ፕሪምየር ሊግ | የ28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ – ክፍል 1

ነገ ከሚከናወኑት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መካከል ሶስቱ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ መሳኝ ድርሻ ይኖራቸዋል። የዛሬው ክፍል አንድ ቅድመ ዳሰሳችን ትኩረቶችም እነዚሁ ጨዋታዎች ይሆናሉ።

ጅማ አባ ጅፋር ከ ደደቢት

እንደ ደደቢት የመጀመሪያ ዙር ጉዞ ቢሆን ኖሮ ይህ ጨዋታ የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ የመሆን አቅም ነበረው። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታ በተፈጠረው ረብሻ ከሜዳው ውጪ ይህን ጨዋታ እንዲያደርግ የተወሰነበት ጅማ አባ ጅፋር ከሁለት ተከታታይ ድሎች በኋላ ነው አዳማ ላይ ደደቢትን የሚያስተናግደው። አባ ጅፋር በአዲስ አበባ ስታድየም በመከላከያ እና ወልዲያ ላይ ያሳካቸው ድሎች በሊጉ አናት እንዲቆይ የረዱት ሲሆን ቀሪዎቹን ሶስት ጨዋታዎች በድል መወጣት አመቱን በሻምፒዮንነት ለመጠናቀቅ የሚያበቃው በመሆኑ ይህን ጨዋታ በታላቅ ትኩረት የሚያደርገው ይሆናል። በመጀመሪያው ዙር ከስድስቱ ተከታታይ ድሎቹ ያደናቀፈው አባጅፋር ላይ ተመሳሳይ ታሪክ የመስራት ዕድል የገጠመው ደደቢት ጥሩ ጊዜ ላይ አይገኝም። ከዘጠኝ ሳምንታት በኋላ አርባምንጭን የረታበት ውጤትም በቀረበበት የተጨዋች ተገቢነት ክስ ምክንያት በፎርፌ የሚተካበት ዕድል ሊኖር ይችላል። በመሆኑም በመጀመሪያው ዙር የደረሰበትን ሽንፈት ከመበቀል ባለፈ ቅጣቱ ቢተላለፍበት እንኳን አሁን በደረጃ ሰንጠረዡ ተረጋግቶ የተቀመጠበትን ቦታ ለማጠናከር የሊጉን መሪ መፈተኑ እንደማይቀር ይታመናል።

የጅማ አባ ጅፋሮቹ ቢኒያም ሲራጅ እና ኄኖክ ኢሳያስ በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ ሲሆኑ ደደቢት በበኩሉ ኩዌኪ አንዶህ ቢመለስለትም አስራት መገርሳ እና ስዩም ተስፋዬን በቅጣት እንደሚያጣ ተሰምቷል።

የጎል ልዩነቱን ማስፋት የሚጠበቅበት ጅማ አባ ጅፋር ከጥሩው የመከላከል አደረጃከቱ ባለፈ በማትቃቱም በኩል ተሻሽሎ መቅረብ ይጠበቅበታል። እየተቀያየሩ ወድ ኋላ በመመለስ ከአማካይ ክፍላቸው ጋር በመገናኘት የተጋጣሚን የተከላካይ ክፍል ግርታ ውስጥ የሚከቱት ሁለቱ አጥቂዎች ኦኪኪ አፎላቢ እና ተመስገን ገብረ ኪዳን ደካማውን የደደቢት የኋላ ክፍል መፈተናቸው የማይቀር ነው። ለዚህ ደግሞ የቡድኑ የመስመር አማካዮች እና የመስመር ተከላካዮች በተለይም ኄኖክ አዱኛ ሚና ከፍ ያለ ነው። ብዙም ክፍተት በማይገኝበት የአባ ጅፋር የተከላከይ መስመር እና የተከላካይ አማካዮች መሀል ክፍተትን ለማግኘት እንደሚሞክር የሚጠበቀው ጌታነህ ከበደ ደግሞ እንደ ሁልጊዜው የቡድኑ የፊት መስመር የመምራት ሀላፊነት ይኖርበታል። ሆኖም የተጨዋቹ እንቅስቃሴ ለበድኑ የመስመር አጥቂዎች ወደ ውስጥ የመግቢያ ክፍተት የሚፈጥር እና ለሁለቱ የማጥቃት አማካዮች ጥምረት የተመቸ መሆን ይገባዋል። በአጠቃላዩ የጨዋታው ሂደት ደደቢት ይበልጥ ለኳስ ቁጥጥር ቦታ የሚሰጥበት አባ ጅፋር ደግሞ በፈጣን ሽግግር በቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ የሚሞክርበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– የ13ኛው ሳምንት የሁለቱ ቡድኖች የአዲስ አበባ ስታድየም ግንኙነት በጅማ አባ ጅፋር 2-1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር። ውጤቱ የደደቢትን የስድስት ጨዋታ የማሸነፍ ጉዞም የገታ ሆኖ አልፏል።

