቃም ሳውሬል ኦልሪሽ የሰራውን ስህተት በመጠቀም በቀላሉ ወደፊት የሄደውን ኳስ ፍፁሞ በአግባቡ ተጠቅሞ መከላከያን በድጋሚ መሪ አድርጓል። ፍፁም በፍጥነት ሐት-ትሪክ ሊሰራባቸው የሚችልበቸውን አድሎች ቢያገኝም አንደኛው ኢላማውን ስቶ ወደ ውጪ ሲወጣበት ሌላኛውን ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሯል። በቀላሉ ወደ ድሬዳዋ የግብ ክልል ሲደርሱ የነበሩት መከላከያዎች የመጀመርያውን አጋማሽ ያሳረጉት በ38ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት ሳሙኤል ታዬ በማራኪ ሁኔታ ኳስን አገናኝቶ 3-1 በመምራት ነበር።


ከእረፍት መልስ በእጅጉ ተሻሽለው የቀረቡት ድሬዳዋ ከተማዎች በርካታ የግብ እድሎችን በመፍጠር ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርገዋል። በ65ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ዳኛቸው በቀለ በግንባሩ በመግጨት የጎል ልዩነቱን ማጥበብ ችሏል። በቀሪዎቹ ደቂቃዋች የአቻነት ግብ ፍለጋ ወደፊት ተጭነው ለመጫወት የሞከሩት ድሬዎች እንደ ብልጫቸው ግልፅ የግብ እድል መፍጠር ሳይችሉ ጨዋታው በመከላካያ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። በቀጣይ መከላከያ አዳማን ከውድድር ካስወጣው ፋሲል ከተማ ጋር የሩብ ፍፃሜ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ 0-0 (4-2) መቐለ ከተማ

(በዮናታን ሙሉጌታ)

9፡00 ላይ በጀመረው በዚህ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በርከት ያሉ ተጠባባቂ ተጨዋቾቹን ሲጠቀም መቐለ ከተማ በበኩሉ በአመዛኙ የተለመደውን የመጀመሪያ ስብስቡን ወደ ሜዳ አስገብቷል። በዚህ መሰረት የኢትዮ ኤሌክትሪኮቹ ዮሀንስ በዛብህ ፣ ሰይዱ አብዱልፈታ ፣ ዳንኤል ራህመቶ እና ምንያህል ይመር ቆየት ካለ ጊዜ በኃላ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ መካተት ሲችሉ በመቐለ ከተማ በኩል የተለየ የነበረው የአማኑኤል ገ/ሚካኤል አለመሰለፍ ነበር።

በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኖቹ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ያሳዩ ቢሆንም ጨዋታው በበርካታ የግብ ሙከራዎች የታጀበ አልነበረም። እምብዛም የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ያልነበራቸው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ፈጠን ባለ መንገድ ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክሩ ይታዩ የነበረ ቢሆንም የተሻሉ የሚባሉት የግብ ሙከራዎቻቸው ሁለት ብቻ ነበሩ። 8ኛው ደቂቃ ላይ በብቸኛ አጥቂነት የተሰለፈው ኃይሌ እሸቱ ከተክሉ ታፈሰ ጋር በመቀባበል ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ወደ ግብ የሞከረው እና 33ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ አኳኋን ስንታየሁ ዋለጬ ከርቀት ያደረገው ሌላ ሙከራም ፍሊፕ ኢቮኖን ያልፈተኑ ነበሩ። ከአቼምፖንግ አሞስ የ21ኛ ደቂቃ የርቀት ሙከራ ውጪ ሌላ ሙከራ ሳያደርጉ ወደ እረፍት ያመሩት መቐለዎችም ወደ ኑሁ ፉሰይኒ አድልተው ለመሰንዘር ይሞክሩት የነበረው ጥቃት እምብዛም አስፈሪ አልነበረም። ቡድኑ በተወሰኑ አጋጣሚዎች በተጋጣሚው ሳጥን ውስጥ የተገኘባቸው ቅፅበቶች ቢኖሩም የመጨረሻ ዕድል መፍጠር ግን አልቻለም።


ከዕረፍት መልስ መቐለዎች አንፃራዊ ጥንካሬ ታይቶባቸዋል። ተጋጣሚያቸው ወደ ኃላ እንዲያፈገፍግ ማስገደድ በቻሉባቸው የሁለተኛ አጋማሽ ደቂቃዎች ግን እንደመጀመሪያው ሁሉ ሰብረው ወደ ውስጥ መግባት ተስኗቸዋል። 63ኛው ደቂቃ ላይ ካርሎስ ዳምጠው ከርቀት በቅጣት ምት እስካደረገው ሙከራ ድረስም ቡድኑ ሌላ አጋጣሚ ሳይፈጥር ቀርቷል። በኃይሉ ተሻገር እና አዲስ ነጋሽን ቀይተው ካስገቡ በኃላ የተፈጠረባቸውን ጫና በተወሰነ መልኩ ማቃለል የቻሉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮችም በማጥቃቱ በኩል ግን እጅግ ተዳክመው ነበር። የቡድኑ አብዛኞቹ ጥረቶች መሀል ሜዳ ላይ ከሚታዩ የተቆራረጡ ቅብብሎች ሳይልፍ ነበር መደበኛው 90 ደቂቃ የተጠናቀቀው። ሆኖም ወደ መጨረሻው ላይ ወደ ፊት አጥቂነት የመጣው የመቐለው ቀኝ መስመር ተከላካይ አቼምፖንግ አሞስ በጭማሪ ደቂቃ ከአሸናፊ ሀፍቱ የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር። በዚህ መልኩ ያለግብ የተጠናቀቀው ጨዋታ ወደ መለያ ምቶች አምርቶ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የመጀመሪያዎቹን አራት ምቶች ወደ ግብነት ሲቀይር በመቐለ በኩል ግን ኑሁ ፉሰይኒ እና አቼምፖንግ አሞስ በመሳታቸው ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተጠናቋል። በውጤቱም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደደቢትን በፎርፌ ካለፈው ጅማ አባ ጅፋር ጋር በሩብ ፍፃሜው ይገናኛል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ወላይታ ድቻ

