ደደቢት ከ አርባምንጭ ከተማ – ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ

ነገ ይደረጋሉ ተብለው ሲጠበቁ ከነበሩት ሶስት ተስተካካይ ጨዋታዎች መካከል ሁለቱ በመሰረዛቸው የዛሬው ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳችን አዲስ አበባ ላይ እንደሚካሄድ የሚጠበቀውን የደደቢት እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ ብቻ ይመለከታል።

ደደቢት ከ አርባምንጭ ከተማ

ከ25ኛው ሳምንት የተላለፈው ይህ ጨዋታ ሳይደረግ የቀረው በአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ድንገተኛ ህልፈት ምክንያት ነበር። ከዚህ በኋላ በነበሩት ሁለት ሳምንታት በተደረጉ ጨዋታዎች አርባምንጭ ከተማ ሁለት ነጥቦችን አሳክቶ ላለመውረድ የሚያደርገውን ትግል ባለበት የቀጠለ ሲሆን ደደቢት ደግሞ ምንም ውጤት ሳያስመዘግብ በነበረበት 34 ነጥብ ላይ ለመቆየት ተገዷል። በሁለተኛው ዙር ከአምስት ነጥቦች በላይ ማግኘት የተሳነው ደደቢት አሰልጣኙን በሞት መነጠቁ ተጨምሮበት የውድድር አመቱ ከዚህም በላይ አስቸጋሪ እንዳይሆነበት ያሰጋል። የመጀመሪያው ዙር ሲገባደድ በ16 ነጥብ ልዩነት ቁልቁል ሲመለከታቸው የነበሩ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች አሁን ልዩነቱን ወደ 5 ቀንሰው የያኔውን የሉጉ መሪ ስጋት ውስጥ ከተውታል። ደደቢት ከነገው ጨዋታ ጀምሮ ነጥብ መሰብሰብ ካልጀመረም ከዚህ በላይ አደጋ ውስጥ መግባቱ የሚቀር አይመስልም። 28 ነጥብ ላይ ለሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ደግሞ እስከ 10ኛ ደረጃ ከፍ የሚልበትን ዕድል የሚሰጠው በመሆኑ ጨዋታው ትልቅ ቦታ ይኖረዋል። ቀጣዩን ጨዋታ ሜዳው ላይ እንደማድረጉም ቡድኑ ነገን በድል ከተወጣ ተስፋውን ማለምለም ይችላል።

የደደቢቱ የመስመር አጥቂ አቤል ያለው ቡድኑ በቀይ ካርድ ቅጣት የሚያጣቸው አንዶህ ኩዌክ እና አስራት መገርሳን በ5 ቢጫ ካርድ ቅጣት የሚቀላቀላቸው ሲሆን አርባምንጭ ከተማ ግን በኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ በ5 ቢጫ ካርድ ምክንያት ያላሰለፈውን አለልኝ አዘነን ግልጋሎት ከማግኘቱ ውጪ የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና የለበትም።

የሳለፍነው ሳምንት የቡድኖቹ ጨዋታዎች በውጤት ብቻም ሳይሆን በሜዳ ላይ እንቅስቃሴም ለደደቢት ተጨማሪ ስጋት ለአርባምንጭ ከተማ ደግሞ ተስፋ ሰጪ ነበሩ። አሁንም በኳስ ቁጥጥር ላይ ትኩረቱን ያደረገው ደደቢት ከአዲስ አበባ የመጫወቻ ሜዳ አመቺ አለመሆን ጋር አብሮ መሄድ አልቻለም። በማጥቃት ላይ የሚያሳትፋቸውን ተጨዋቾች ቁጥር ከፍ በማድረጉ በኩል ችግር ባይታይበትም ሶስተኛው የሜዳ ክልል ላይ ለመድረስ የሚፈጅበት ጊዜ እና የሚበላሹት ቅብብሎቹ ለቡድኑ አደጋ መሆናቸው አልቀረም። ይህ ሁኔታ ቡድኑን ለመልሶ ማጥቃት የሚያገልጠው በመሆኑ እና አሁንም አስራት መገርሳን አለማያዙ ደግሞ በነገው ጨዋታ ላይ ዕክል እንደሚሆንበት ይታሰባል። የቡድኑ የኳስ ስርጭት መቋጫ የሆነው ጌታነህ ከበደ ነገም ማጥቃቱን የሚመራ ሲሆን ወደ ኋላ እየተሳበ ከአማካይ ክፍሉ ጋር ከሚያደርገው ግንኙነት ቡድኑ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚሞክር ይጠበቃል።

በአለልኝ አዘነ እና ወንደሰን ሚልኪያስ የአማካይ ክፍል ጥምረት የተከላካይ ክፍሉን በሚገባ የሚያግዘው አርባምንጭ ኳስ ተቆጣጥረው ለሚጫወቱ ቡድኖች ፈተና መሆን እንደሚችል የአዳማው ጨዋታ በሚገባ አሳይቶናል። ነገም ቡድኑ ለጥንቃቄ ቅድሚያ ሰጥቶ እና የመስመር ተከላካዮቹን ጭምር ሙሉ ለሙሉ በመከላከል ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን እንደሚጠባበቅ ይገመታል። እነዚህ አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ ደግሞ ቡድኑ በተለይም በግራው ወገኑ በእንዳለ ከበደ እየተመራ በፍጥነት ወደ ግብ ለመድረስ የሚደርገው ጥረት ተጠባቂ ነው። የእንዳለ ከበደ እና ስዩም ተስፋዬ የአንድ ለአንድ ግንኙነትም በዛው መጠን ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪ ድንቅ አቋሙን እያሳየ የሚገኘው አለልኝ አዘነ ተጋጣሚ መሀል ለመሀል ክፍተት ሲሰጥ በፍጥነት ሰብሮ በመግባት ማጥቃቱን የሚያግዝበት መንገድ ለአርባምንጭ ተጨማሪ ተስፋን የሚሰጥ ነው።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በበርካታ አቻዎች የታጀበው የሁለቱ ግንኙነት 13 ጊዜያት በሊጉ ሲስተናገድ ደደቢት 4 በማሸነፍ የበላይነት ይዟል። አርባምንጭ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በ7 አጋጣሚዎች አቻ ተለያይተዋል። ደደቢት 19፣ አርባምንጭ 13 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

– በአዲስ አበባ ስታድየም 6 ጊዜ ተገናኝተው ደደቢት ሁለት ጊዜ አሸንፎ አራት ጊዜ አቻ ሲለያዩ አርባምንጭ ምንም አላሸነፈም።

– ያለፉት ሶስት ተከታታይ የአዲስ አበባ ስታድየም ግንኙነቶች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። በተለይ ባለፈው ዓመት 24ኛ ሳምንት ላይ አርባምንጭ 2-0 ከመመራት ተነስቶ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ጎሎች አቻ የተለያየበት ተጠቃሽ ነው።

ዳኛ

– ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው መሪነት የሚካሄድ ይሆናል።