– ጅማ አባ ጅፋር ከ22ኛው ሳምንት ጀምሮ አራት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች ከገጠሙት በኋላ መከላከያ እና ወልዲያን ማሸነፍ ችሏል። በነዚህ ጨዋታዎች ሶስት ግቤችን ያስቆጠረ ሲሆን አንዴም መረቡን ሳያስደፍር ወጥቷል።

– ደደቢት 10 ግቦችን ካስተናገደባቸው አራት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ አርባምንጭ ከተማን 2-1 በመርታት ከ86 ቀናት በኋላ ሶስት ነጥብ ያሳካበትን ውጤት አስመዝግቧል።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

ሲዳማ ቡና ከ መቐለ ከተማ

ለሁለቱም ተገጣሚዎች ወሳኝ በሆነው በዚህ ጨዋታ ከወራጅ ቀጠናው ጋር የሶስት ነጥብ ልዩነት ብቻ ያለው ሲዳማ ቡና ከመሪው በሁለት ነጥብ ርቀት የተቀመጠው መቐለ ከተማን ያስተናግዳል። አዳማ ላይ ያሳካው ድል በፎርፌ ከተተካ በኋላ ሲዳማ ከሀዋሳ ከተማ ነጥብ ተጋርቶ ድሬዳዋን ቢያሸንፍም በ27ኛው ሳምንት በፋሲል ከተማ ያስተናገደው ሽንፈት ከስጋት እንዳይላቀቅ አድርጎታል። ይህን ጨዋታ በድል መወጣትም ቡድኑን ካለበት ስጋት የሚያላቅቀው በመሆኑ ዋጋው እጅግ ከፍ ያለ ነው። በ27ኛው ሳምንት መከላከያን ያሸነፈው መቐለ ከተማም ውጤቱን አጥብቆ ይፈልገዋል። ከድሬዳዋ ከተማ እና ከፋሲል ከተማ ሙሉ ውጤት ማግኘት ያልቻለው መቐለ ያገኘውን ሊጉን የመምራት ዕድል አጥቶ ወደ አራተኝነት ተንሸራቷል። ቡድኑ ሻምፒዮን ለመሆን ከበላዩ የሚገኙት ሶስት ክለቦች ነጥብ እንዲጥሉ የግድ የሚል ቢሆንም የራሱን የሶስት ሳምንታት ጨዋታዎች በድል ማጠናቀቅ እና በርከት ያሉ ግቦችን ማስቆጠር ግን የራሱ የቤት ስራ ይሆናል።

በሲዳማ ቡና በኩል የጉዳት ዜና ባይኖርም ከክለቡ ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ የገባው እና ያለፍትን ሶስት ቀናት ልምምድ ላይ ያልተገኘው ባዬ ገዛኸኝ ከጨዋታው ውጪ መሆኑ ተነግሯል። የመቐለ ለተማዎቹ ቢስማርክ ኦፖንግ እና አንተነህ ገ/ክርስቶስ ደግሞ ልምምድ የጀመሩ ግን ደግሞ ለጨዋታው ብቁ መሆናቸው ያልታወቁ ተጨዋቾች ናቸው።

