አርባምንጭ ከተማ ቅሬታ አለኝ ያለ ተረኛው ክለብ ሆኗል

አርባምንጭ ከተማ ከደደቢት ጋር የፊታችን ሰኞ እንዲያደርገው ቀን የተቆረጠለትን ተስተካካይ ጨዋታ አስመልክቶ ቅሬታውን ገልጿል። 

ክለቡ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፃፈው ደብዳቤ አስቀድሞ በ26/09/2010 ሊደረግ ለነበረው ጨዋታ አራት ቀናት ቀድም ብሎ ወደ አዲስ አበባ ያመራ እንደነበር እና ጨዋታው ለ28/09/2010 ተዘዋወሮ ከዛም በአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ህልፈት ምክንያት ሳይካሄድ መቅረቱን አስታውሷል። በወቅቱ ለሶስት ተጨማሪ ቀናት በአዲስ አበባ መቆየቱ ያስከተለበትን የፋይናንስ ቀውስ እና ይህ እንዲካካስም የበጀት ድጋፍ እንዲደረግለት መጠየቁንም በ01/10/2010 በፃፈው ደብዳቤ አሳውቆ እንደነበር ገልጿል።

አርባምንጭ የፊታችን ሰኞ ይደረጋል የተባለውን ይህን ተስተካካይ ጨዋታ ለመቀበል ይቸግረኛል ያለው ‘ያነሳሁትን ጥያቄ ያላገናዘበ እና ለተጨማሪ ኪሳራ እና እንግልት የሚዳርገኝ ነው’ በማለት ነው። የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ታዲዮስ ጨመሳ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ሀሳብ ሲያስረዱ ” በወቅቱ ሀዘን ነበር። ያን ተቀብለናል። ያ የሚያጋጥም ችግር ነበር። አሁን ላይ ግን ወቅቱን ያልጠበቀ በመሆኑ ለተጨማሪ ወጪ ሊዳርገን የሚችል ፕሮግራም ነው። ዳግም ወደ አዲስ አበባ ሂዱና ተጫወቱ መባሉ እኛን ጎድቶናል። መርሀ ግብሩ የእኛን ጥያቄ ሳያገናዝብ የተደረገም ጭምር ነው። በውጤት ማጣት ላይ ከመሆናችን በተጨማሪ ካለብን የበጀት እጥረት እና ከደረሰብን እንግልት አኳያ ጨዋታውን ማድረጉ ለኛ ተጨማሪ ራስ ምታት ነው። ” ብለዋል።

የፌድሬሽኑ በበኩሉ ” ጥያቄያቸው ተገቢ ቢሆንም የውድድር ዓመቱ እየተጠናቀቀ በመሆኑ እና ጊዜው እየሄደ መሆኑን ከግምት ውስጥ አስገብተን የወጣ መርሀ ግብር በመሆኑ በተያዘለት ቀን ይደረጋል።” ብሏል