አሰልጣኝ ሥዩም አባተ ቀዶ ጥገና ሊደረግላቸው ነው

ያለፉትን ወራት በህመም ላይ የሚገኙት አንጋፋው አሰልጣኝ ሥዩም አባተ የተሻለ ህክምና ለማግኘት ግንቦት 14 ወደ ታይላንድ ማምራታቸው ይታወቃል፡፡

አሰልጣኝ ሥዩምን ለማሳከም እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ኮሚቴ አባል የሆኑት የሙያ ባልደረባ እና የቅርብ ጓደኛ የሆኑት አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ታይላንድ ካቀኑበት ጊዜ አንስቶ ያሉበትን የጤና ሁኔታ ለሶከር ኢትዮዽያ ተናግረዋል።

” መጀመርያ ከነበረበት የግል ሆስፒታል በመቀየር በጥራትም ሆነ በዋጋም የተሻለ ወደ ሆነ የመንግስት ተሸጋግሯል። የህመሙ ሁኔታ ጥሩ መሻሻል እያሳየ ሲገኝ ሳይታሰብ በድንገት ከተኛበት አልጋ ተነስቶ በእግሩ ለመራመድ እየሞከረ ባለበት ሰዓት ከአጠገቡ የሚደግፈው ሰው ያልነበረ በመሆኑ ወድቆ ያልታሰበ ህመም አጋጥሞት ትንሽ ተደናግጠን ነበር። ከመደበኛ የህክምና ክትትሉ ውጭ የወደቀበት የሰውነቱ አካል ላይ ሌላ ህመም አጋጥሞት ሰሞኑን ህክምና እየተከታተለ መሆኑ አሳዛኝ ነገር ነው። አሁን አብሮት ወደ ታይላንድ የተጓዘውን ወንድሙ ሰለሞን አባተን በመቀየር ባለቤቱን ወ/ሮ ዙርያሽ እና የመጨረሻ ልጁን ኮሚቴው ባሳለፍነው ቅዳሜ ወደ ስፍራው የህክምናውን ጉዳይ እንዲከታተሉ ልኳቸዋል። በዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ ያለበትን ሁኔታ ማወቅ ያልቻልኩ ቢሆንም የፊታችን ሰኞ አልያም ማክሰኞ የቀዶ ጥገና ህክምናውን በተሳካ ሁኔታ ያደርጋል ብለን በተስፋ እንጠብቃለን። የቀዶ ጥገናውን ካጠናቀቀ በኋላ መቼ ወደ ሀገሩ ይመለሳል የሚለውን የህክምና ባለሙያዎቹ የሚወስኑት ይሆናል።”