(በዮናታን ሙሉጌታ)

ቅዱስ ጊይርጊስ በአመዛኙ ሰሞንኛ ቡድኑ ይዞ ነበር ጨዋታውን ያከናወነው። በዚህ ረገድ የአበባው ቡታቆ ፣ ምንተስኖት አዳነ ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና አቡበከር ሳኒ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ መምጣት ብቻ እንደለወጥ የሚቆጠር ነው። የአምናዎቹ ሻምፒዮኖች ወላይታ ድቻዎች በተቃራኒው በርከት ያሉ ለውጦች አድርገዋል። በዚህም ታዲዮስ ወልዴ ፣ በረከት ወልዴ ፣ ፀጋዬ ባልቻ ፣ ዮናታን ከበደ እና ተመስገን ዳባ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ መምጣት ችለዋል።


ጫን ብለው ጨዋታውን የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አብዛኛውን የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ በበላይነት አሳልፈዋል። ሆኖም ኳስ ይዘው በድቻ የሜዳ አጋማሽ ላይ እንደመቆየታቸው ሳይሆን ብዙዎቹ ሙከራዎቻቸው ከመስመር አማካዮቻቸው እንዲሁም ከአበባው ቡታቆ ከሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች የተገኙ ነበሩ። ከዚህ ውጪ ቡድኑ የቆሙ ኳሶች ዕድሎችን ባገኘባቸው አጋጣሚዎችም አስፈሪነቱን ሲያሳይ ቆይቷል። በ3ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ሳላዲን ባርጌቾ በግንባሩ በሞከረው ኳስ ይህን ጥንካሬዉን ማሳየት የጀመረው ጊዮርጊስ 11ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት አዳነ በተመሳሳይ አጋጣሚ ያገኘውን ኳስ ሲያስቆጥር ቀዳሚ መሆን ችሏል። 21ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉአለም መስፍን ያደረገው የቡድኑ ሌላ ሙከራም እንዲሁ ከማዕዘን ምት ተነስቶ በግንባር የተገጨ ነበር። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የተሻለ ተነቃቅተው የነበሩት ድቻዎች ግን ይህ ነው የሚባል የግብ ዕድል አልፈጠሩም። የተሻለ ሆኖ ከታየው አማካይ አብዱልሰመድ አሊ ይነሱ የነበሩ ኳሶችም በአግባቡ ወደ መጨረሻ ዕድልነት አልተቀየሩም። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ወቅት ድቻዎች አንዴ 3 ለ 1 በሌላ ዕድል ደግሞ 3 ለ 2 ሆነው በጊዮርጊስ ሜዳ ላይ የተገኙባቸውን የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችም ሳይጠቀሙ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወላይታ ድቻዎች በማጥቃት ፍላጎታቸው ተሽልሽለው ታይተዋል። ሆኖም የቅዱስ ጊዮርጊስን የአማካይ ክፍል አልፈው ለመግባት በእጅጉ ተፈትነዋል። ለፊት አጥቂው ተመስገን ዱባ የሚደርሱ ኳሶችም ከሮበርት ጋር ፊት ለፊት የሚገናኙት አልሆኑም። 58ኛው ደቂቃ ላይ ዮናታን ከበደ ካሻገረለት እንዲሁም 83ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ያሬድ ዳዊት ካሻማው ቅጣት ምት ሙከራዎችን ያደረገው ተመስገን ኢላማውን መጠበቅ ሳይችል ቀርቷል። እንደመጀመሪያው ከተሻጋሪ ኳሶች ይልቅ በመልሶ ማጥቃት በርከት ያሉ ዕድሎችን ያገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶችም ተጨማሪ ግብ ባያስቆጥሩም በምንተስኖት ብቸኛ ጎል ጨዋታውን ማሸነፋቸው አልቀረም። ቡድኑ ከፈጠራቸው አጋጣሚዎች መሀከል 64ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት አዳነ ከአበባው የደረሰውን ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ሞክሮ ወንድወሰን ያወጣበት እንዲሁም 75ኛው ደቂቃ ላይ አሜ መሀመድ በግራ መስመር ሰብሮ በመግባት የሞከረው እና ኢላማውን ያልጠበቀው ኳስ ተጨቃሾች ነበሩ። በድሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሩብ ፍፃሜውን የተቀላቀለ ሲሆን ከሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና አሸናፊ ጋር እንደሚጫወት ይጠበቃል።