ሪፖርት | ወላይታ ድቻ እና ወልዋሎ ነጥብ ተጋርተዋል

ከ27ኛው ሳምንት ተላልፎ ዛሬ 9፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም የተደረገው የወላይታ ድቻ እና ወልዋሎ ዓ.ዩ ተስተካካይ ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በ26ኛው ሳምንት ከአርባምንጭ ጋር ያለ ግብ የተለያየው ወላይታ ድቻ በዛሬው ጨዋታ በበረከት ወልዴ እና ዮናታን ከበደ ምትክ አብዱልሰመድ ዓሊን እና ኃይማኖት ወርቁን የተጠቀመ ሲሆን ወልዋሎ ዓ.ዩ በበኩሉ ደደቢትን 1-0 ባሸነፈበት ጨዋታ የተጠቀመውን የመጀመሪያ ቡድን ዛሬም ይዞ ቀርቧል።

በሊጉ ለመቆየት በሚደረገው ትግል ውስጥ ከጨዋታው የሚገኘው ነጥብ በእጅጉ የሚያስፈልጋቸው ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታውን በከፍተኛ ፉክክር ነበር የጀመሩት። የአዲስ አበባ ስታድየም የመጫወቻ ሜዳ ምቹ ባይሆንም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ፈጣን እና ተመጣጣኝ ጨዋታን አስመልክተውን ነበር። አስርሩ ደቂቃዎች በዚህ መልኩ ያለፉ ቢሆንም ሙከራ ግን አልተስተዋለባቸውም። ኳስን ከኋላ መስርተው በአጫጭር ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት የሚታወቁት ወልዋሎዎች ቀስ በቀስ የበላይነቱን በመውስድ 13ኛው ደቂቃ ላይ አብዱርሀማኑ ፉሰይኒ ከሳጥን ውስጥ ባደረገው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ የድቻን ግብ መፈተሽ ጀምረዋል። የድቻን የተከላካይ መስመር በተደጋጋሚ ሰብረው መግባት አይሁንላቸው እንጂ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመውሰድ ከራሳቸው የሜዳ ክልል ርቀው መቆየት ችለውም ነበር።

በአመዛኙ በመከላከሉ ላይ ለማተኮር ተገደው የነበሩት ድቻዎች ከ15ኛው ደቂቃ በኋላ ተነቃቅተው ታይተዋል። በኃይማኖት ወርቁ እና ታድዮስ ወልዴ ጥምረት መሀል ሜዳ ላይ የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመቋቋም ጥረት በማድረግ በዋናነት በቀኝ መስመር አማካይነት በተሰለፈው እዮብ ዓለማየሁ በኩል አመዝነው ጫና መፍጠር ችለዋል። ሆኖም 17ኛው ደቂቃ ላይ ጃኮ አራፋት ከርቀት በቅጣት ምት በቀጥታ ከመታው እና 21ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልሰመድ ዓሊ ካደረገው ሙከራ ሌላ ተጨማሪ ግልፅ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ቡድኑ ይዞት በገባው የ4-2-3-1 አሰላለፍ የግራውን መስመር ይዞ ሲጫወት የነበረው በዛብህ መለዮ እንደወትሮው አለመሆንም ለድቻ የማጥቃት አማራጮች ማነስ ሌላው ምክንያት ነበር።

