በነገው እለት የሚካሄዱ ጨዋታዎች ተሰረዙ

በ27ኛው ሳምንት በፀጥታ ችግር ምክንያት ሳይካሄዱ ቀርተው ነገ እንዲደረጉ መርሀ ግብር ወጥቶላቸው የነበሩት የወላይታ ድቻ እና ወልዋሎ ዓ.ዩ እንዲሁም የሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታዎች መሰረዛቸው ታውቋል። ቦዲቲ እና ሀዋሳ ላይ ሊደረጉ ለነበሩት እነዚህ ጨዋታዎች መሰረዝ በምክንያትነት የቀረበው የደቡብ ፖሊስ ኮሚሽን በጨዋታዎቹ ላይ ለሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች ኃላፊነት እንደማይወስድ በማሳወቁ እንደሆነ ተነግሯል።

የ28ኛው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር ከመካሄዱ አስቀድሞ እንዲደረጉ ተወስነው የነበሩት ሁለቱ ጨዋታዎች በድጋሜ ሳይካሄዱ መቅረታቸው ከፌዴሬሽኑ በኩል ሌላ ማስተካከያ እንዲያስፈልግ ያደረገ ሲሆን የሊግ ኮሚቴውም በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ውስጥ ጉዳዩን ተመልክቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።