ከሶስቱ ፊት አውራሪዎቹ መሀከል ባዬ ገዛሀኝን የማይጠቀመው ሲዳማ ቡና አሁንም የመስመር አጥቂዎቹን ወደ ግብ የመድረሻ አማራጭ አድርጎ ቢጠቀምም አማካይ ክፍሉም ጥሩ ጥንካሬ እየተላበሰ ይገኛል። ሆኖም በዮሴፍ ዮሀንስ የሚመራው ይህ የቡድኑ የመሀል ክፍል ከተጋጣሚው ወደ መሀል ሜዳ የማይቀርብ የተከላካይ ክፍል አንፃር በቀላሉ ለመስመር አጥቂዎቹ ኳስ የሚያደርስበት ክፍተት ላያገኝ ይችላል። በመሆኑም ከሌላው ጊዜ በተለየ ለኳስ ቁጥጥር የተሻለ ቦታ ያለው ሲዳማ ቡናን ልናይ የምንችልበት ዕድል ይኖራል። በመቐለ ከተማዎች በኩል ግቦች ወሳኝ መሆናቸው ሲታሰብ ቡድኑ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ላይ ካተኮረው የማጥቃት አጨዋወቱ በተሻለ የማጥቃት ተሳትፎ ባላቸው ተጨዋቾች የሚታገዝ አቀራረብ ያስፈልገዋል። በዚህም የማጥቃት ተሳትፎ የሚያደርጉ የመስመር ተከላካዮች ፣ ወደ ውስጥ አጥብበው መግባት የሚችሉ አማካዮች እንዲሁም የሚካኤል ደስታን ወደ ፊት የተገፋ እንቅስቃሴ ያስፈልገዋል። ከዚህ ውጪ ቡድኑ በተሻጋሪ ኳሶች አጠቃቀም ላይ ያለውን ጥንካሬም ተጨማሪ ዕድሎችን የመፍጠሪያ አማራጭ አድርጎ ሊጠቀምበት ይችላል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበት የሊጉ ጨዋታ በመጀመሪያው ዙር መቐለ ላይ ተደርጎ በባለሜዳው 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

– ሲዳማ ቡና ለመጨረሻ ጊዜ በሜዳው ያደረጋቸውን ሶስት ጨዋታዎች በሙሉ በ1-0 ውጤት ማሸነፍ የቻለ ሲሆን አዳማ ላይ ያሳካው ድል ግን በተጨዋች ተገቢነት ክስ ምክንያት በፎርፌ ተተክቷል።

– መቐለ ከተማዎች ካለፉት አራት ጨዋታዎቻቸው ውስጥ ግብ ሳያስቆጥሩ የወጣባቸው ሁለቱ ጨዋታዎች ከመቐለ ውጪ የተደረጉ ነበሩ።

ዳኛ

– ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የመምራት ሀላፊነት የተሰጠው ለኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሃን ነው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ

ከሁለት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ ውስጥ ለመካተት የተጫወቱት ሁለቱ ቡድኖች ነገ ደግሞ በሊጉ ሁለተኛ ዙር እዛው አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ይገናኛሉ። ለአራት ሳምንታት ከአንድ በላይ ግብ ማስቆጠር ተስኖት የቆየው ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን አስመዝግቦ በነጥብ የተስተካከለው የሊጉ መሪ አባ ጅፋርን በግብ ልዩነትም ደረስኩብህ እያለው ነው። ከ22ኛው ሳምንት በኋላ ከሽንፈት የራቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዳለፉት አመታት ሁሉ የሊጉን አጨራረስ ለማሳመር እየተንደረደረ ቢመስልም ይህን ጨዋታ ጨምሮ ቀጣዮቹን ሁለት ሳምንታት በርከት ያሉ ግቦችን እያስቆጠረ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ከአፍሪካ ኬንፌዴሬሽን ዋንጫ ከወጣ በኋላ እያበበ መጥቶ የነበረው የውድድር ዘመኑ ዳግም መጨላለም የጀመረው ወላይታ ድቻ ከመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎቹ ሁለት ነጥቦችን ብቻ ነው ያገኘው። የደረሰበት 31 ነጥብም ከወራጅ ቀጠናው እምብዛም አላራቀውም። በመሆኑም በመጀመሪያው ዙር ሶዶ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስን የ11 ሳምንታት ያለመሸነፍ ጉዞ የገታበትን ውጤት ነገም በመድገም ቀስ በቀስ ከገባበት የመውረድ ስጋት ለመውጣት ጉዞ መጀመር ይኖርበታል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወሳኝ አማካዩ ናትናኤል ዘለቀን ከጉዳት መልስ የሚጠቀም ሲሆን ሳላሀዲን ሰይድ ፣ ሪቻርድ አፒያ እና አማራ ማሌ ግን አሁንም በጉዳት ከቡድኑ ውጪ ናቸው። በወላይታ ድቻ በኩል ተከላካዩ ተስፉ ኤልያስ በጉዳት ጨዋታው የሚያልፈው ሲሆን በልምምድ ላይ ጉዳት የገጠመው ውብሸት አለማየሁ ደግሞ የመግባት እና ያለመግባቱ ጉዳይ አለየለትም።

ከናትናኤል ዘለቀ መምጣት በኋላ እርጋታን መላበስ የቻለው የቅዱስ ጊዮርስጊስ አማካይ ክፍል ቡድኑ ሁነኛ አጥቂ ባይኖረውም እንኳን ግቦችን ማግኘት እንዳይቸግረው እያደረገ ይገኛል። በተለይም የመስመር አማካዩ ኦስካር ታቫሬዝ ሚና እየጎላ የመጣ ሲሆን በነገው ጨዋታም ከዚህ ተጨዋች የሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች እና ወደ ውስጥ ዘልቆ የሚገባባቸው ጊዜያት ወሳኝ ይሆናሉ። ቀስ በቀስ የማጥቃት ተሳትፏቸው ከፍ እያሉ የመጡት የቡድኑ የመስመር ተከላካዮችም ከተጋጣሚያቸው ወጣት የመስመር አማካዮች ጋር ሲገናኙ የሚኖራቸው ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በነገው ጨዋታ አስፈላጊ ይሆናል። ወላይታ ድቻ ታድዮስ ወልዴን እና ኃይማኖት ወርቁን በአንድነት በማሰለፍ በአርባምንጩ ጨዋታ ደካማ እንቅስቃሴ በማድረጉ ወደ መጀመሪው ዕቅዱ እንደሚመለስ ይጠበቃል። በዚህም እንደ እዮብ አለማየሁ እና አመረላ ደልታታ አይነት የመስመር አማካዮችን በመጠቀም ጃክ አራፋትን መዳረሻ ያደረጉ የመስመር ጥቃቶችን መሰንዘር የቡድኑ ዋነኛ ዕቅድ የመሆን ዕድል አለው። በኢትዮጵያ ዋንጫው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከፍተኛ ብልጫ የተወሰደበት ወላይታ ድቻ በቅርብ ጊዜ ልዩነት ይህን ጨዋታ ማድረጉ የጥሎ ማለፉ ጨዋታ ላይ የታየበትን ክፍተቶች አስተካክሎ የመምጣት አጋጣሚን እንደሚፈጥርለትም ይታመናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ እስካሁን 9 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 4 ድል በማስመዝገብ ቀዳሚ ሲሆን 2 ጊዜ ወላይታ ድቻ አሸንፏል። በቀሪዎቹ 3 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ፈረሰኞቹ 13 ሲያስቆጥሩ የጦና ንቦቹ 6 አስቆጥረዋል።

– አዲስ አበባ ላይ 4 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 3 ሲያሸንፍ ወላይታ አንድ ጊዜ (በመጀመርያ ግንኙነታቸው) ማሸነፍ ችሏል።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለተኛው ዙር አራት ጊዜ የክልል ቡድኖችን ያስተናገደ ሲሆን ስምንት ግቦች በማስቆጠር ሁለት ጊዜ ብቻ መረቡ ተደፍሮ ሁሉንም ጨዋታዎች አሸንፏል።

– ወላይታ ድቻ በሁለተኛው ዙር በአንድ አጋጣሚ ብቻ ወደ አዲስ አበባ ስታድየም የመጣ ሲሆን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ተመልሷል።

ዳኛ

– ጨዋታው በፌደራል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው መሪነት ይከናወናል።