የወላይታ ድቻን መነቃቃት በማክሸፍ ወደ መጀመሪያው የበላይነታቸው የተመለሱት ወልዋሎዎች ቀሪውን የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች በበላይነት ማከናወን ችለዋል። በነዚህ ጊዜያትም ከአጫጭር ቅብብሎች ይልቅ ለሶስቱ የፊት አጥቂዎች የሚጣሉ ኳሶች ዋነኛ የቡድኑ መሳሪያዎች ነበሩ። 32ኛው ደቂቃ ላይ አብዱርሀማን ፉሰይኒ በግራ መስመር በአስገራሚ ሁኔታ የድቻን ተጨዋቾች በማለፍ ያደረገው ሙከራ ከተቋረጠበት በኋላ ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ከዛው ግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ሪችራድ ኦዶምጎ በግንባሩ አስቆጥሯል። ከዚህም ባሻገር 39ኛው ደቂቃ ላይ አብዱርሀማን ፉሰይኒ ከሳጥን ጠርዝ ላይ ሞክሮት በግቡ ቋሚ የተመለሰው እንዲሁም 44ኛው ደቂቃ ላይ ኦዶንጎ ወንደሰን ገረመውን አልፎ ወደ ግብ የላከው እና ተክሉ ታፈሰ ከመስመር ላይ ያወጣው ኳስ ከሶስቱ ተጨዋቾች ቅንጅት የተፈጠሩ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ታድዮስ ወልዴን አስወጥተው አመረላ ደልታታን ያስገቡት ድቻዎች ወደ ቀደመው የ 4-1-4-1 አሰላለፍ የመምጣታቸውን ውጤት የተመለከቱት በ3 ደቂቃዎች ውስጥ ነበር። 48ኛው ደቂቃ ላይ ነፃ ሆኖ በግራ መስመር ኳስ የተቀበለው ጃኮ አራፋት ወደ ውስጥ ሲያሻማ ዮሀንስ ሽኩር በሚገባ ባለማራቁ በቦታው ይገኝ የነበረው አመረላ ደልታታ ወደ ግብ ለውጦታል። ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ ተጠናክረው የቀረቡት ወላይታ ድቻዎች ጨዋታው ሊጠናቀቅ 15 ደቂቃዎች እስኪቀሩት ድረስ የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። 52ኛው ደቂቃ ላይ ጃኮ አራፋት ከአመረላ ከደረሰው ኳስ ከሳጥን ውስጥ በቀጥታ ያደረገው ሙከራ እንዲሁም 74ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ ከጃኮ በደረሰው ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ያልተጠቀመበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪ 58ኛው ደቂቃ ላይ እሸቱ መና ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ እዮብ ዓለማየሁ በግንባሩ ማስቆጠር ችሎ የነበረ ቢሆንም ከጨዋታ ውጪ በመሆኑ ሳይፀድቅለት ቀርቷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸውን የበላይነት ያጡት ወልዋሎ ዓ.ዩዎች በቁጥር ተበራክተው ተሻጋሪ ኳሶችን በመጠቀም ተደጋጋሚ ጥቃት የሰነዘረውን ተጋጣሚያቸውን ጫና ከመቋቋም ባለፈ ወደ ፊት ገፍተው መሄድ ተቸግረው ታይተዋል። አስፈሪ የነበረው የቡድኑ የሶስትዮሽ የፊት ጥምረትም በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ከመቆየት ይልቅ ለአማካይ ክፍሉ ቀርቦ ቅብብሎችን ለመከውን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ይህ ሁኔታ ከድር ሳሊህ ፕሪንስ ሰቨሪንሆን ቀይሮ ከገባ በኋላ የቀጠለም ሲሆን ቡድኑ የመጨረሻ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችል ቀርቷል። ጨዋታውም እንደ አጀማመሩ ሳይሆን እየተቀዛቀዘ መጥቶ በ1-1 ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል። በመሆኑም ሁለቱም ቡድኖች 31 ነጥብ ላይ ሲደርሱ ወላይታ ድቻ በነበረበት 11ኛ ደረጃ ላይ ወልዋሎ ዓ.ዩ ደግሞ 12ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጡ ሆኗል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ – ወላይታ ድቻ

ሜዳው ለሁለታችንም ከፍተኛ ተፅዕኖ ነበረው። ነገር ግን ውጤቱን ስለምንፈልገው ጥሩ ተፎካክረናል። በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ አልነበርንም ፤ በሁለተኛው አጋማሽ ግን የአሰላለፍ ለውጥ አድርገን ነገሮችን አስተካክለናል። ውጤት ተጋርተን መውጣታችንም ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው። የተሻረው ጎል የዳኞች ውሳኔ ነው። ከዚህ ውጪ ግን ዳኛው (ለሚ ንጉሴ) ሜዳው ባይመችም ተሯሩጦ በትጋት በመዳኘቱ ምስጋና ይገባዋል።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወልዋሎ ዓ.ዩ

ተስተካካይ ጨዋታ በመሆኑ በጉዞ ደክመን ነው እዚህ የደረስነው። ካለንበት ሁኔታ አንፃር ጨዋታው ወሳኝ በመሆኑ ተጠንቅቀን ነው የተጫወትነው። በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ነበርን ፤ ከእረፍት መልስ ግን በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ተጭነውን ነበር። ሆኖም ሜዳው ለሁለታችንም የተመቸ ባይሆንም እልህ እና ታታሪነት የተሞላበት ጨዋታ ነበር። በአጠቃላይ ግን በአቻ ውጤት መጠናቀቁ ለሁለታችንም ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ።